አቶ ግርማ ዋቄ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊነታቸው ለቀቁ
በቃለየሱስ በቀለ | The Reporter
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ላለፉት ስድስት ዓመት ያገለገሉት አቶ ግርማ ዋቄ፣ ከዛሬ መስከረም 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው እንደለቀቁ ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ አቶ ግርማን የሚተኳቸው ምክትላቸው አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ግርማ ለተወሰነ ጊዜ ከአቶ ተወልደ ጋር አብረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ግርማ 65 ዓመታቸው ሲሆን፣ ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት የቦይንግ 787 ድሪም ላይነር አይሮፕላኖች መጥተው ማየት ይፈልጉ ነበር፡፡ አቶ ግርማ ከአገር ውጪ በመሆናቸው አስተያየታቸውን ማግኘት አልቻልንም፡፡ አቶ ግርማ እ.ኤ.አ በ2004 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ብስራት ንጋቱን የተኩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በገልፍ ኤርና ዲኤችኤል ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ አቶ ግርማ ከወጣትነታቸው ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የስራ ድርሻዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
አቶ ተወልደ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የገቡት እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም ሲሆን፣ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ አቶ ተወልደ የሕንድና ደቡብ ኤስያ እንዲሁም የጅዳ የክልል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካም የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል፡፡