የመብራት ሃይል እጥረት መባባስ
ዳዊት ታዬ | ሪፖርተር
ለተከታታይ ዓመታት በኃይል እጥረት ሳቢያ ተፈጥሮ የነበረው የኃይል መቋረጥ ችግር በተወሰነ ደረጃ መሻሻል ታይቶበት የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እንደገና በስፋት መታየት ጀምሯል፡፡
ከ60 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ያመነጩ የነበሩ ጄኔሬተሮች ሥራ አቁመዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ፣ በናዝሬትና በደብረ ዘይት አካባቢ ቢያንስ በሳምንት ውስጥ በተደጋጋሚ ቀናት ለሰዓታት የኃይል መቋረጥ አለ፡፡ ይህም ኮርፖሬሽኑ በይፋ ሳይናገር በፈረቃ ኃይል ማደል መጀመሩን የሚያሳይ ነው እየተባለ ነው፡፡
በቃሊቲ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አንድ ባለሀብት እንደጠቆሙት፣ ባሳለፍነው ሦስት ሳምንት ውስጥ በየሳምንቱ ሐሙስ፣ ሐሙስ ከ12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ ኃይል ሲቋረጥባቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በየሳምንቱ ሐሙስ ለሰዓታት የኃይል መቋረጥ እየገጣማቸው በመሆኑም፣ እንደቀድሞው የኃይል አቅርቦት በፈረቃ መታደል እንደጀመረ አድርገው ወስደውታል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ የኃይል ችግር የለም፤ ኃይልም በፈረቃ እየታደለ አይደለም፡፡
በሌሎች የከተማው ክፍልም ተመሳሳይ የሆነ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን የሚገልጹት የከተማው ነዋሪዎች፣ በተለይ ምሽት ላይ ለተከታታይ ሰዓታት ኃይል የሚቋረጠው፣ የኃይል እደላ በፈረቃ መሆኑን እንድናምን አድርጎናል ይላሉ፡፡
የኃይል እደላው እንደቀድሞው በፈረቃ እየታደለ ከሆነም ኅብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ መነገር ነበረበትም የሚሉት ነዋሪዎች፣ ባልተጠበቀ ቀንና ሰዓትም የኃይል አቅርቦት መቋረጥ መከሰቱ ለሥራም እንቅፋት እየሆነ ነው ብለዋል፡፡
የገርጂ አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ ቀደም ሲል በሳምንት አንድ ቀን ለሰዓታት የኃይል አቅርቦት ይቋረጥባቸው እንደነበር ገልጸው፣ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በየቀኑ ለተከታታይ ሦስት ሰዓታት ኃይል ተቋርጦባቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ካነጋገርናቸው አብዛኛዎቹ የከተማ ነዋሪዎች ገለጻ ለመረዳት የተቻለው፣ ቢያንስ በሳምንት ውስጥ በየቀኑ ከሦስት ሰዓት ያላነሰ የኃይል መቋረጥ የሚከሰት መሆኑን ነው፡፡
ምሽት ላይ የሚቋረጠው የኃይል አቅርቦት የሚለቀቀው ደግሞ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ በመሆኑ፣ ሆን ብሎ የተደረገ የኃይል ማቋረጥ ተግባር እንደሆነ ያመለክታልም ብለዋል፡፡
አቶ ምስክር ግን በተሰጡት አስተያየቶች ላይ አይስማሙም፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ እየታየ ካለው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንጻር የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ብለዋል፡፡
‹‹በተለይ ከ12 ሰዓት እስከ ሦስትና አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኃይል መጨናነቅ ይታያል፡፡ ይህም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከአቅም በላይ ጭነት እንዲበዛባቸው ስለሚያደርግ፣ ጭነቱ እስኪስተካከል ድረስ ለተወሰነ ጊዜ የኃይል መቆራረጥ ሊከሰት ከመቻሉ ውጭ ኃይል በፈረቃ አይታደልም፤›› ብለዋል፡፡
ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ጭነት በሚበዛባቸው ሰዓታት ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን የኃይል መጨናነቅ ለማስተካከል በኮርፖሬሽኑ በኩል ተጨማሪ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እየተዘረጉ ስለሆነ፣ አሁን እየተነሱ ያሉት ቅሬታዎች ሊስተካከሉ እንደሚችሉም አቶ ምስክር ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ምስክር ገለጻ፣ በየጊዜው እያደገ በመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ምክንያት ኅብረተሰቡ የቁጠባ ባህልን ማዳበር ይኖርበታል፡፡
ይህንንም ለማድረግ ደንበኞች ኃይል ሳይቆራረጥባቸው አገልግሎት እንዲያገኙ በአብዛኛው ጭነት በማይበዛበት ሰዓት (ከሌሊቱ 6 ሰዓት እስከ ንጋቱ 2 ሰዓት) ድረስ ቢጠቀሙ የተሻለ ነው የሚልም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን ሐሳብ የሚያጣጥሉ በርካታ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የተለያዩ ግለሰቦች ኮርፖሬሽኑ ‹‹ስውር ፈረቃ›› አውጆብናል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህንንም የኃይል ቀውስ ሲሉ ይገልጹታል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ለመቀነስ ከውጭ በኪራይ መጥተው የነበሩት ጄኔሬተሮች አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በናፍታ የሚሠሩ ጄኔሬተሮችን በኪራይ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የኃይል እጥረቱን ክፍተት በመሙላት በደብረ ዘይትና በናዝሬት ከተሞች ኃይል እንዲያመነጩ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ ከአከራዩ ኩባንያ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሥራው ሊቋረጥ መቻሉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በናዝሬት ከተማ 47 የሚደርሱ በናፍታ የሚሠሩ ጄኔሬተሮችን በኪራይ ያቀረበው አግረኮን የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረት ለስድስት ወር አገልግሎት 56 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ለማግኘት ተስማምቶ ነበር፡፡
ክፍያው የተያዘው ለኩባንያው ሠራተኞች ለናፍታ ወጪና ለጄኔሬተሮች ወጪ ሲሆን፣ ጄኔሬተሮቹ በቀን የስድስት ትላልቅ ቦቴዎች ነዳጅ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ጄኔሬተሮቹ የሚጠቀሙት ነዳጅ በቀን ከአንድ ሚሊዮን ሊትር በላይ ይሆናል፡፡
በናዝሬት ተተክለው የነበሩት 47 ዲዝል ጄኔሬተሮች በአጠቃላይ 30 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጩ የነበረ ሲሆን፣ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን የኃይል እጥረት ክፍተት በመድፈን እገዛ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የተጠቀሱት ጄኔሬተሮች ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ሥራቸው በመቆሙ፣ በፊት ያመነጩት የነበረውን 30 ሜጋ ዋት ከቆቃ የኃይል ማመንጫ ከሚመነጨው ኃይል ጋር ተገናኝቶ፣ የኤሌክትሪክ ኃይሉ ወደ አዲስ አበባና ወደ ተለያዩ ከተሞች ይሠራጭ እንደነበር ታውቋል፡፡
እነዚህ ጄኔሬተሮች ሥራቸውን በማቆማቸው ምክንያት ተጨማሪ የኃይል እጥረት ችግር እየፈጠሩ ነው የሚሉት ምንጮች፣ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች እየታየ ያለው የኃይል መቆራረጥ እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠር ነው ይላሉ፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ከናዝሬት ከተነቀሉት ጄኔሬተሮች በተጨማሪ በደብረ ዘይት በተመሣሣይ ኪራይ 30 ሜጋ ዋት ሲያመነጩ የነበሩት ጄኔሬተሮች አገልግሎት እንዳቋረጡ ተነግሯል፡፡
በደብረ ዘይት የነበሩት ጄኔሬተሮች ከአንድ የግሪክ ኩባንያ በኪራይ የመጡ እንደሆነም ታውቋል፡፡ በናዝሬትና በደብረ ዘይት ከተሞች ያሉ ጄኔሬተሮች ሥራ ማቆማቸው ትክክል መሆኑን የገለጹት አቶ ምስክር፣ ጄኔሬተሮቹ ቀድሞም ቢሆን የተተከሉት የኃይል እጥረት በሚገጥምበት ሰዓት እጥረቱን ለመሸፈን ተብሎ እንጂ በቋሚነት የሚሠሩ አልነበሩም ብለዋል፡፡ የጄኔሬተሮቹ መቆም የፈጠረው ችግር አለመኖሩን አቶ ምስክር ቢገልጹም፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ግን የጄኔሬተሮቹ ሥራ ማቆም በኃይል አቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ይላሉ፡፡
ጄኔሬተሮቹ ሥራ ላይ በነበሩበት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ይወጣባቸው እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ምስክር፣ የጀኔሬተሮቹ ሥራ ማቆም ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሪ ማዳን ማስቻሉን ይገልጻሉ፡፡
የደብረ ዘይቱን ሳይጨምር ናዝሬት ላይ ተተክለው ሲሠሩ የነበሩት ጄኔሬተሮች ብቻ በቆዩበት የወራት ዕድሜ ከ56 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አስወጥተዋል ለሚለው ጥያቄ፣ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ አስወጥተዋል ወይም አላስወጣም ለማለት እንደሚቸገሩ፤ነገር ግን ብዙ ወጪ ይወጣባቸው እንደነበር አቶ ምስክር ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 2000 ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ይህ አቅም በደረሰበት አደጋ አገልግሎት መስጠት ያቋረጠውን የግልገል ጊቤ ሁለት 420 ሜጋ ዋት ያጠቃልላል፡፡ መንግሥት በቅርቡ በነደፈው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 8000 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት መዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል፡፡