ሁለቱ ሲኖዶሶች በተአምረ ማርያም ምክንያት አልተጣሉም:አይጣሉምም::ለተሃድሶ መልስ -አባ ወልደ ትንሣዔ ጫኔ
መጀመሪያ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ከእስጢፋኖስ ጋር ያጣላቸው ብዙ ነገሮች አሉ:: እስጢፋኖስ ለሥዕል; ለመስቀል : ለንጉሥ አልሰግድም አለ:: ንጉሡም የአምላክ እናት; የመስቀል እና የራሱም ክብር ስለተነካ ቀጥቶታል:: ቅ/ጴጥሮስ “ለገሮች ብቻ ሳይሆን ለጠማማች ገዢዎች በፍርሃት ሁናችሁ ተገዙ”(1 ጴጥ 2:18) የሚለዉን ንጉሡ በደንብ ስለሚያዉቀው ለክፉ ንጉሥ ሳይቀር ተገዙ እያለ ቅ/ጴጥሮስ በመንግሥቴ ይህንን አይነት ትምህርት አታስተምር አለው :: እምቢ! አለ:: እስጢፋኖስ ተቀጣ::ንጉሡ ተቆጥቶ ደቂቀ እስጢፋኖስን በዘመኑ ሲቀጣቸው ኑሯል::
ተሃድሶዎች መጽሓፍ ቅዱስን አትቀበሉም እንጂ ተአምረ ማርያም ከመጽሓፍ ቅዱስ አይጋጭም እናንተ ካላጋጫችሁት በስተቀር::
- በመጀመሪያ ተአምረ ማርያም የተጻፈው በአጼ ዘራዓ ያዕቆብ ነው የሚል ምንም መረጃ የለም:: እስቲ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ጻፈ የሚል አምጡ:: ተአምረ ማርያም እንደሚለው በቅ/ደቅስዮስ እንደተጻፈ ይነግረናል:: በንጉሥ ዘመን ከአረብኛ ወደ ግዕዝ ተተረጎመ ይላል እንጂ ንጉሡ ጻፈው አይልም::
- ተአምረ ማርያም የሚለው ፍጥረት ሁሉ ለአዳም ተፈጠረ ይለናል:: ለእመቤታችን ተፈጠረ ማለት ምኑ ያጠራጥራል? እሷ እኮ አዳም የአዳም ልጅ ነች::( በዘፍ1:26-30) እንድምናነበው”እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ ለአዳም ፈጥሮ ግዛቸው ለአንተ ነው የፈጠርኩት:እያለ አይ ፍጥረት ለአዳም; ለእመቤታችን አልተፈጠረም ካላችሁ ከእግዚአብሔር ጋር እየተጣላችሁ ነው:: ከአዳም እና ሔዋን እመቤታችን ትበልጣለች:: ይህ የእግዚአብሔር ምስጢር የገባው ፍጥረት ሁሉ ሰለ እመቤታችን ተፈጠረ (ሰለ አዳም ተፈጠረ አለ) ፍጹም መጽሓፍ ቅዱሳዊ ነው:: ሌላው የዚህ ምስጢር በኋለኛው ዘመን ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ተዋህዶ እንደሚያድን የእግዚአብሔር ዕቅድ ነበር ለማለት ነው:: (ሉቃ1:48) እመቤታችን “ትውልድ(ፍጥረት) ሁሉ ያመሰግነኛል” ብላለች::ይህ በወንጌል የተጻፈ ነው መሰረዝ አትችሉም:: ይህንን ለማሳየት ነው ፍጥረት ሁሉ ለእመቤታችን ተፈጠረ ያለ:: ምስጢረ ሥጋዌ ያልገባው ይህንን ለመረዳት ይከብደዋል:: የሚያስተዉል ካለ ከተአምረ ማርያም ከምናገኘው በላይ የሚያስደንቅ የድንግል ማርያም ተአምር እኮ ሉቃስ ወንጌል ላይ ተጽፏል::(ሉቃ1:44)″የሰላምታሽን ድምጽ በሰማሁ ጊዜ ጽንሱ በማሕጸኔ በደስታ ዘለለ” በማለት የመጥምቁ ዮሓንስ እናት ቅ/ኤልሳቤጥ ለወላዲተ አምላክ በድንግል ምክንያት የተፈጸመዉን ተአምር ነገረቻት:: ይህ እኮ ወንጌል ዉስጥ የተጻፈ ተአምረ ማርያም እኮ ነው::
- ዘፍ25:18″እግዚአብሔር ሁለት ኪሩቤል(መላእክት)ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ አለው ሙሴም ሠራ:: አሁንም ከብዙ መቶ አመታት በኋላ ሰሎሞን “በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል(መላእክት) ሠራ”1ነገስት6:23 እንግዲህ እግዚአብሔር የተቀረጸ ምስል አትቅረጹ ብሎ,ወዲያው ሁለት ኪሩቤል ቅረጽልኝ ብሎ እግዚአብሔር ያዘዘው: መናፍቃን እንደሚሉት ሳይሆን: የጌታችንን; የእመቤታችንን; የመላእክትን; የቅዱሳኑን ሥዕል መከልከሉ ሳይሆን የሌላ ምስል እንዳንቀርጽ ነው የታዘዝነው ብለን ማመን አለብን:: አለበለዚያ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው ።ዘጼ20:4&5 ምስል አትቅረጽ አለ:: ዘጸአት25 የኪሩቤልን ሥዕል ቅረጽ ሲል ሁለቱ ፈጽመው አይገናኙም:: ስለዚህ የቅዱሳንን ሥዕል መቃወም ማለት የኪሩቤልን ሥዕል ሥሩ ብሎ ያዘዘዉን እግዚአብሔርን መቃወም ነው:: አታምታቱት:: ስለዚህ እነሙሴ በኪሩቤል መካከል ይሰግዱ እንደነበር እኛም ለቅዱሳን ሥዕሎች እንሰግዳለን:: እስቲ አስቡ ዲያብሎስ እንኳ የራሱን ምስል እንደሚያሠራ ምስሉም እንደሚተነፍስ; እንደሚናገር ብሎም የማይሰግዱትን እንደሚአስገድል ቅ ዮሐንስ በራዩ ጽፎት ይገኛል:: ራዕ 13:15 &16 እንዴት ሰይጣንን ያሸነፈው ቅዱስ ሚካኤል ሥዕሉ; ከዚህ ርኩስ ፍጥረት በበለጠ ተአምር አይሠራ? ክብርስ የማንሰጥ በምን ምክንያት ነው?ከላይ ለኪሩብ (ለመልአክ) ሥዕል እንዲቀረጽ ፈጣሪ እንዳዘዘ አይተናልና:: የእምቤታችን ሥዕልም ከዚህ እጅግ የበለጠ ተአምር ስለሚፈጽም ለሥዕሏ ክብር እንሰጣለን; እንሰግዳለን:: አሁን የነቅዱስ ሚካኤልን እና የሌሎችን ቅዱሳን ሥዕሎች የሚቃወም ነገ እኮ ቅ/ዮሐንስ እንዳለው የአውሬውን ምስል ለመቀበል ነው:ሩጫው:: ተአምረ ማርያም ላይ ለእመቤታችን ሥዕል እንድንሰግድ; ተአምሯን እንድንሰማ ሲነገረን; ክርስቶስን የሚያምን ክርስቲያን; የእመቤታችንን ተአምር ለመስማት አይከበደውም:: እርግጥ ተጠራጣሪዎች አያደርጉትም:: አሁን ተአምረ ማርያምን የተቃወማችሁ: ነገ መጽሓፍ ቅዱስን ትቃወማላችሁ ምክንያቱም በወንጌል” በኔ የሚያምን እኔ የማደርገዉን ያደርጋል;ከዚህም የሚበልጥ”ዮሐ 14:12 የሚለዉን ቃል የሚቀበል ተአምረ ማርያም ለመቀበል አይከብደዉም:: ነው ቀስ ብላችሁ እመቤታችን አታምንም በሉ እና ሰይጣን እንኳ የማይጠራጠረውን ካዱና ይለይላችሁ:: እኛ እመቤታችን ክርስቶስ ያደረገዉን አድርጋለች: ታደርጋለች: አሁን ተአምረ ማርያም ከአንበባችሁት በላይ እንደምታደርግ ክርስቶስ “ከዚህ የሚበልጥ” እያለ በወንጌሉ ይናገራል ሰሚ ካለ:: ይህንን መሰረዝ አትችሉም:: ክርስቶስን የሚወድ እመቤታችንን ይወዳል ለርስዋ ሥዕልም ይሰግዳል; ተአምሯን ይሰማል:: መቅድሙ ላይ እንደተጻፈው:”የታወቀ ምክንያት ካልከለክለው በስተቀር” ክርስቲያን ነኝ እያለ ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይሄድ: እና ተአምሯን የማይሰማ :እሷን ብቻ ሳይሆን ልጇንም እንደናቀ ሰለሚቆጠር; ተወገዘ:: መጽሓፍ ቅዱስ ዕብራዉያን 10:28″የሙሴን ሕግ የናቀ ሁለት ሦስት ምስክሮች ከመሰከሩበት ፈጽሞ ይሙት” ይላል:: የክርስቶስ እናት በልጇ ቸርነት ያደረገችዉን ተአምር የሚንቅማ እንዴት አብዝቶ አይቀጣም? ይቀጣል እንጂ:: ክርስቶስ በስጋ የመጣ አምላክ ብሎ የሚታመን መንፈስ በስጋ የወለደችዉን እመቤታችንን ያከብራል:: ለሥዕሏ በመስገድ; ተአምሯን በመስማት ፍቅሩን ይገልጻል::ያወገዙት በትዕቢት ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄድም ብሎ የቀረዉን: እንደሆነ መቅድመ ተአምረ ማርያም ይነግረናል::ቅ ጳውሎስ “እኛ የክርስቶስ ልብ አለን”1ቆሮ2:16:” እኔ ክርስቶስን እመስላለሁ::እናንተም እኔን ምሰሉ አለን”1ቆሮ 11:1 ቅ ጳውሎስ እንዲህ ካለ የእመቤታችን መልኳ;ሃሳቧ;ልቧ የአምላክን(የልጇን) ይመስላል ቢል ምኑ ላይ ነው ከመጽሓፍ ቅዱስ የሚጋጨው? በድጋሜ ቅ ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች ለሱ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጽላቸው እንዲህ ብሎ ጽፎላቸዋል”አዎን እንደ ክርስቶስ ተቀበላችሁኝ” ገላ4:14:: እና የክርስቶስን እናት እንደ ክርስቶስ አክብረን ብንቀበላት ምኑ ነው ከመጽሓፍ የሚጋጨው?ራሱ ክርስቶስ “እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ” ብሎናል እኮ: ካስተዋልን ማቴ 10:40 ስለዚህ ዘጠኝ ወር በማሕጸኗ የተሸከመች ከሓዋርያት: ከነብያት; ከቅዱሳን ሁሉ ትበልጣልች::
- ቅዱስ ቁርባን መቀበል ካልቻለ ተአምረ ማርያም ሰምቶ ይሂድ የሚለው ግልጽ እና ጥሩ ምክር ነው::ይህ የአባቶቻችን ምክር ነው:: እንግዲያስ መቀበል ላልቻለ ምን ይበል?ተስፋ ይቁረጥ?” ካልቻለ” ምን ያድርግ?መልሱን ንገረኝ?በእመቤታችን ተማጽኖ ይሂድ አለ እንጂ ሥጋ ወደሙን ይተካዋል:አትቀበሉ:አላለም::አታጣሙት:: እኔ መቀበል ካልቻልኩ ምን ታደርገኝ? በቀኝ የተሰቀለው ስጋ ወደሙ ተቀበለ አይልም::በሚያስደነቅ ምሕረቱ ማረው:: ከነብዩ ኤልያስ አንበልጥ:: እሱ እንኳ ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን(2ነገስት2:9-12) “ካንተ ሳልወሰድ አደርገልህ ዘንድ የምትሻውን ወደ እኔ ለምን(ጸልይ)”አለው:: የኤልሳዕም ጸሎት ልመና “ያንተ መንፈስ እጽፍ ድርብ ሆኖ በኔ ላይ ይወረድ አለው” ኤልያስም ሳርግ ካየህኝ ይሆንልሃል አለው:: አየው መንፈሱ እጽፍ ድርብ ሆኖ አረፈበት::
ነብዩ ኤልሳዕ ከሞተ በኋላ በአጽሙ የሞተ ሰው አስነሳ:: 2ነገስት13:20-21 ስለዚህ ነብዩ ኤልሳዕ ወደ ኤልያስ ከጸለየ እና ኤልያስም ወደሱ እንዲለምን ከመከረው:እኛም ኣባታችን ሆይ ብለን: ወደ ወላዲተ አምላክ መጸለያችን ምኑ ነው ተአምረ ማርያም ከመጽሓፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጨው? ይህ ተአምረ ማርያም ጋር ቢጻፍ ኖሮ ይሰረዝ ትሉ ነበር:: እግዚአብሔር ለሙሴ እኮ የሰጠዉን ሥልጣን ብናስታዉሰው;ብናስተዉለው እንዲህ የእመቤታችንን ክብር አንቃወምም ነበር:: እየረሳነው እኮ ነው:: ዘጸአት7:1 “ሙሴ እይ እኔ ለፈርዖን(ለግብጽ) አምላክ አድርጌሃለሁ አለው”አሁን ልጇ የዚህ አምላክ(ለዚህ ትውልድ)አምላክ አድረጌሻለሁ ቢላት መችም ተሀድሶዎች ሰላማዊ ሰልፍ መዉጣታችሁ አይቀርም:: እናቱ ሰለሆነች;እናትና አባትህን አክብር ብሎ ያዘዘን እናቱን ሲያከብራት አይተናል; እናያለንም(ያሳየናል):: ዲያብሎስ ቢቆጣም:: የእመቤታችንን ክብር ለሙሴ የሰጠዉን; ለሷማ አብልጦ አይሰጣትምን? ይሰጣታል:: ከዚህ የምረዳው ከፈጣሪ ጋር እየተጣላችሁ ነው::እንኳን ለእናቱ ለእመቤታችን ይቅርና በፍርድ ቀን በ12 ዙፋኖች ተቀምጠው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባዉን አና የሚወጣዉን የሚፈርዱ እኮ ሓዋርያት ናቸው ማቴ19:28″የሰው ልጅ ሲመጣ በ12 ዙፋኖች ተቀምጣችሁ ተፈርዳላችሁ”አላቸው ::በዚያን ጊዜ ዳኞች(ሓዋርያት) ይቀየሩ ማለት እንደማትችሉ አሁን እወቁት::ሰማይ ምድር ቢያልፍ ቃሉ አያልፍምና;አንድ ጊዜ በቃሉ ስልጣኑን(የመንግስተ ሰማያትን ቁልፍ) ሰቷቸዋልና(ማቴ 16:19)ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በላይ በሰማይ በታች በምድር የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚተካ እንደሌለ ታስተምራለች::ሁሉም ወደ ሥጋው ወደሙ እንዲቀርቡ;ከቅዱስ ቁርባን እንዳይርቁ ትመክራለች::ነገር ግን ለዚህ ያልበቁትን ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማድረግ; ንስሐቸውን እስከሚፈጽሙ ድረስ በደጅ ጥናት ያሉትን;በትምህርት ላይ ያሉትን ሁሉ መቀበል የማችሉትን እንጂ የሚችል ሥጋዉን ደሙን ተቀበሉ ያልቻላችሁ ተአምረ ማርያም ስሙ እና ሂዱ ብላ ትሰብካለች:: በተጨማሪ እየቆረቡን ያለነዉንም መቀበል የማንችልበት ችግር ሲገጥመን:ተአምረ ማርያም ሰምተን;በርሷ ተማጽነን እንሄዳለን:አንጠራጠርም::ይህ እኮ ወንጌልም ላይ ማርቆስ 11:23-24″እውነት እላችኋለሁ; ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ባይጠራጠር …የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ:ይሆንላችሁማል::” የምናምን ኦርቶዶሳዉያም እንደሚደረግለን እናምናለን:ይደረግልናል::ከዚያም በእመቤታችን ምልጃ ንስሐ ገብተን;ለሥጋው ወደሙ እንበቃለን:: - ውግዘት በተአምረ ማርያም አልተጀመረም ቅ:ጳዉሎስ ሁለት ጊዜ “ከተቀበላችሁት የተለየዉን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ(የተወገዘ) ይሁን” ብሏል::45 ሚሊዮን ኦርቶዶክሳውያን የተቀበልነው የተሰበከልነን የሚቃወመዉን መጀመሪያ ቅ ጳዉሎስ በኋላ ደግሞ እነ አቡነ ገብርኤል እና ኣባ ሚካኤል አዉግዘዉልናል::በሥጋዉም በምድር በሰማይ በነፍሱም የክብር ትንሳኤ የለዉም አለ ለዘላለም ይቃጠላል ሲል ነው::
- አሥሩን ትእዛዛት እና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል የፈጸምኩ እኔ ነኝ የሚል ማን ነው?ተአምረ ማርያም የሚለው ትእዛዙን ለመፈጸም ባንችልም(አሁንም አልቻልንም) ተስፋ አለን; በክርስቶስ አምነን በእመቤታችን ተማጸነን እንድናለን ነው ያለን:: ትእዛዙን አትፈጽሙ አላለም:ት እዛዙን አትፈጽሙ እንደሚል አድርገህ አታቅርበው:: ይህንን አነጋገር የወሰደው ከቅ ጳዉሎስ ነው”በሕግ ለመጽደቅ የምትፈልጉ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል” ይለናል::ገላ5:4;ገላ 2:16″ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ስራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል::” እኛም በክስቶስ አምነናል;በወላዲተ አምላክ ተማጽነናል:: የሐዋር13:39″…በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ሮሜ 3:20 & 28 “ይህም የሕግን ሥራ በመስራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው” ሮሜ8:3″ከሥጋ የተነሳ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለዉን ;እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢያተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢያትም ምክንያት ልኮ አድርጓልና” ስለዚህ በተአምረ ማርያም የምናገኘው ሕጉንና ት እዛዙን ባለመፈጸማችን ተስፋ እንዳንቆርጥ;ልክ ቅ/ጳዉሎስ እንዳስተማረው;በልጇ ቸርነት;በወላዲተ አምላክ አማልጂነት ትድናላችሁ ቢለን;ተስፋ ለማቆረጥ የሚጻፈው ጽሑፍ መቆም አለበት::
- የብላዔ ሰብዕ 78 ነፍስ አጥፍቶ መማሩ በማቴ10:42″በደቀ መዝሙር ስም ቀዝቃዛ ዉሃ ቢጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም” በሚለው አምላካዊ ቃል መሰረት ነው:: ተአምራ ማርያም እንደሚነግረን ስምዖን የተባለው ይህ ሰው ብዙ ነፍስ ካጠፋ በሗላ ንስሓ ገባ:ተጸጸተ ልክ በቀኝ እንደተሰቀለው ወንበዴ::በወንጌሉ መሰረት ለድሀ ከደቀመዛሙርት ሁሉ;ከፍጥረት ሁሉ በከበረችው በእመቤታችን ስም ቀዝቃዛ ዉሀ ለድሀ አጠጣ:: እመቤታችም በወንጌሉ መሰረት ማርለኝ አለችው; ማረላት::በቀኝ የተሰቀለ ከብላዔ ሰብዕ(ከዚህ ሰብ በላ) የበለጠ ይሥራ; አይሥራ እኛ አናዉቅም:: ቃል ኪዳን ሲሰጥ ክርስቶስ ገደብ አላስቀመጠም(ይህንን ያህል የገደለ አልምርም:የሚል የለ)::በደቀ መዝሙር ስም ያጠጣ አለ እንጂ::ስለዚህ የወንበዴውን መዳንም እየተጠራጠሩ በወንጌል አምናለሁ ማለት አይቻልም:: በወንጌል ተጽፎ ነው እንጂ በቀኝ የተሰቀለው ታሪክ በተአምረ ማርያም ቢጻፍ ኖሮ አይቀበሉትም ነበር::
ይቀጥላል!….
ወስብሃት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር