የስደቱ “የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ”

ስለ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሣ የክብር እንግዳነት ምርጫ የወሰደው ፖለቲካዊ አቋም

ዘውገ ፋንታ (የፌደሬሽኑ የቀድሞ ቦርድ አባል)

መግቢያ

በውጭ ያለው ማንኛውም የኢትዮጵያኖች ማህበራዊ ድርጅት፣ በሀገር ውስጥ እንዳለው ድርጅት ሁሉ በተዘዋዋሪ ወይም በቀጥታ በወያኔው መንግሥት ቁጥጥር ስር ካልሆነ በስተቀር ለመቀጠል እንዳይችል ውዝግብ እየተፈጠረ ስለሆነ ሕብረተሰቡ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን መረዳት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱት ጋዜጦች እንዲሁም ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉት የዜና ማሰራጫ መስመሮች መንግሥታዊ ድርጅት የሆነው የአሜሪካ ድምፅ ሳይቀር አምባገነኑ መሪ በአሜሪካ ምድር ቆሞ በድፍረትና በንቀት ያገዳቸው መሆኑን ለአሜሪካ ሕዝብ አሰምቷል። ኢትዮጵያኖች በየትኛውም ሀገርና ምድር የሕብረተሰብ ጉዳያቸውን ያለሁከትና ብጥብጥ ለማካሄድ ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ ሀብት ለወገኖቿ ጥፋት ስራ በየሀገሩ እየተረጨ መሆኑ ግልጽ ነው። ወያኔ መጨቆኛ ሴራ-ድሩን ለማስፋፋት ሲል የኢትዮጵያ ወገኖችን ለሌላ ጨቋኝ ዘረኞች አሳልፎ እየሰጠ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል።