የመድረክ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል አቶ ሙሉ መጃ አረፉ

(ሪፖርተር) — የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሥራችና ምክትል ሊቀመንበር፣ የኅብረት መሥራችና የመድረክ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ሙሉ መጃ፣ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው መስከረም 4 ቀን 2003 ዓ.ም. አረፉ፡፡

አቶ ሙሉ ከ1959 ዓ.ም. እስከ 1965 ዓ.ም. ለሁለት ተከታታይ ጊዜ በመመረጥ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በፓርላማ የወላይታ ሕዝብ እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1965 እስከ 1975 ዓ.ም. በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ በቶች በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ በ1983 ዓ.ም. የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን መሥርተዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ኅብረት ሲቋቋምም ከኅብረቱ መሥራቾች ከእነፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር አብረው ሠርተዋል፡፡ የኅብረቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ኅብረቱ የመድረክን ጥምረት ሲፈጥር አብረው በማቋቋም በመድረኩ ውስጥ የማዕከላዊ ምክር ቤቱ አባል በመሆን እስከ እለተ እረፍታቸው ድረስ አገልግለዋል፡፡

አቶ ሙሉ ከባለቤታቸው ጋር ለ53 ዓመት በትዳር የኖሩ ሲሆን፣ የ10 ልጆች አባትና 16 የልጅ ልጆችን እንዳዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡