“ሶስተኛው ሪፐብሊክ”፡ የቶሮንቶ ስብሰባና የኢትዮጵያ መጪው ዘመን ክፍል አንድ በተከሌ አበበ
ቦታው ኤድመንተን ውስጥ ነው። ስብሰባው የኦጋዴን ማህበረሰብ ስብሰባ። ተናጋሪው ኦባንግ ሜቶ። የምስራቅ ጫፍና የምእራብ ጫፍ ወግ። ሰሜንና ማእከሉ መነጋገርና መግባባት በተሳናቸው ግዜ፡ የምእራቡ ኢትዮጵያዊ የምስራቁን ኢትዮጵያ ሲያግባባውና ሲሸመግለው። “እኛ ኢትዮጵያዊያን” ብሎ ጀመረ ኦባንግ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ብሎ ሲጨርስ፡ በመካከል ግን አንዲት የኦጋዴን ሴት ተነሳችና “who the hell are you to tell me that I am an Ethiopian? I am not Ethiopian. You have to apologize for calling me an Ethiopian” አለችው። ወረደችበት። ወደ አራት መቶ የሚጠጉ የኦጋዴን ተወላጆችና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አዳራሹን ሞልተውታል። ኦባንግ አልደነገጠም። እንዲህ ያለውን ጥያቄና ፍጥጫ ለምዶታል።
ይሄ ወግ ማእከል የሚያደርገው የቶሮንቶውን ስብሰባ ነው። ነገር ግን ቶሮንቶ ከመድረሳችን በፊት ኤድመንተንን፡ ጎዴን፡ ነጌሌን፡ ጅማን፡ ዲሲን፡ ቢቸናን፡ ጋይንትን ማሰስ ሊኖርብን ይችላል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም፡ ወዳጄ ዳንኤል ጥላሁን እንደሚለው፡ “ሶስተኛ ሪፐብሊክ ያስፈልገናል፤” ሶስተኛውን ሪፐብሊክ እንዴት ብናዋቅረው መልካም ነው የሚለው ሀሳብ ላይ አንድ ሀሳብ ለማከል ነው። አደንኛው ሪፐብሊክ አልሰራም።የደርጉ መሆኑ ነው። 1974። ሁለተኛውም እየሰራ አይደለም። የኢህአዴጉ። 1991። ሶስተኛው ሪፐብሊክ አንድ ቀን ይመጣል። እናመጣዋለን። ሲመጣ ግን ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ ተብሎ እንደተጻፈው መዘጋጀት አለብን። ምንድነው የምንፈልገው? እነሆ የሶስተኛው ሪፐብሊክ ጥንስስ በቶሮንቶ ተጠነሰሰ ባልልም፡ በዚህ የግንቦት መጀመሪያ ሳምንት በቶሮንቶ ከኦጋዴን፡ ከአፋር፡ ከጋምቤላ፡ ከጅማና፡ ከጎንደር የተነሱት ነቢያት ንግግር ያደረጉበት ስብሰባ ስላጣነውና ስለሚያስፈልገን ነገር ትንሽ ይላል።
ወደ ኤድመንተን ልመልሳችሁ፡ ወደኦባንግና ወደዚአች የኦጋዴን ሴት ፍጥጫ። የኔ እህት፡ “እስኪ ኢትዮጵያዊ ላለመሆንሽ ሶስት ምክንያቶች ስጪኝ” አላት። “ሰላሳ እሰጥሀለሁ” አለችው። “የለም የለም ሶስት ስጪኝና እኔ ሰላሳ ግዜ ይቅርታ እጠይቅሻለሁ” አላት ኦባንግ መልሶ። “አንደኛ፡ የኢትዮጵያን ቋንቋ አልናገርም። (አማርኛ መሆኑ ነው) ሁለተኛ የኢትዮጵያዊያን ሀይማኖት የለኝም (ኦርቶዶክስ ክርስትና መሆኑ ነው)። ሶስተኛ መልኬም ኢትዮጵያዊ አይመስልም።” “እሺ አዚያ ጋር አቁሚ።” አለ ኦባንግ። “መልካም፡ እንግዲያውስ የሚከተሉትንም ጥያቄዎች መልሺልኝና ከዚያ በኋላ ይቅርታ እጠይቅሻለሁ።” ሄይ ኦባንግ ምንም ወሬ አታብዛ፡ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብያለሁ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ነሽ ስላልከን ይቅርታ መጠየቅ አለብህ የምትል ይመስለኛል በሆዷ። ኦባንግ በትእግስትና በርጋታ፡ ደግሞም በሶቅራጥስ መንገድ ማስረዳቱን ቀጠለ።
“እዚህ አገር ከመጣሽ ስንት አመት ሆነሽ?” አላት። አስራ አምስት አካባቢ፡ አለችው። “እዚህ አገር ከመጣሽ ወደሌላ አገር ሄደሽ ታውቂያለሽ?” አዎ። “የት የት?” ሲላት ምን ይሰራልሀል? አለችዉ። “መልሺልኝ እባክሽን” ስለአላህ አላት ኦባንግ። እንግሊዝ፡ ስዊድን፡ ኔዘርላንድስ፡ … በቃ በቃ። በምን ፓስፖርት ሄድሽ? በካናዳ ፓስፖርት። አሁን ማርሽ ወደ እንግሊዘኛ ልቀይር፡ “Are you a Canadian?” “yes I am a Canadian” and “Are you proud to be a Canadian?” “yes I am proud to be a Canadian”። good አለ ኦባንግ። “Do you look like a Canadian?” ተፋጠጡ። ከዚአ በኋላ ኦባንግ አንበለበለው።
ካናዳዊ ያሰኘን መልካችን አይደለም። ካናዳዊም ያሰኘን ቋንቋችን አይደለም።፡ካናዳዊም ያሰኘን ሀይማኖታችን አይደለም። መነጋገር መቻላችን ነው። የግድ መግባባትም የለብንም። መነጋገር ግን ያስፈልገናል። አናዳችን ስለአንዳችን መመስከር አለብን። አንዳችን አንዳችንን መክሰስ ሳይሆን፡ መግባባትና መነጋገር አለብን። የዚያን ግዜ አንዳችን ያንዳችን ቤተሰብ፡ ያንዳችን አካል እንደሆንን ይሰማናል። ኢትዮጵያዊማ ነን። በኢትዮጵያዊነታችን ያጣነው ነገር ስላለ ብቻ ኢትዮጵያዊነታችን ይሰረዛል ማለት አይደለም። እስኪ እንነጋገር አለ። በቶሮንቶም ኤድመንተን ካቆመበት ቀጠለ።
ኦባንግ ያስደስተኛል። ኦባንግ ያረካኛል። ከዚህ በፊትም ብያለሁ የኛን ተልእኮ ለብቻው ተሸክሞ ከሰሜን ደቡብ ከምስራቅ ምእራብ ሲንከራተት፡ ከጋምቤላ ኦጋዴን፡ ከጎንደር ቦረና ሲንከራተት፡ ከግንቦት ሰባት ኦነግ፡ ከኦብነግ፡ አንድነት፡ ሲቀባበሉት ያሳዝነኛል፡ ምስኪን። ግን ደግሞ ያረካኛል። እኔ ብለው የማያምርብኝን እሱ ሲለው ስሰማ፡ አንጀቴ ቅቤ መጠጣት ብቻ ሳይሆን፡ ለካስ ስለኔ ሆነው የሚናገሩ ሌሎችም አሉ እንድል ያደርገኛል። ያኔ ብቻ አይደለም፡ ትናንትም፡ ሜይ 7 ቶሮንቶ በድጋሜ ስለኔ ተናገረ። ኦባንግ የአንድነት ሰባኪ ነው። ግን ደግሞ በአንድነት ስም በደል አልተፈጸም ብሎም ሽምጥጥ አድርጎ የሚክድ አክራሪ አማራም አይደለም። ስለዚህ ከሁለቱም ወገን አድማጭ አለው። ከተገፉትም፡ በገፊነት ከሚከሰሱትም። ከራሱም ከሌሎችም ታሪክ እያጣቀሰ በደል እንነበረ፡ እንዳለ፡ ወፊትም ሊኖር እንደሚችል፡ በደል ብቻውን ግን የሆነውን (ነ ይጠብቃል) እንደማይንድ፡ ይልቅስ በደሉ ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ እንድንቀይስ እንደሚያስገደደን ይናገራል። ባለፈው ሳምንት በቶሮንቶ የሆነው ያ ነው።
ባለፈው የግንቦት የመጀመሪያ ቅዳሜ፡ ኦባንግ ባንድራዋን እያየ፡ ይሄንን ባንድራ እንደአንድነትና እንደ ነጻነት የሚያዩዋት አሉ። ይሄንን ባንድራ ደግሞ እንደ ባርነትና እንደ ጭቆና ምልክት የሚመለከቱት አሉ። ባንድራው መዳኛም መሞቻም አይደለም። መዳኛችንም መሞቻችንም ከባንድራው ጀርባ የምንገነባው ስርአት ነው። ችግራችን የስርአት ነው። የዚህ ብሄር ወይንም የዚያ ብሄር አይደለም። በዚህ ባንድራ ስር መኖራችን ነው ለጭቆና የዳረገንና መገንጠል አለብን የምትሉት ተሳስታችኋል። ይሄ ባንድራ ስር ጭቆና አልነበረም የምትሉም ክፉኛ ተሳስታችኋል። ጭቆና ነበር። ጭቆና አሁንም አለ። የእኩልነት ስርአት ካልገነባንም ጭቆናው ይቀጥላል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ግን መነጋገር ነው። የተጨቆነ ካለ፡ ውሸትህን ነው አንበለው። ምክንያቱም እውነቱን ነውና። በኔም ደርሷል። እሱን ይዘን መከራከር ለማንም አይበጅም እንጂ።
የዛሬ ዘጠኝ አመት አካባቢ፡ ነው፤ በ2002። ኦባንግ አዲስ አበባ ነበር። አንድ ካልጋሪ የሚኖር አብሮ አደግ የጋምቤላ ጓደኛው ይደውልና፡ “እባክህ እናቴ በጠና ስለታመመች፡ አዲስ አበባ ወስደህ አሳክምልኝ” ይለዋል። የጓደኛው እናት አዲስ አበባ መጥተው ሆስፒታል ሲሄዱ፤ ህክምናቸው ለ15 ቀን ተቀጠረ። ኦባንግ ወደካናዳ መመለስ ስለነበረበት፡ የካልጋሪ ጓደኛው ባዘዘው መሰረት እናቱን አዲስ አበባ ቤት ተከራይቶ ሊያስቀምጣቸው ተስማሙ። ኦባንግ ደላላ ጋር ሄደ። ቤት ተገኘላቸው። የሁለት ወር አካባቢ ኪራይ ከፈለ። በነጋታው የቤት እቃዎችን ገዝተው ጭነው ሲመጡ፡ ነጠላ ነገር የለበሱ የቤቱ ባለቤት ሴት “እኛን ሲመለከቱን የለም የለም ለነዚህማ ቤት አላከራይም ብለው በመጸየፍና በመኮሳተር እምቢ አሉን።፡እማማ ምንድነው ችግሩ ስላቸው፡ አላከራይም እንደውም ለናንተ ከማከራይ፡ ቤቴ ሳይከራይ ባዶውን ቢቀመጥ ይሻላል፤ አሉት።” ኦባንግ አዘነ። መንገድ ዳር ቁጭ ብዬ ተከዝኩኝ። የጫንነውን እቃ የምናስቀምጥበት አጥተን ተንከራተትን። ይሄ ሁሉ የሆነው ኢህአዴግ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ብሄሮች ነጻ ባወጣ በአስራ አንደኛው አመት መሆኑ ነው።
ከጓደኛው ጋር ተደዋወሉ። የሆነውን ነገረው። ልጁ አማረረ። “እንደው ዝም ብለን ነው እኮ አገር አለን፡ ኢትዮጵያዊ ነን የምንለው። በዚህ መልኩ ምኑን አገራችን ሆነች?” ሲል ክፉኛ ወቀሰ። ኦባንግ አረጋጋው። እዚህ ጋር ነው ኦባንግ የሚመቸኝ። ሌሎች የተገፉ የኦጋዴን፡ የኦሮሞና የአፋር ሰዎችንም እንደዚያ ነው ቶሮንቶ ላይ ሲመክራቸው የነበረው። ችግር መኖሩን አይክድም። የችግሩ ምንጭ ግን ለኦባንግ የጤናማ መንግስት፡ ፍትሀዊ ስርአት አለመኖር ነው። ለምሳሌ ካናዳ ቢሆን መልክን ወይንም ዘርን ወይንም ጾታን መሰረት አድርጎ አገልግሎት መከልከል፡ በጠቅላላው እንዲያ ያለው አሰራር በህግ የተከለከለ ነውና ልከስ፡ ፍርድ ቤት ሄጄ መፍትሄ ላገኝ እችላለሁ። ኢትዮጵያም እኚያ ሴት ክፉ ሆነው ሳይሆን፡ እንደዚያ ያውን አሰራር የምንቀርፍበት ስርአት ስላልገነባን ነው ለችግር የተጋለጥነው። ስለዚህ ችግሩ የስርአት ነው። በመገንጠል አይፈታም። ችግሩ የኚያ ሴትና የኦባንግ ብቻ አይደለም። ችግሩ፡ አበበ በለው እንዳለው፡ የሁላችንም ነው። እንደዉም የኦባንግም የድርጅቱም ዋንኛ መልእክት “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ነጻ አይወጣም ነው።” የሚለው። የኢትዮጵያ ችግር አማራ፡ ትግሬ፡ ኦሮሞ፡ አኝዋክ የመሆን ሳይሆን የዜግነት ችግር ነው ባይ ነው። ዜግነት ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያዊ ማለትስ? እያለ ይቀጥላል። እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ አለብን ነው የሚለው ኦባንግ።
ጃዋርም ይሄንን ይጋራል። ጃዋር የገባው የገጠር ልጅ ነው። እሱ ራሱ ነው፡ “እኔ የገጠር ልጅ ነኝ” ያለው። የዛሬ አስራ ምናምን አመት፡ ጃዋር ከገጠር እየመጣ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መሰለኝ፡ ትምህርቱን ይማራል። ቤት ተከራይቶ። አከራዩ ደግ ሴት ነች። ሲበዛ ደግ። ግን አማራ ነገር ሳትሆን አትቀርም። የከተማ ሰው። አንድ ቀን ማታ ጃዋር፡ እጅግ ከመሸ፡ ዝናብ እየደበደበው ወደቤት ይመጣል። ቤት አከራዩ፡ ተቀበለችው። እሳት አነደደችለት። ምግብ አቀረበችለት። እያጎረሰችው፡ ጋቢ እየደረበችለት፡ አንድ ህይወቱንና አስተሳሰቡን የቀየረው ነገር ጣል አደረገች። እንዲህ አለችው …
(አሁን ወደ ዲሲ እየተጓዝኩ ነው። ቅዳሜ ሜይ 14፡ 2011 በኔትቪቲ ቤ/ክርስቲያን ለሚከበረው የኢትዮጵያዊነት እሴትና ውርስ አስጠባቂ ማህበር የምስረታና የመክፈቻ ዝግጅት) ስለዚህ ጽሁፉ ስመለስ ይቀጥላል። ተከታተሉኝ። እስከዚአው ግን
አስተያየት ካላችሁ፡ በ[email protected] ላኩ።