የኢትዮጵያውን ሥደተኞች ሞት በሳውዲ አረቢያ
እስካሁን አስራ-አንዱ ለሞት፥ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሌሎችን ለበሽታ እና የተቀሩትን በሙሉ ለስቃይ የዳረገዉ ችግር የሚወገድበት ብልሐት አሁንም ግልፅ አይደለም።
የስዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች ወደ ሐገራቸዉ ለመመለስ ካሰሯቸዉ ኢትዮጵያዉያን መካካል ጂዘን ዉስጥ አምስቱ ከነሱ በፊት ጂዳ ዉስጥ ደግሞ ሌሎች ስድስት መሞታቸዉ በትናንቱ ዜናችንና ከዚያም በፊት ተዘግቧል።ምክንያቱ የእስር ቤቱ ሙቀትና መጨናነቅ ነዉ።የሰዎቹ መሞት ከመሰማቱ በፊት ስደተኞቹ የታሠሩበት ቦታ ለሕይወታቸዉ አደገኛ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ዘግበንም ነበር።ይሁንና እስካሁን አስራ-አንዱ ለሞት፥ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሌሎችን ለበሽታ እና የተቀሩትን በሙሉ ለስቃይ የዳረገዉ ችግር የሚወገድበት ብልሐት አሁንም ግልፅ አይደለም።የጂዳዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክ ያነጋገራቸዉ በጂዳ የኢትዮጵያ ቆስልና የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ተጠሪዎች ግን ጉዳዩን እየተከታተልን ነዉ ይላሉ።