መፍትሄ ያልተገኘለት የሲሚንቶ ዋጋ ጣራ ደረሰ
(ኢትዮ እማማ)
ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሲሚንቶ ዋጋ እየጨመረ ከመሄዱም በላይ የወያኔ መንግስት ከውጪ ሲሚንቶዎችን ማስመጣት ቢጀምርም ዋጋው በአሁኑ ወቅት ከማሸቀብ አልፎ ጣሪያ መንካት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከውጪ ያስመጣው 150,000 ቶን ሲሚንቶ የጫነው የመጀመሪያ መርከብ ጅቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ሲሚንቶው
አዲስ አበባ እንደሚደርስና በኢትዮጵያ ያለውን የሲሚንቶ ችግር እንደሚቀርፍ አቶ ዚያድ ወልደገብርኤል በያዝነው ሳምንት በግዮን ሆቴል ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ጋር በደረገው ውይይት ላይ ገልፀው ነበር።
ሆኖም የሲሚንቶው ዋጋ አሁንም እያሻቀብ ነው።በአሁኑ ወቅት በመንግስት ስር ያለው ሙገር ሲሚንቶና መሶብ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሲሚንቶ ችግርን መቅረፍ ስላልቻለ ከውጪ ማስመጣቱ ላይ ትኩረት ማድረጉን አቶ ዚያድ ገልፀዋል።
ይሁንና ሲሚንቶው በአንዳንድ የመንግስት መገልበጫ መኪናዎች እየተጫኑ ለሲሚንቶ አከፋፋዮች እንደሚሸጡና የሲሚንቶ ቸርቻሪዎችም ለምሳሌ አንድ የፖርታላንድ ፖዞላና ሲሚንቶ (ፒፒሲ) እ.ኤ.ኤ በ2006 ላይ 80 ብር የነበረው ፤በ2009 መጨረሻ ላይ 155 ብር የነበረ ሲሆን ፤ አሁን ደግሞ ከፋብሪካው ሲወጣ
243ብር ሆኗል ።የገቢያው ዋጋ ደግሞ 400 ብር ደርሷል። ለዛውም በዚህ ዋጋ የማይገኝበት ጊዜ አለ ። ይህ ደግሞ የሲሚንቶው ሽያጭ የበርካታ ሰዎችን ኪስ በማደለብ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል ባይ ናቸው እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አገላለፅ።
ከዚህ ሌላ ሲሚንቶው ለአንዳንድ ባለስልጣኖች ቤት መሥሪያ እንደሚውልና ባለስልጣኖችም ያስገነቡትን ቤት በከፍተኛ ብር እየሸጡ በኪራይ ቤቶች ውስጥ እየተከራዩ እንደሚኖሩ ተጠቁሟል።ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 105 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኘው ሙገር ሲሚንቶ በአሁኑ ወቅት 777,766 ቶን ፒፒሲ ሲሚንቶ 89,000 ኦፒሲ ሲሚንቶ ሲያመርት በአጠቃላይ 845,000 ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው።
በዙም ተፈላጊነት ያልነበረውና ቶሎ የመፈረካከስ ባህሪ ያለው የወያኔ ንብረት የሆነው የመሶብ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያመርተው ምርት መሶብ ሲሚንቶ በፊት ተፈላጊነቱን እንዳላጣ ሁሉ አሁን ግን እሱንም ማግኘት እንዳልቻሉ አንዳንድ ኮንትራክተሮች በምሬት ይገልፃሉ።