በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ሒሳብ መኖር ተጠቆመ
(ሪፖርተር) — በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በኩል በሃዋላ፣ በሲፒኦ እና በቼክ ልውውጥ የተደረገባቸው ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ሰነዶች፣ ሳይወራረዱና ሳይታረቁ በዋናው መሥሪያ ቤት ሒሳብና የሒሳብ ማስታረቂያ መምሪያ (Account and Reconciliation Office) ተወዝፈው እንደሚገኙ የባንኩ ምንጮች አስታወቁ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች በተለይም የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንን የመሳሰሉ በርካታ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች፣ ሒሳባቸውን በወቅቱ የማያስታርቁ በመሆኑ ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በየቅርንጫፎቹ የሚደረጉት የሃዋላ፣ የስፒኦና የቼክ ዝውውር በወቅቱ አለመወራረዱና አለመታረቁ ባንኩ ራሱ ያለበትን የፋይናንስ ደረጃ በትክክል ይታወቃል ብሎ ለመናገር እንደማይቻል ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሒሳብ ቁጥር ‹‹EIBO›› የቅርንጫፍ ሒሳብ ተብሎ በቅርንጫፍ መካከል የሚደረጉ የሰነድ ልውውጦች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ሒሳቦች በየጊዜው ሒሳባቸው ተሠርቶ የማይወራረድና የማይታረቅ በመሆኑ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሰነድ ሳይወራረድ በእንጥልጥል ይገኛል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ 20 ሚሊዮን ብር በቅርንጫፋቸው ስም ተመዝግቦ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ገንዘብ የቅርንጫፋቸው ዕዳ ይሁን ወይም ለቅርንጫፋቸው የተከፈለ ገንዘብ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ያልቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባንኩ በየወሩ የሒሳብ መዝጋት ሥራ ይሥራ እንጂ በርካታ ሰነዶች ክፍያ ቢፈጸምባቸውም ሳይወራረዱ ተከማችተዋል፡፡
በተመሳሳይም በውጭ ምንዛሪ የሥራ ክፍል በርካታ የውጭ ምንዛሪ ሳይወራረድ ተከማችቶ ይገኛል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባንክ ባለሙያ እንደተናገሩት፣ ባንኩ በዓለም አቀፍ ኦዲተሮች ሒሳቡ እስካልተመረመረ ድረስ የፋይናንስ አቋሙን በትክክል መናገር አይቻልም፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመተግበር ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ በተለይ የገንዘብ ምንጮቹ የሆኑትን የፋይናንስ ተቋሞቹን በሚገባ ሊፈትሽ ይገባል ሲሉ አንድ ባለሙያ ገልጸዋል፡፡
መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (ቢፒአር) ግቡን መቷል ተብሎ በባንኩ የተለጠፈው ማስታወቂያ ከድርጊቱ ጋር አይሄድም ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀን ለማግኘት በተደጋጋሚ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ያደረግነው ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡