የአላሙዲ ኩባንያ 5,000 ሰራተኞች ከፊሊፒንስ ወደ ኢትዮጵያ ሊያስመጣ ነው

ኃያል ዓለማየሁ | The Reporter

ከጥቂት ወራት በፊት የሚድሮክ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን የተረከበው በሚድሮክ ጥላ ሥር የሚገኘው ሜፖ የተባለው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ቢሮ፣ አምስት ሺሕ የፊሊፒንስ ዜጎችን ለመቅጠር ዝግጅት ማጠናቀቁን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡ የእነዚሁ የውጭ አገር ዜጎችን ቅጥርም በኢትዮጵያ ሠራተኞች ላይ ስጋት መፍጠሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 350 የሚሆኑ የፊሊፒንስ ዜጎች የአፍሪካ ኅብረት በሚድሮክ ወይም በሜፖ የሚያስገነባውን ሆቴል ጨምሮ፣ በተለያዩ የሜፖ ፕሮጀክቶች ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቀደም ሲል የእነዚሁ በሜፖ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ የፊሊፒንስ ዜጎች ቁጥር 400 ደርሶ እንደነበር የገለጹት ምንጮች፣ የተወሰኑት በቀን ሥራ ላይም ተመድበው ይሠሩ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሜፖ እነዚህ አምስት ሺሕ የሚሆኑ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በዓለም ላይ የታወቁ የፊሊፒንስ ዜጎችን ለመቅጠር የወሰነው፣ በተለይ የአፍሪካ ኅብረት በቀድሞው ከርቸሌ በሚያሠራው ሆቴልና ሌሎች ፕሮጀክቶች በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ሥር በነበሩበት ጊዜ እጅግ ተጓተው የነበሩ በመሆኑ፣ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማፋጠን እንደሆነ ታውቋል፡፡

ሜፖ የወሰደው ዕርምጃ አንዳንድ ሠራተኞች ላይ ከሥራ ህልውና ጋር በተያያዘ ስጋት መፍጠሩን የጠቆሙት ምንጮቻችን፣ እነዚሁ የፊሊፒንስ ዜጎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የሚሠሩዋቸውን የግንበኛ፣ የአናጢነትና የመሳሰሉትን ሥራዎች እየተቆጣጠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለእነዚሁ አምስት ሺሕ ለሚሆኑና በመላው በአገሪቱ በሚገኙት የሜፖ ፕሮጀክቶች ላይ ለሚሳተፉት ፊሊፒያውያን፣ ድርጅቱ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወሰደው ሰፊ ቦታ ላይ የመኖሪያ መንደር በማዘጋጀት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

ይህንኑ ሁኔታ እንዲገልጹልን የሜፖ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሆኑት ለሚስተር ባሲም አልዳኸር በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይም ጉዳይ የሚመለከታቸውን ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን አግኝተን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አብዛኛዎቹ በስምንተኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ ስለነበሩ አልተሳካም፡፡

ሜፖ የተረከባቸውን ፕሮጀክቶች ለማቀላጠፍ አዳዲስ ማሽኖችና የግንባታ መሣሪያዎች በብዛት በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡

በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ሥር በነበሩበት ወቅት የተጓተቱትን በርካታ ፕሮጀክቶች ለማፋጠን፣ በውጭ አገር ዜጋ የሚመራው ሜፖ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡