የወያኔ የግብርና ሚኒስቴር የጋምቤላ ነዋሪዎችን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

በብርሃኑ ፈቃደ | ሪፖርተር

በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በመዠንገር ዞን የጐማሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር አመራሮች፣ ነዋሪዎችና የአካባቢ ተወላጅ ምሁራን በቀበሌያቸው ለዘመናት ሲጠበቅ የቆየ ደን ላልተገባ ኢንቨስትመንት መዋሉን ‹‹ሕገወጥ ነው›› በሚል ደጋግመው ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት የሚያቀርቡትን ጥያቄ እንደማይቀበል ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ከበደ፣ ‹‹ደኖችን ዝም ብለን ይዘን መቀመጥ አንችልም፤›› በሚል ደኖች ይጠበቁልን የሚለውን ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉ፣ ቬርዳንታ ሃርቨስትስ ለተባለው የህንድ ኩባንያ የተሰጠው 3012 ሔክታር የደን ይዞታ ለሻይ ልማት ስለሚውል፣ ሕዝቡም የሚፈልገው ልማትን በመሆኑ፣ እየቀረበ ነው የሚባለው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሻይ ልማቱ በራሱ ደን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኢሳያስ፣ በ3012 ሔክታር መሬቱ ላይ ከሻይ ቅጠል ባሻገር የቡና ተክልና ሌሎችም የእርሻ ሥራዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ እየተነሳ ያለው ጥያቄ የኅብረተሰቡ ሳይሆን፣ ‹‹የጥቂት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድምፅ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ከቀበሌው ምክትል ሊቀመንበር ጀምሮ ወደ ላይ ካሉት ኃላፊዎች ጋር በጋራ ስምምነት የተደረገበትን የኅብረተሰብ የልማት ጥያቄ እያስተናገደ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ በቃለ መጠይቁም ወቅት ሰነዶችን አሳይተውናል፡፡

በአንፃሩ በቀበሌው ዋና ሊቀመንበር አቶ ታምሩ አምበሎ የተመሩት የአካባቢው ተወላጆች ከ1,500 በላይ የሚጠጋ ፊርማ አሰባስበው ደኑ እንዳይነካ ከመጠየቃቸውም በላይ፣ በክልሉ የመዠንገር ዞን፣ ጐደሬ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽሕፈት ቤትና በአራት ማኅበራት (ገጂ፣ ዕድገት ባንድነት፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፤ ልማትና አጠቃቀም የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥር ሆነዋል) መካከል የደን አስተዳደር የውል ስምምነት በኅዳር ወር 2003 ዓ.ም. መፈረሙን የሚገልጽ ሰነድ ሪፖርተር ጋዜጣ አግኝቷል፡፡

በአንድ በኩል ልማቱ አስፈላጊ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በሌላ በኩል የሚነገረው ጉዳይ ግን በኅብረተሰቡ የተመነጠሩ ደኖች ላይ ብቻ የሚካሄድ የእርሻ ልማት እንቅስቃሴ መሆኑን ነው አቶ ኢሳያስ ለሪፖርተር የተናገሩት፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው፣ ታህሣሥ አንድ ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ቀደም ሲል የወረዳው ነዋሪዎች ተመሳሳይ አቤቱታ አቅርበው ጉዳዩን ለፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጽሑፍ አስታውቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

‹‹ለግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር በቁጥር 818-4/1124፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2002 ዓ.ም. የተጻፈ ደብዳቤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪካን ወክላ በምትደራደርበት ወቅት፣ እንዲሁም ከእርሻው ይልቅ ከካርቦን ትሬዲንግ የምናገኘው ጥቅም የበለጠ ስለሆነ፣ ደኑ የማይነካበት ሁኔታ እንዲመቻች ማሳሰቡ ይታወሳል፤›› በማለት ፕሬዚዳንት ግርማ ለግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ጽፈውላቸዋል፡፡

ደብዳቤው በዚህ አላበቃም፤ ‹‹ስለሆነም በቅርብ ቀን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተን የደረስንበትን እያስታወስኩ፣ አገራችን በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በዓለም አቀፍ መድረኮች በጠቅላይ ሚኒስትራችን አማካይነት አፍሪካን ወክላ በምትደራደርበት ወቅት፣ በምንም ምክንያት የደን መሬት ለእርሻ መሰጠት ስለሌለበት ደኑን ለማልማት በሚፈልጉ ሰዎች ወይም በሕዝብ ተሳትፎ እንዲለማ በክቡርነትዎ በኩል ተገቢው እንዲፈጸም እጠይቃለሁ፤›› በሚል ይቋጭና ግልባጭ ለጐማሬ ቀበሌ ሊቀመንበር ለአቶ ታምሩ አምበሎ መሰጠቱን ያመለክታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ዘገባ ያወጣን ሲሆን፣ በወቅቱ ያነጋገርናቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡቦንግ በደኑ ላይ የሚደርስ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመኖሩ በጥናት መረጋገጡን አስታውቀው ነበር፡፡

አቶ ኢሳያስ በአንድ በኩል 3012 ሔክታር መሬቱ የተመረጠው የቁጥቋጦ ቦታ በመሆኑ እንደሆነ ቢገልጹልንም፣ በሌላ በኩል ግን በአካባቢው የሚገኘው መቆረጥ ያለበት ሁሉ እንደሚቆረጥ ገልጸዋል፡፡ ሻይ በራሱ ደን እንደሆነ፣ የሙያ ሥነ ምግባር፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሥራዎችና የመሳሰሉት ሁሉ ተግባራዊ ከተደረጉ በኋላ ልማቱ እንደሚካሄድ ተከራክረዋል፡፡

ሌላ ቦታ ልማቱን ማካሄድ አይቻልም ወይ? በሚል ለጠየቅናቸውም፣ ሻይ በባህሪው ከፍተኛ የዝናብና የሙቀት መጠን፣ አሲዳማ መሬትና የመሳሰሉትን የሚፈልግ በመሆኑና እንዲህ ያሉት መሬቶች ደግሞ የሚገኙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል ከ7,500 ሔክታር በላይ መሬት ለሻይ ልማት መዋል እንደሚችል መጠናቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ በጐማሬ ቀበሌ የሚገኘው ደን ቁጥቋጦ እንደሆነ ቢናገሩም፣ በጋምቤላ ክልል፣ የመሬት አጠቃቀም፣ አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ አስተባባሪነት ለማኅበራቱ አስተዳድሩት ተብሎ የተሰጠው ቦታ ጥቅጥቅ ደን ከመሆኑም ባሻገር፣ በስም የተጠቀሱ ወንዞችንና ምንጮችን በውስጡ ያቀፈ ስለመሆኑ በደን አስተዳደር የውል ስምምነቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

በ3012 ሔክታር መሬት የሰፈረው የደን ሀብት ጥብቅ በመሆኑ እንዳይነካ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከለከል የቆየ መሆኑን፣ ሼክ መሐመድ አላሙዲንን ጨምሮ ሦስት ኢንቨስተሮች ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ 6,000 ቶን የሻይ ምርት ከ2,700 ሔክታር ይመረታል ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ በአገሪቱ ከ500,000 ሔክታር በላይ የሻይ ልማት ሊካሄድባቸው የሚችሉ ቦታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በጋምቤላ ክልል ጐማሬ ቀበሌ የተጀመረው የሻይ ልማት እንቅስቃሴ እንደማይቋረጥ አስረግጠዋል፡፡

ቬርዳንታ ሃርቨስትስ በሔክታር 111 ብር ሒሳብ የአንድ ዓመት የመሬት ኪራይ ክፍያ ለክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገቢ ያደረገ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡