አፄ ዘርኤአቆብና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ፡- ታሪክ ማፋለስና ቅዱሳን መሳደብ ይቁም Addisu Tesfaye Mengistu
የ ኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ለማፈራረስ በተለያዩ ግዜያት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል።መሰረትዋ በ ዓለት ላይ የሆነው ተዋህዶ ግን በማንም ሳትንበረከክና ሳትፈርስ ለሁለት ሺ አመታት ተጉዛ እዚህ ደርሳለች። ፈተናው ግን አሁንም አልቆመም። የወቅቱ የቤተ ክርስትያን ፈታኞች ደግሞ በደጉ፣ በሊቁና በታላቁ የኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ዘርዓያዕቆብ ላይ ዘምተዋል። በበርካታ ድረ ገጾች ላይ ስማቸውንና ክብራቸውን የሚያጎድፍ አዲስና ተለጣፊ መሰረተ ቢስ ታሪክ ከመለጠፍ አልፎ ፤ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ስርዓትና ሓይማኖት ያበላሹ ንጉስ “ ብለው እስከመሳደብ ደርሰዋል። ኢነዚሁ የተረት ሊቃውንት፣ “ታምረ ማርያምን የጻፉ እሳቸው ናቸው፣ ገዳም ገብተው አፈረሱ መነኩሴ ነበሩ” እና ወዘተ የሚሉ የፈጠራ ክሶችንም አስነብበዋል። እውን ግን ያፄ ዳዊት ልጅ አፄ ዘርአያዕቆብ ይህን አድርገው ይሆንን ? አረ በፍጹም። እንዲያውም በ ኢትዮጵያ ቤተ መንግስትም ሆነ ቤተ ክህነት ከፍተኛ ውለታ ሰርተው ያለፉ ደግና ምትክ የለሽ ነጉስ ነበሩ። አንቀጽ ባንቀጽ እንመልከት
አፄ ዘርኣ ያእቆብ፤ ሲነግሱ የተረከቡዋት ኢትዮጵያና የ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን
አፄ ዘርአያቆብ ፈጠጋር በተባለው ቦታ (ባሁኑ ኦሮምያ ክልል አዋሽ ወንዝ አካባቢ) ተወለዱ።እንደንጉስ ልጅነታቸውም በቤተ መንግስት አደጉ። አባታቸው አፄ ዳዊት ሲሞቱ ታላላቅ ወንድሞቻቸው አጼ ቴዎድሮስ (ቀዳማዊ)ና አጼ ይስሀቅ ንግስናውን ተረክበው ኢትዮጵያን ለ 20 ዓመት ገዙ።ወንደሞቻቸው ነግስው ሳለም አምባ ግሼን ላይ ለብዙ አመታት ታሰሩ። በሗላም እሳቸው ነገሱ። ከነገሱም በሗላ የሲዳሞ ሀድያ ንጉስ ልጅን ከስልምና ወደ ክርስትና አስጠምቀው አገቡ። ()
አፄ ዘርአያቆብ የተረከቧት ኢትዮጵያ ግን በቤተ መንግስቱም በ ቤተ ክህነቱም ወገን አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ላይ ነበረች። አባታቸው አፄ ዳዊት “አባይን ገድባለሁ” ብለው ገብፆችን አስፈራርተዋቸው ስለነበር ግበፀችና ቱርኮች ባዳል በኩል ክርስትያኑን መንግስት ለመደምሰስ ተዘጋጅተዋል። በሰሜን የዮዲት ጉዲትን ያይሁድ ስርወ መንግስት መልሶ ለመትከል ቤተ እስራኤሎች( ፈላሾች) ጦር ሰብቀው ተነስተዋል። ቤተክህነቱም ውስጥም ውዝግቡና ልዩነቱ ሰፍቶ ነበር። ቤተክለሃይማኖትና ቤተ ኤውስጣጥዮስ ልዩነታቸው ከሮ ሰፊ ክፍተት ተፈጠረ። ሚካኤላውያን ሚባሉቱ ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን መለየት ጀመሩ።የአይክኖክላስትን የኑፋቄ መርዝ የሚረጨው የነ እስጢፋኖስ ( የደቂቀ እስቲፋኖስ መነሻ) ቡድንም ሌላው ችግር ነበር። //
ጀግናው ፣ሐዋርያው ና ሊቁ ዘርአያቆብ ግን በግብፅና በቱርክ ድጋፍ የክርስትያኑን መንግሰት አጥፍቶ የእስላም መንግስት ለመትከል አስቦ የተነሳውን እና የዮዲትን ያይሁድ መንግሰት ለመትከል የተነሱትን የፈላሻ እንቅስቃሴ በጦር ሀይል ድባቅ ከመቱ በሗላ ፤ በሃይማኖት የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ፊታቸውን ወደ ቤተ ክህነት መለሱ ።
ቤተ ተክለሃኢማኖትና ቤተ ኤዎስጣጢዮስ፤ ሚካኤላውያውንና የአይክኖክላስት ኑፋቄ አራማጆች። ሶስቱንም በመጠኑ እንመልከት።
ቤተ ኤዎስጣጢዮስና ቤተ ተከለሃይማኖት
በአጼ ዘርያእቆብ ዘመነ መንግስት ተነስቶ የነበረው ከባዱ የየሃይማኖት ውዝግብ የቤተ ተክለሃይማኖትና በቤተ ኤዎስጣጢዎስ መካከል ሰንበትን በተመለከተ የተነሳው ልዪነት ነበር።የልዩነታቸውም ምክንያት የሰንበት አከባበር ሲሆን ፣ ቤተ ተክለሃይማኖቶች ትምህርታቸው ሰንበት እሁድ ብቻ ናት ሚል ሲሆን ፤ የቤተ ኤውስጣጢዮሶች አስተምህሮ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ ( ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜ እና የሐዲስ ኪዳን ሰንበት እሁድ ) ሁለቱም ሰንበታት ስለሆኑ መከበር አለባቸው የሚል ነበር። ሁለቱም አመለካከቶች ይመሩ የነበሩት በወቅቱ ከፍተኛ ክብርና ዝና በነበራቸው ሊቃውንት አባቶች መሆኑ ሌላው ፈታኝ ነገር ነበር። ቤተ ተክለሃይማኖቶች በማእከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ ክፍላተ ሀገራት ባሉ ገደማትና ምዕመናን ክፍተኛ ተከታይ ነበራቸው። ግብጻውአኑ ጳጳሳትም ቤተ ተክለሃይማኖትን የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየታቸው ደግሞ ሌላው አበይት ጉዳይ ነበር።
ቤተ ኤውስጣጢዮሶች ደግሞ ከአስመራ( ኤርትራ) የሚገኘው የደብረ ቢዘን ገዳም ጀምሮ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባሉ ሌሎች ገዳማትና አድባራት በርካታ ተከታዮችና ደጋፊዎች ነበሯዋቸው።ይህም ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ መዘዝ ነበረው። በወቅቱ ለንጉሰ ነገስት አጼ ዘርአያዕቆብ ከባድ ፈተና ነበር;; ይንንም ዝነኛው ታሪክ ፀሀፊ Adrian እንዲል ሲል ይገልጸዋል
“Debre Bizan, the greatest of Ewostotathian monastery lies on the Eastern edge of the plateau of Eritrea, only ten miles from the sea and overlooking the coast . The political value of supporting Sabbath observance with in Zera Yaikobs strategy is obvious enough. With out Ewostotathian loyality Eritrea , the coast , and even wider areas of the North might hardly be served . yet he waited pretty patiently before calling the council”
ይሕው በቃውንቱ መካከል የተፈጠረ ልዩነት ወደ አስከፊ ክፍፍል እያመራ በመሄዱና የሀገሪቱንም ህልውና ችግር ውስጥ እከተተ እንደሆነ የተረዱት አጼ ዘርአያቆብ አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል ተባሉት ጳጳሳትን ከግብጽ ካስመጡ በሁዋላ በሁለቱ አስተምህሮዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት በተጉለት ቡልጋ ደብረ ምጥማቅ ገዳም ጉባኤ ዘረጉ። በዚሁ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስትያን ሊቃውንት በተገኙበት ጉባኤ ላይ መጠነ ሰፊ ክርክር ከተደረገ በሁዋላ ሊቃውንቱ ሰንበታት ማለትም ቀዳሚት ሰንበት ቅዳሜና የሐዲስ ኪዳን ሰንበት እሁድ ሰንበታት ተብለው መከበር እንደሚገባችው ፤ የቀዳሚት ሰንበት አከባበር ግን እንደ አይሁድ ባለ አከባር ሳይሆን ክርስቲያናዊ አከባበርን የተከተለ መሆን እንዳለበት የሁለቱም ወገኖች ሊቃውንት ተስማምተው ለ በርካታ አስርተ አመታት የቤተ ክርስትያን አባቶችን ሲያናቁር የነበረው የሰንበት አከባበር ጉዳይ በማያዳግም ሁኔታ ተወሰነ።ለዘመናት ሲንከባል የመጣው ልዩነት ባፄ ዘርአያቆብ ዘመነ መንግስት መፍትሄ አገኘ።
ሚካኤላውያን
ሌላው በኚሁ ንጉስ አጼ ዘርአያቆብ ዘመን ህዝቡን ያምስ የነበረው የሃይማኖት ውዝገብ ሚካኤላውያን የሚባለው ነበር። ይሕው “የዘሚካኤላውያን” በመባል ሚታወቀው እንቅስቃሴ ጊዮርጊስ በሚባል መነኩሴ ይመራ ነበር። ትምህርታቸውንም Church in EthiopiaAfrica በተባለው መፅሀፍ እንዲህ ሲል ሲገልፀው
“ Giorgis a monk who taught the unknowabilty of God and gave rise to the group known as The mikaelities “ ::ግብፃውያኑ የታሪክ ጸሀፊዎች ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አብራርተው ፅፈውታል።
“ .. compared the unity and trinity of God with three suns whose lights are united when they appear side by side, three suns (persons) with one light (divinity). The opponents of this view, proposed instead, as Fre Makhebar did, one sun with a disk (God the Father), light (God the Son), and heat (God the Holy Spirit). ‘
የዚህ ቡድን አባለት በርካታ የሚያነሳቸው ነጥቦች ቢኖሩም ዋናው የሚታወቁበት አጀንዳ ግን በምስጢረ ስላሴና ምስጢረ ስጋዌ ጉዳይ ነበር ፤፤ ጥቂቶቹ የክርክር ነጥቦቹም እነዚህ ነበሩ
• ስላሴ ጎን ለጎን ባሉ በሶስት ነገር ግን አንድ ብርሃን( መለኮት) ባላቸው ሶስት ጸሐይ ይመሰላሉ ። የለም ስላሴ ባንድ ጸሐይ ይመሰላሉ። የጸሐዩ ክበብ አብን ብርሀኑ ወልድን ሙቀቱ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን በሚለው ምሳሌ ይመሰላሉ …
• ወልድ ለፍርድ ሲመጣ አብና መንፈስ ቅዱስም ከጎኑ ሆነው በሰው አምሳል ይታያሉ እና ይህን መሰሎች ነበሩ።
ይህም ልዩነት ለመፍታትም በዘርአያቆብ ድካም ጉባኤ ተዘረጋ። ሊቃውንቱ ተቀምጠው ተወያይተው ትክክለኛው ትምሀርተ እንዲፀና አደረጉ።
ደቂቀ እስጢፋኖስ ( ኤኢክኖክላስቶች)
በሜድትራኒያን አካባቢ ከ 7-9ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ “ስዕላትን እና ቅርፃቅርፆችን ከቤተክርስትያን ይወገዱ” የሚል የኑፋቄ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። Iconoclast የተባሉት ቡድኖች ስእላት በቤተክርስትያን አያስፈልጉም ብለው ስእላትን ካምልኮ ስፍራዎች በሙሉ ለማስወገድ ተነስተው ነበር {}። የሜዲትራንያኑን ዓለም ክርስትያኖች ያመሰው ይህ የኑፋቄ ትምሀርት ወደ ኢትዮጵያም በ 13ኛው ክፍለ ዘመን እየተንዃተተ መግባቱ አልቀረም። ባፄ ይግባ ፅዮን ዘመነ መንግስት( 1285-1294) አንዳንድ በ ኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ውስጥ ይህንን ሐሳብ የሚያራምዱ አይክኖክላስቶች ( ፀረ ስእልና ቅርጻ ቅርጽ ) ተነስተው እንደነበረ የኮፕት ታሪክ ሊቃውንት በኮፕቲክ በመዛግብታቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል ።
“In Ethiopia it started during the reign of Yagbe’a Seyon (1285-1294), when a group of clergy maintained that the icon was mere slate and the cross a mere piece of wood from Golgotha. These dissidents created great schism in the church. Since Ethiopian leaders suppressed dissidence …”
እነዚሁ ኤክኖክላስቶችን የተበከለ ትምህርት ይዘው ስእልና መስቀል ከቤተ ክርስትያን መውጣት አለባቸው ብለው ቤተ ክርስትያንን ሲበጠብጡ የነበሩት አካላት በወቅቱ በነበሩ ሊቃውንትና በነገስታቱም ድጋፍ ከቤተ ክርስትያን ከኑፋቄያቸው አንዲታገሱ ቢደረግም ፤ ውስጥ ለውስጥ ግን መርዛቸውን ማግሳታቸው አልቀረም።በ15ኘው ክፍለ ዘመን ተነስቶ የነበረውም መናፍቁ እስጢፋኖስና ተከታዮቹ ደቂቀ እስጢፋኖስ በመስቀልና በመቤታችን ክብር ላይ ያነሳው ጥያቄ መነሻው ይሄ ከሜድትራኑ ዓለም በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ተነስቶ የነበረና በሁዋላ ባስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የገባ ፤ በወቅቱ የነበሩትም ንጉስ አጼ ግባጽዮንና በሊቃውንቱ ተወግዞና ታግሶ የነበረ ኑፋቄ ፤ በሁዋላም በዘመነ አጼ ዘርአያእቆብ ዘመነ መንግስት እስጢፋኖስ መልሶ ያነሳው ትምህርት ነው። ይህንንም ችግር ለመፍታት አጼ ዘርአ ያእቆብ ባደባባይ ጉባኤ ስለጠሩና ጉዳዩ ካጼ ዘርአቆብና ከእስጢፋኖስ ስም ጋር ይነሳል እንጂ የዚህ የኒፋቄ ትምሀርት መነሻ ኤክኖክላስቶች ናቸው( የዛሬው ጂሆባ መሰረቱ የጥንቱ አርዮስ እንደሆነው ሁሉ ) ።
በዘመናቸው የተነሳውን የሃይማኖት ውዝግብ መፍትሄ ካልሰጡ ለሀገር የሚተርፍ ችግርና መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የተረዱት አጼ ዘርአ ያእቆብ፤ አስጢፋኖስንም ለሌሎቾ ( ለቤ ተክለሃይማኦትና ለቤተ ኤውስጣጢዮሶች እንዲሁም ለሚካኤላውአን ) እናዳደረጉት ሁሉ ጉባኤ ሰርተው ሊቃውንቱን ሰብስበው አወያዩ;
አቡነ ጎርጎርዮስ የቤተ ክርስትያን ታሪክ በተባለው መጽሀፋቸው ገጽ 45 ላይ ሁኔታውን እንዲህ ገልጸውታል
“ ቤተ ክርስትያናችንን ስነ ጽሁፍና ኪነ ጥበብ አስፋፉት ፣አምልኮ ጣኦትን ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት የታገሉት ኦጼ ዘርአያቆብ ናቸው። ከዚህም ሌላ በዘመናቸው ዜና መዋእላቸው እንደሚለው ደቂቀ እሰጢፋ የሚባሉ ለመቤታችንና ለመስቀል ስግደት አይገባም የሚሉ መናፍቃን እንደተነሱ ይጽፋል። ይሕውም ዜና መዋእል እንደሚለው እነዚህን መናፍቃን ንጉሱ ባሉበት ሊቃውንቱ ተከራክረው ረቱዋቸው. ከዚህ በሁዋላ እነ ደቂቀ እስጢፋኖስ ለፍርድ ወደ ንጉሱ ቀረቡ ። ንጉሱም ፍርዳቸውን ክምእመናን እንዲቀበሉ የተሰበሰቡትን ምእመናን ጠየቁ ሁሉም በሞት ቅጣት እንዲቀጡ በየነባቸው።
የዘርአያዕቆብ መጻሕፍት
አጼ ዘርአያቆብ በቀደሙት ግዜያት ተነስተው ሲንከባለሉ እሳቸው ዘመነ መንግስት ላይ ደርሰው ምእመናንና ቤተ ክርስትያንን ሲያውኩ የነበሩ ሶስቱንም ልዩነቶች ፣ ሊቃውንቱን ስብስበው አከራክረው ሰላም አወረዱ። ደብረ ምጥማቅ ቡልጋ በተካሄደው ጉባኤ ቤተ ተክለሃኢማኖትና ቤተ ኤውስጣጢዮሶች ለበርካታ ዘመናት የቆየውን የሰንበት አከባበር ልዩነታቸውን አስወግደው ተስማሙ።፡ ሚካኤላውያንም አንስተውት ነበረውን የሚስጥረ ስላሴ ና ስጋዌ አስተምሀሮ ልዩነት በጉባኤ ተፈታ። መናፍቁ እስጢፋኖስ ም ከሊቃውንቱ ጋር ተከራክሮ ተረታ።
አጼ ዘርአያቆብ ችግሩ ተፈታ ብለው ግን አርፈው ቁጭ አላሉም። ከዚህ በፊት ተነስተው ነበሩ ችግሮች ወደፊትም እንዳይደገሙና በቃል የተደረገው ክርክር ቢረሳ በማለት ህዝባቸውን የሚመክር መጻህፍትን ማዘጋጀት ጀመሩ።የሚካኤላውያን የሃይማኖት ጉዳይ ከሚስጥረ ስላሴ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረዱት ነጉሰ ነገስት ዘርአያዕቆብ መጽሐፈ ስላሴ የሚባል መጽሀፍን ደረሱ። መናፍቁ እስጢፋኖስ በመቤታችን ክብር ላይ የኑፋቄ መርዝ እንደረጨ የተገነዘቡት ዘርአያዕቆብ መጽሀፈ ምእላድ የሚባል መጽሀፍን ደረሱ። ስለ ሰንበት አከባበርና ሌሎች ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚመክር መጽሀፈ ብርሃን ተሰኘ ሌላ አስደናቂ መጽሀፍ ደርሰው ለህዝባቸው መማርያና መጽናኛ ይሆን ዘንድ አበረከቱ።
ታምረ ማርያምና አጼ ዘርአያቆብ
አንዳንድ የተሳሳቱ ወገኖች ተአምረ ማርያምን የደረሱት አጼ ዘርአያቆብ እንዲሆኑ አድርገው በሬ ወለደ አ ይነት ተረት ሲአወሩ ይደመጣሉ። ሌሎች ደግሞ “ታምረ ማርያምን ለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ያስተዋወቁት እንዲነበብም ያደረጉት እሳቸው ናቸው” በማለት የተሳሳተ ታሪክ ያወራሉ ይጽፋሉም። እውነቱ ግን ሌላ ነው።
ታምረ ማርያም ከጥንት ጀምሮ በ አትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሲነበብ የነበረና በሊቃውንቱም ሆነ በምእመናኑ ዘንድ የተከበረ መጽሀፍ ነው። ለዚህም እንደከዋክብት የበዛ ማስራጀ ማቅረብ ቢቻልም ጥቂቱን እንመልከት ።
Jacques Mercier, “Ethiopian Art History” in Ethiopian Art: The Walters Museum (London: Third Millennium, 2001), በተባለው መጽሀፉ ገጽ 51ላይ ታምረ ማርያም ባጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት ይነብብ እንደነበረና አረብኛውንም ታምረ ማርያም ያስተረጎሙት አጼ ዳዊት መሆናቸውን እነዲህ ሲል ይገልጣል።
“During his(Dawit) reign, two surviving examples of illustrated manuscripts were produced. One is a translation of the Miracles of Mary which had been written in Arabic, done at the command of Emperor Dawit; this is the oldest surviving illustrated book commissioned by an Ethiopian Emperor”
James bedinger , African kings በተባለ መጽሀፉ ላይም ዛግዌ ነገስታት በመቤታችን ስእል ስርኛ በመስቀል ስር ሰግደው ተንበርክከው ጸሎት ያደርሱ እንደነበረ ፤ታምረ ማርያምም በየሰንበቱ ይነብብ እንደነበር መስቀልንም ይስሙ ይሳለሙ እንደነበረ በማያሻማ ጽሁፍ ገልጾታል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገድለ ዜና ማርቆስ የያዛቸው መረጃዎችና ሁነቶች በሚል ጥናታው ጽሁፉ ላይ አንዳቀረበው ገድለ ዜና ማርቆስ ብዙ ምስክርነቶችን የሚሰጥ ሲሆን … ጸሐፌ መንክራት ዮሐንስ ተአምረ ማርያምን በጻፈ ጊዜ እመቤታችን ያደረገችለትን ነገር /ገጽ.192/፡፡ ተአምረ ማርያም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በፊት እንደ ነበረ መረጃ እንደሚሰጥ ይገልጣል።
የመቤታችን 33ቱ በ ኣላትም አፄ ዘርአያቆብ የፈለሰፉት ሳይሆን በወቅቱ ክግበፅ ቤተክርስትያን ( ሙአላቅ) የተወሰደ ስርአት እንደሆነ ይህንን በረከት በአልም ያስተማሩት ግብፃውያን እንደሆኑ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ይናገራል።
“Many miracles that she worked in Spain, France, Italy, Syria, and Egypt were translated into Ge‘ez, the church language of Ethiopia. At that time, the rule from Mu‘allaqa, Masehafa ser‘at, ordaining thirty-three holidays in honor of the Virgin, was brought to Ethiopia.”
አፄ ዘርኤአቆብ በርካታ ጉባኤያት እንዲካሄዱ በማድረግ ቤተ ክርስትያንን ትምህርት አፅንተዋል። በቤተክርስትያን አነጋገር ትምህርተ ሃይማኖት በጉባኤ ተወሰነ ሲባል፤ሰዎች ተሰባስበው የጋራ መግለጫ አወጡ ማለት ሳይሆን ፤ገበሬ አህሉ አጠገብ ወይም እህሉን መስሎ አዝመራውን የሚጎዳ አረም ሲበቅል ከህሉ መካከል ነቅሎ እንዲጥል ቤተክርስትያንም ባይኑዋ አይታ በጆሮዋ ሰምታ በጇ ዳሳ በምታውቀውና በምታምነው እውነት አጠገብ የራስዋን እውነት መስሎ የሚጎዳትን የመናፍቃንን አስተሳሰብ አረም ነቅላ ለመጣል ጉባኤ ታደርጋለች። አረሙንም ነቅላ ጥላ ትምህርተ አዝመራዋን ትተክላለች። ይህም ክጥንት ሐዋርያት የተገኘ ትውፊት ነው ( ጉባኤ ኒቅያ ፣ ኤፌሶን ወዘተ ) ። አፄ ዘርአያቆብም ያደረጉት ይህንን ነው።
አንድም ለቤተ ክርስትያን እንግዳ የሆነ አዲስ ትምህርት አላስማሩም። የነበረውንና በሊቃውንት የተወሰነውን እንዲፀና አደረጉ አንጂ። ታምረ ማርያምም በዛግዌ ነገስታት ዘመን ጀምሮ ይነብብ ይከበር የነበረ መጽሀፍ እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል። አረብኛውን ቅጂም ያስተረጎሙት አፄ ዳዊት መሆናቸውንነ አሁንም በርካታ መረጃዎች ይናገራሉ ። ግማደ መስቀል አፄ ዳዊት ዘመን ስለመጣ የመስቀል በ አልም በድምቀት መከበር የጀመረው በሳቸው ዘመን ሲሆን ቀጥሎም ልጆቻቸው በአጼ ቴዎድሮስ (ቀዳማዊ)ና በአጼ ይስሀቅ የቀጠለ ትውፊት እንደነበረ አሁንም ታሪክ ኢመሰክራል ። አፄ ዘርኤአቆብ ይሄንን ጥንታዊ ስርአት አስተብቆ መቀጠል እንጂ ሀዲስ ትምህርት አላመጡም ። አላስተማሩምም።
ሲጠቃለል
በዘመናችን ተለጣፊ አዲስ ታሪክ እየፃፉ፣ ደጋጎችን ነገስታት ፃድቃንና ሊቃውንት መሳደብ ፋሽን ሆኖዋል። ከዚህ በፊት ለብዙዎች አዲስ ታሪክ ተፅፎላቸው ፣በሙት ደብዳቢዎች ሲሰደቡ ሲወገዙ ከርመዋል፡፤አሁን ደግሞ ተረኛው አፄ ዘርአያቆብ ሆነዋል። አፄ ዘርአያቆብ ግን በቤተከርስትያን የታሪክ ሰማይ ላይ ፣ እንደንጋት ኮከብ የሚያበራ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል። ለመላው የተዋህዶ ክርስትያን በሙሉ ጀግናና ፃድቅ ናቸው –አፄ ዘርአያቆብ ዳዊት ስመ መንግስቱ ቆስጠንጢኖሰ።
“To ZeraYakob …as he grew older he grew more e worried by the weakness in the faith of his people, the superstition, the ignorance, the pagan practice, the appeal of Judaism,the pastoral laziness, the theological deviation of the monks …were his prime concerns
በክርስቶስ መሰረት ላይ የታነፀችው ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንም አንድም የሚታደስ ትምህርተ (ነገረ) ሃይማኖት የላትም ። የቤተክርስትአን ስርአትም ሆነ ነገረ ሃይማኖት የተደነገገው ትናንት በሚሳሳት ዛሬ ደግሞ ስተቱን በሚአርም ሰው ሳይሆን ፤ ትናትም ዛሬም በማይሳሰተው ፍፁም በሆነው መንፈስ ቅዱስ መሪነት የተደነገገ ስለሆነ መታደስ ፣ምንም አይነት ነገረ ሃይማኖትም ሆነ ስርአተ ቤተ ክርስትያን መከለስ ፣መጨመር ፣መቀነስ አያስፈልገውም። ሃይማኖት እናዳባቶቻችን ፣ጥብብ እንደግዜአችን።ሃይማኖትን ተቀብለን ለማማን እንጂ ለመከለስ ስልጣኑም፣ ብቃቱም፣ መብቱም የለንም።
ቤተክርስትያንም የራሷ ፣ በድንቅ ሊቃውቶችዋ የሚመራ የሊቃውንት ጉባኤ አላት። ይህም ጉባኤ የቤተ ክርስትያን ሆኑ መፃህፍትን መርምሮና ተመልክቶ ያሳትማል። ስለዚህ ቤተ ክርስትያን የሚከለስም ሆነ የሚታደስ መፃህፍት የሉዋትም ።ያለ ሊቃውንት ጉባኤ አውቅና ግለሰብ ለሚያሳትሙት ( ተስፋ ዘብሄረ ምናምን ፣ ገብረስላሴ ዘብሄረ ምናምን፣ ዲያቆን እንትና፣ ዘማሪት እንትና ) መፃህፍት ግን ስህትት ካለባቸው ችግሩ ራሳቸውን ግለሰቦቹን( አሳታሚዎቹን ) አንጂ ቤተክርስትያንን አይመለከትም።
ስለዚህ ታድሶዎች ሌላ መጫዋቻ ካርታ ፈልጉ። ትናትና ቤተክርስትያንን እናድሳለን ብለው የተነሱ ሰዎች ዋናው ጥያቄ አድርገው ሲያቀረቡ የነበረው “በኦርጋን በጊታር አንዘምር” ነበረ።፡በሁዋላ “ማርያም አታማልድም ፣ መላክት አያማልዱም ፣ ክርስቶስ ነው አማላጅ” ማለት ጀመሩና በመጨረሻ የመናፍቃኑን ጎራ ተቀላቀሉ። “ተሀድሶ ነን፣ መነኮሳት ነን” ሲሉ የነበሩት እነ አባ ዮናስ ፣ አባ ብእሴ መጨረሻቸው የት እንደሆነ እኮ እንተዋወቃለን። እነ ዲያቆን ግርማ፣ እነ ገረመው ፣ ስዪም ወዘተ “ቤተ ክርስትያን ትታደስ “ብለው መጨረሻቸው ምን እነደሆነ እኮ የቅርብ ግዜ ታሪክ ነበር; “ዛሬም ቤተ ከርስትያን አናድስ “ሚለው ዘመቻ ቤተ ክርስትያንን ለማፍረስ ነው። አራት ነጥብ።
ይቆየን
ይቀጥላል
References
Marcus Harold, A history of Ethiopia
Copts in Ethiopia
James bedinger , African kings
Jacques Mercier, “Ethiopian Art History
{}።
Adrian .B, The Ethiopian church and zera yakob
/
አቡነ ጎርጎሪዎስ የ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ታሪክ