የተዘረፈ የሀገር ሃብት መደበቂያ ዋሻ ወይስ ባንክ?

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጀመርያ በቱኒዝያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ለሃያ ሶስት ዓመታት በህዝብ ጫንቃ ላይ ተነሰራፍቶ የሀገሪቱን ሀብት ሲመዘብር የኖረውን መሪ ቤን አሊን ከሀገር እንዲወጣ አድርጎታል: ከሰሞኑም የግብጽ ህዝብ ከአስራ ስምንት ቀናት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ ለሰላሳ ዓመታት ግብጽን በብረት ጡጫ ሲገዛ ከነበረው ሆስኒ ሙባረክ የግፍ አመራር ራሱን ነጻ አውጥቷል:: ይህም የህዝብ ብሶትና በቃኝ ባይነት ወደ አልጄርያ፣ የመን፣ ጆርዳን፣ ሶርያ፣ ሊቢያና ኢራን እየተዛመተ መሆኑን የዜና አውታሮች እየዘገቡ ነው::
ታድያ ለአምባገነን መሪዎች ራስምታት የሆነባቸው ትልቁ ጉዳይ ከስልጣን መውረዱ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሀብት ዕገዳ ነው::

ስዊትዘርላድ በአለም የምትታወቅበት ትልቁ የንግድ ተቋም ባንኮቿ ሲሆኑ እነዚሁ ባንኮች አያሌ አምባገነን መሪዎች ከህዝባቸው የሰረቁትን ገንዘብ ማሸሻና የሌባ አደራ አስቀማጭ ተቋሞች ሆነው ቆይተዋል:: በቅርቡ ግን ከፌብሩአሪ 1_ 2011 ጀምሮ “የተዘረፈ የህዝብ ገንዘብ መደበቂያ ዋሻ አንሆንም” በማለት የሀገሪቱ ፓርላማ መክሮበት ህግ አርቅቆና አጽድቆ በስዊትዘርላንድ ስራ ላይ ውሏል::

ከድሃው ከተራበው ከተጎሳቆለውና እንዳይናገር አፉ ተሸብቦ መብቱ ከሚረገጠው ህዝብ የተዘረፈውን ገንዘብ በተለያየ የዓለም ባንኮች የሰወሩት አምባገነን መሪዎች ከህዝብ ጉሮሮ ነጥቀው ለክፉ ቀናችን ብለው ያሸሹት ገንዘብ መታገዱ ለሌሎች ስልጣንን የሙጥኝ ብለው ህዝባቸውን ለሚያሰቃዩና ለሚዘርፉ ያስደነገጣቸውና ቆም ብለው ድርጊቶቻቻውን እንዲመረምሩ ያስገደዳቸው ጉዳይ ሆኖአል:: ችግሩ ያለው ግን አምባገነን መሪዎች ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ ራሳቸውን እየሾሙ በየምርጫው እያጭበረበሩ ጥቅም የሚያስጠብቁላቸውን የምዕራብ አገሮች ጌቶቻቸው በሚሰጧቸው የእድሜ ማራዘሚያ ገንዘብና ድጋፍ ተንሰራፍተው መቀመጣቸው ነው:: እነዚሁ የሌባ አይነደረቆች ታድያ የህዝብን ተቃውሞ እንደሀገር ተቃውሞ ፣ ተቃዋሚዎቻቸውን እንደ አሸባሪ፣ እነርሱም ከወረዱ ሀገሪቱ በአሸባሪዎች እጅ እንደምትወድቅ ወይም ህዝብ ወደ ዕርስ በርስ እልቂት እንደሚያመራ እያስፈራሩ ሀገሪቱ የምትኖረው እነርሱ ሲኖሩ ብቻ እንደሆነ አድርገው ያለእፍረት ራሳቸውን አሳምነው መኖራቸው ነው:: ለህዝብና ለአለም ይህንኑ ወሸት እውነት ብለው ለማሳወቅ መሞከራቸው ለህዝብ ያላቸውን ንቀት ነው የሚያመላክተው:: ካለነርሱም ያ ህዝብ መሪ እንደማይኖረው የነርሱን ጀግንነት እውቀትና ብቃት ብቻ በሚያራግቡ የስርአቱ ጥቅም ተካፋዮች የሚያቀነቅኑትን ዜማ በተመስጦ እየሰሙ አምነው ለአቀንቃኞችም ወረታ ከዘረፉት እየወረወሩላቸው በሌብነት የሚከሳቸውንም ለማጥፋት የሚሞክሩ ሌቦችና ህሊና ቢሶች ናቸው::

አምባገነን መሪዎች ላይ በጋራ የሚታየው ባህርይ ተቃዋሚን ማጥፋት፣ ያለ ፍርድ ማሰር ፣ሚዲያውን ማነቅና መንግስት በሚቆጣጠረው መለፈፊያ ሁሉ የራስን ዝናና የውሸት እድገት ቁጥሮች ማስተላለፊያ ማድረግ ህዝብን ማደንቆርና ማሳሳት እርስ በርሱ እንዳይተማመን በጥርጣሬ አይን እንዲተያይ ማድረግ ነው:: በተራበውና በተጎዳው ህዝብ ስም በልመና ወይ በእርዳታ የመጣውን ገንዘብ ባልተገራ ራሥ መውደድና ስግብግብነት ገንዘብ ሰርቆ ውጭ ባንኮች ውስጥ ማሸሽ ለምእራባውያን ለጋሽ ሀገሮች እይታ ደግሞ የይስሙላ ምርጫ ትያትር መስራትና ዴሞክራሲ እኛም ህዝባችንም አጥብቀን የምንፈልገው ነው ብሎ መዋሸት የብዙዎች በሀገር መሪነት ስም ራሳቸውን ያስቀመጡ በየሀገሩ ያሉ የወሮበላ መሪዎች ተግባር ነው::

በምኒሊክ ቤተመንግስት ራሱን እስረኛ ያደረገውና ባመታት አንዴም አደባባይ ቢታይ ጥይት ከማይበሳው መስታወት ከለላ ስር ተደብቆ ስለሀገሪቱ የሁለት አሃዝ እመርታዊ እድገት የሚዋሸው መለስ ዜናዊም ከዘራፊ መሪዎች ተርታ የተመደበ ከተራበ ጉሮሮ ነጥቆ የውጭ ባንክ አካውንቱን እያደለበ ያለ አምባገነን ነው:: ይህ የሚመራውን ሀገር የሚጠላ ሰው ጤንነቱ ታውኮአል:: የሚወስዳቸውንም መድሃኒቶች በጫት እያወራረደ ሌትና ቀኑ ረዝሞበት ጸሃይ ሳያየው እየነጣ እየገረጣ ሁለት የፊት ቀለም እያወጣ መሄዱን ያስተዋሉ ብዙዎች ናቸው:: መለስ ዜናዊ የሚመራውን ህዝብና ሀገር በንቀትና በጥላቻ ቁልቁል የሚያይ ባለግዜ አምባገነን ከመሆኑም በላይ በተራበው ህዝብ ስም የሚደረገውን እርዳታ ከረሃብተኛው ጉሮሮ እየነጠቀ የሚያሸሸው የገንዘብ መጠን ከሌሎቹ አምባገነን መሪዎች የማይተናነስ ነው:: q
ቅጥ ካጣው መስገብገቡ የተነሳ ከውጭ በተለያየ ርእስ የሚገባውን ገንዘብ መዝረፍ አልበቃ ብሎት የሀገሪቱን መሬቶች ለውጭ ሀብታሞች በረጅም አመታት ሊዝ እየሸጠ ያለ የወሮበላ ቁንጮ ነው:: በቅርቡ አስር ሺህ ቶን ቡና የደረሰበት ባለመታወቁ የሰረቁትም የራሱ የ ጉና ጅቦች ስለሆኑ መለስ ዜናዊ እሱን ተውት ከእንግዲህ ግን ቢሰረቅ ሌባውን እጁን እንቆርጣለን የሚልና ህዝብ ላይ የሚያሾፍ የሌባ መሪ ነው:: አዜብ መስፍን በአውሮፓ ገበያ ላይ ታይታ ከባሏ ሂሳብ ወይ ከአስር ሺህው ቶን ቡና ሽያጭ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ በልብስና በውድ ጌጦች መሸጫዎች ስትመነዝር ስታባክንና ስትረጨው የታዘበው በአውሮፓ የሚገኝ ኤቢሲ ኢንተርናሲዮናል የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል::
የናይጄሪያው ሳኒ አባቻ ከሃገሪቱ ሰርቆ ያሸሸው 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሌብነቱ ታሪክ አስወቀሰው እንጂ ከልብ ድካም ጋር ከተያያዘው ሞቱና ከተቆረጠለት እድሜ ያ ሁሉ ገንዘብ አንዲትም ስዓት ሊጨምርለት አልቻለም::

በሄግ የአለም ፍርድ ቤት ጉዳዩ እየታየ ያለው የቀድሞው የላይቤሪያ መሪ ቻርልስ ቴይለር በዝርፍያ የሰበሰበውን የደም እንቁ ገንዘብ እንዲታገድና ወደ ላይቤሪያ እንዲመለስ ከሚጥሩት ውስጥ የስዊትዘርላንድ መንግስት ግምባር ቀደም ሀገር መሆኑን በአምባገነን መሪዎች የተሰረቀ ሀብትና ንብረት ወደየሀገሮቻቸው እንዲመለሱ ባለም አቀፍ ህጋዊ አማካሪ ሆነው የሚሰሩት ማርክ ቪላሲክ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በላኩት ጽሁፍ አረጋግጠዋል::

የግብጹ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ በለንደን በአሜሪካ በፓሪስ በስዊትዘርላንድ የተለያዩ ባንኮች ያሸሸው የግብጽ ህዝብ ገንዘብ እንዳለ የሚነገር ሲሆን ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የተሰኘው በታዳጊ ሀገሮች የሚካሄደውን ሙስናና በሀገር ሀብት ዝርፊያ ላይ የተሰማሩትን የሚከታተል ድርጅት ዘገባ እንደሚያመለክተው ከ2000 እስከ 2008 ዓም ብቻ 57 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ወደተለያዩ የምእራቡ ዓለም ባንኮች በአደራ መቀመጡን ይገልጻል::

የሙባረክ ንብረቱና የተንቀሳቃሽ ገንዘቡ ልክ ከቢል ጌትስ ወይም ከዋረን በፌት የሚበልጥ ተብሎ የተነገረለት ሲሆን በእንግሊዝ በአሜሪካና በስዊትዘርላንድ ባንኮች ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር አሽሽቷል የሚሉ አያሌ ዘገባዎች ይገኛሉ:: የዚሁ ንብረትና ገንዘብ ጉዳይም ሳይሆን አይቀርም ሆስኒ ሙባረክ ስልጣን ላይ ተንፈራጦ እኔ ከወረድኩ ግብጽ ወደ አስከፊ ትርምስ ውስጥ ትገባለች ብሎ ሲያስፈራራ የነበረው ወይም እስራኤልን የሚጠሉት የእስላም ወንድማማቾች ፓርቲ ስልጣን ይወጡና እስራኤል ወዮላት በማለት አሜሪካኖችንን ሲያስጨንቅ የከረመው:: ያለውን ብር መጠን ያወቁና ከግብጽ የተሰረቀውን ገንዘብ ያዩ እንግሊዛውያን ምራቃቸውን እየዋጡ ያንን ገንዘብ ለንደን እየመነዘረ እንዲኖር ከመመኘት ይመስላል ከሰሞኑ ከወደ ለንደን የሚሰማው ዜና የሙባረክ ባለቤት ሱዛን ሙባረክ በግማሿ የዌልሽ ዝርያ ስለአላት፣ የሻርማ አልሼክ ኑሮውና ደህንነቱ ያሳሰባቸው እንደሆነ፣ የለንደን ኑሮው ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ ሊሆን እንደሚችል ወደ ለንደን መጥቶ እንዲኖር እየገፋፉት እንደሚገኙ ተጽፎ ለንባብ በቅቷል::

ከየሀገራት መሪዎች በህገወጥ መንገድ የተዘረፉ ገንዘብና ንብረቶች እንዲታገዱና ህጋዊ ባለቤቶቻቸው ለሆኑ ሀገሮች እንዲመለሱ በሚያዘው አዲሱ የስዊትዘርላንድ ህግ መሰረት በቅርቡ የቱኒዚያው የቤንአሊ የግብጹ የሆስኒ ሙባረክ የአይቮሪኮስቱ ባግቦና የሃይቲው ዱቫሌየር ገንዘብና ንብረቶች ላይ ዕገዳ መጣሉ ሌሎችን ስልጣን ላይ ያሉትን ሌቦች አስበርግጎአል:: በቅርብም የፊሊፒንሱ የቀድሞ መሪ ፈርዲናንድ ማርቆስ ከዘረፈውና ስዊስ ባንክ ካስቀመጠው ላይ 684 ሚሊዮን ዶላር የቀድሞ የናይጄሪያ መሪ ሳኒ አባቻ በአምስት አመት የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ቆይታ ከሰረቀው ወደ 4 ቢሊዮን ከሚጠጋ ገንዘብ ላይ 700 ሚሊዮን ዶላር ከፔሩው ሞንቴሲኖስ 92 ሚሊዮን ዶላር ከሜክሲኮው ሳሊናስ 74 ሚሊዮን ዶላር ወደየሀገሮቻቸው የተመለሰ ገንዘብ መሆኑን የሰዊዘርላንድ ፌዴራል ካውንስልን ጠቅሶ ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር አሴት ሪከቨሪ የተባለው ድርጅት አስታውቋል::

ይህ ከድሃ ህዝብ እየተነጠቀ በአምባገነኖች ያልተገራ ስግብግብነት ወደውጭ ባንኮች የሚሸሽ ገንዘብ ማብቂያው ላይ ዓለም እየተነጋገረበት ያለ በስዊትዘርላንድ የተጀመረው እገዳ ወደሌሎችም ሀገሮች እንደሚስፋፋ ተስፋ ያለው ጅምር ሆኗል:: የተሰረቀውን ገንዘብ ወደየሀገሮች የመመለሱ ሁኔታ የተዘረፈውን ሲያስደስት ዘራፊዎችን እያሳሰበ መጥቷል::

ቸር ይግጠመን
ዮሐንስ ተመስገን::