ውይይት፣ «ቡና አዕምሮ ንብረት ባለቤትነት፥ ባህልና ልማት!»

በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የፍሬዴሪክ ፓርዲ የጥናት ማዕከል ለህትመት የበቃውና የኢትዮጵያን ምርጥ ቡና ጅምር ጥረት በምሳሌነት የተመለከተው ይህ ጥናት፥ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ፥ እስካሁን እምብዛም ተጠቃሚ ያላደረጋቸውን አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ደሃ አገሮችንም፤ እንደ ግዙፉ አትራፊ ኩባንያዎች ሁሉ፥ የትሩፋቱ ተቋዳሽ ሊያደርግ የሚያስችል አቅም እንደሚያጎናፅፍ ያመላክታል።

አንድ የምርት ውጤት ቁሳዊ ይዞታው ከሚያስገኛቸው ቀጥተኛ ጠቀሜታዎች ባሻገር፤ ከምርቱን ልዩ መሆን፥ ምንነት፥ ሥምና ዝናው ወይም ዕውቅናው፤ እንዲሁም ምርቱ የፈለቀበትን ባህል የመሳሰሉ ባህሪያቱ የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ዋነኞቹ ከአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዕሴቶች ናቸው።

«ቡና፥ ባህልና የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት፤» ዙሪያ በሚያጠነጥነው ተከታታይ ውይይት፤ የመጀመሪያው ክፍል የታሪክ አጥኚዋ ዶ/ር ሄራን ሰረቀብርሃን በጥናታቸውን የመረመሩት የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ በሚታሰቡ ጠቀሜታዎችና ተዛማች ነጥቦች እንመለከታለን። በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ደሃውን የቡና አምራች ገበሬ ከምርቱ ፍሬ ተጋሪነት አስመልክቶ ለንባብ በሚያበቋቸው ፅሁፎች የሚታወቁትን በዚህ በዩናይትድ ስቴትስ፥ የሲያትል ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወንድ ወሰን መዝለቂያን ጨምሮ የተካሄደ ውይይት አጠር ያለ ቀዳሚ ክፍል ያዳምጡ።