የጸደንያ ማሪያም ንግስ በቫንኩቨር ደምቆ ተከበረ

ቫንኩቨር፣ ካናዳ — በየአመቱ የሚከበረው የጸደንያ ማሪያም ንግስ አቡነ ሉቃስ፣ አቡነ ዩሀንስ፣ አቡነ ሚካኤል (ከካልጋሪ)፣ ሁለቱ አባ ገ/ስላሴዎችና የቫንኩቨር ቅድስት ድንግል ማሪያም ደብር አባት መልአከ ጸሃይ አፍወርቅና አምስት መቶ የሚጠጉ ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ መከበሩ ተገለጸ።

ይሄው ከ1999 ጀምሮ በንግስ የሚከበረው በአል ላይ ከሲያትል፣ ከካልጋሪ፣ ከፖርትላንድና ከአሪዞና ድረስ ምእመናን በአውቶቡሶች፣ በመለስተኛ የሰው ማመላለሻዎችና በግል መኪናዎች በመጓዝ የአባቶችን ምክር ሲቀበሉ ውለዋል።

አቡነ ሉቃስ ለምእመናኑ በሰጡት የስብከት ትምህርት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ክብር ታላቅነት ከገለጹ በኋላ በሰው ልጅ ዘንድ እንኳን እናት ያላትን ክብር ለመግለጽ አጼ ቴዎድሮስ ወታደሮቻቸውን ለመቅጠር እናት እንዳላቸው ይጠይቁ እንደነበርና እናት የሌለውን ሰው ከወታደሮቻቸው መሀል ያሰናብቱ እንደነበር ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያትም እናት ያለው ሰው ለእናት ሀገሩ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለስ መሆኑን ስለተረዱ መሆኑን አስተምረዋል።

በመስከረም ወር ባሰለፍነው ቅዳሜ Sep,18/10 በተከበረው ንግስ ላይ የቫንኩቨርና የሲያትል ወጣትና ታዳጊ መዘምራን የምስጋና መዝሙሮን ሲያሰሙና እዚሁ ተወልደው ባደጉ ወጣቶችም ከድቁና አገልግሎት እስከ ከበሮ መምታት ተምረው ለበአሉ ታላቅ ድምቀት ሲሰጡት ተስተውሏል።

የቫንኩቨር ቅድስት ድንግል ማሪያም በቅርቡ ህይዎታቸው ባለፉት የኢትኦጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ታላቅ አባት አቡነ ዜና ቡራኬ ጸንታ የቆየች መሆኗ ይታወቃል።