መፍትሄው አንድ ብቻ ነው! በአንዱዓለም አራጌ
በዚህ በሠለጠነው ዘመን በኢኮኖሚ፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ከፍተኛ እመርታ በአስመዘገቡ አያሌ የዓለማችን አገሮች መሀከል በርካታ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ በጥቂት አፄዎች የጭቆና ቀንበር ሥር እየማቀቀ ይገኛል፡፡ ጭቆናው በጥቂቶቹ ላይ ደግሞ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ከጥቂት እጅግ የከፋ አፈና ከተንሰራፋባቸው አገሮች መካከል ደግሞ ግንባር ቀደሟ አዛውንቷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነች፡፡
ኢትዮጵያ በዘመናዊው ዓለም መካከል በመገኘቷ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መስጠቱ የግድ ቢልም መዘመኗ የቱ ጋ ነው? የሚለው ጥያቄ ግን ከፊት ለፊታችን ተጋርጦ በኢትዮጵያውያን የአዕምሮ ጎዳ ውስጥ ጎጆ የቀለሰ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንስ እውነት ሀገራችንን ከስም ባለፈ ለማዘመን የየራሳችን መላምት እና የመፍትሔ ሃሳቦች ይዘን ወደ አደባባይ መውጣታችን የት ድረስ ነው?
የኢትዮጵያችን ፖለቲካ በፀና ከታመመ አያሌ ዓመታት አልፈውታል፡፡ ዘመን ከፊታችን እየተጎመደ ሲያልፍ ደዌ የተፀናወተው ፖለቲካችን መፍትሔም ከመቅረብ በዚያው ፍጥነት እየራቀ፣ እየነጎደ ከአጠገባችን ይርቃል፡፡ ይህንን ጉዳይ ስናነሣ ቢያንስ የአለፉት 5ዐ ዓመታት የአገራችን የፖለቲካ መልካ-ምድር አዕምሮችንን መሙላቱ አይቀርም፡፡ ይች የሥልጣኔ ምኩራብ፣ የታሪክ ማማና የባህል ሰገነት የሆነች ሀገር ይህንን የፖለቲካ ስንክሳር ከላዩዋ የሚገፍ ትውልድ ማጣቷ ለምን ይሆን? እርግማን ወይንስ ከንጋት በፊት ያለ ድቅድቅ ጨለማ?
ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ስለማንጨነቅ ግን ከቶ አይደለም፡፡ በአለፉት 5ዐ እና 6ዐ ዓመታት ብቻ ብንወስድ እንደነገርማሜ ንዋይ አይነቶች የውጭውን ዓለም በእድገት መስፈንጠር ለመታዘብ የበቁ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለማዘመን የወጡትን ኮረብታ እናስታውሳለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይካሄድ የነበረው የዓለም የፖለቲካ ማዕበል ጉማጅ የነበረው : ከአስር ዓመታት ላላነሠ የተካሄደው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሠላማዊ ትግልንም እንዲሁ፡፡ በቁጭት እቶን የተበላ ትውልድ ምጥ ነበር፡፡ የደርግ ወደ ሥልጣን መምጣትና ተከትሎ የመጣው የኢህአፖን፣ መኢሶንና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ጭምር ያሳተፈው የታሪካችን ምዕራፍም እንዲሁ በተወሰነ መልኩ ተያያዥነት እንዳለው እንደረዳለን፡፡ ይህንን በመሠለው የታሪካችን ምዕራፍ የተፈጠረውን አይንን የሚያደነግዝ ጆሮን ጭው የሚያደርግ አሳዛኝ ክስተት እንዲህና እንዲያ ነው ብሎ ለመናገር በጣም ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን የተወሰነ ነገር ጠቁሞ ማለፍ ይገባል፡፡
ከዛ በፊት ሌሎች ጉዳዮችን እናንሳ፡፡ ንጉሳዊውን ሥርዓት ለመጣል በተማሪዎችን እንቅሰቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን አሻራ ያሳረፉ ወጣቶች ነፍጥ አንግበው ጫካ መግባታቸው፣ ያንንም ተከትሎ የኢትዮጵያችን ምድር ዝናብ ቢያጣም በወንድማማቾች ደም ሲጨቀይ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን በህይወት ለምስክርነት በቅተናል፡፡ እንደበቃ ባህታዊ ዱር ገደል ቤቴ ብለው ጫካ የገቡ ወጣቶች ምንአልባት ለገነገነው የኢትዮጵያችን የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ቢጤ ይዘው ይመጡ ይሆናል የሚለው ምኞትና ግምት አዘል ሃሳብ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን አዕምሮ መጠንሰሱ የሚጠበቅ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ አማላዩ የወያኔ/ኢህአዴግ የሬዲዬ ፕሮፓጋንዳ ሲጨመርበት ወደ እውነትነት እየተቀየረ ያለ ሕልም ይመስል ነበር፡፡ 1983 ዓመተ-ምህረት ገደማ፡፡
አንዳንዶች ይህ ህልም ወደ እውነትነት ይቀየራል ብለው በማሰብና የበኩላቸውን አስተዋፆ ለማበርከት በመሻት ኢህአዴግን መደገፍ ሲጀምሩ፣ ሌሎች ደግሞ በጣሊያን ጊዜ ብዙ አባቶች እንዳረጉት ከባለጊዜው ጋር መስሎ ለመገኘት በኢህአዴግ ጎራ ተፍ ተፍ ማለትን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አደረጉት፡፡ እምቢ ለእኔነቴ ብለው ጫካ እንደወረዱ አብዝተው የነገሩን ወያኔዎች በዋናነት በነርሱ እና ጥቂት ጋሻ ጃግሬዎቻቸው አለ የሚባለውን ሥልጣን ብቃት ኖረም አልኖረም ተቀራመቱት፡፡ እንዲህ ነው እንጂ ነፃ አውጭ! የጭቁን ሕዝብ አለኝታ! ሥልጣን መያዛቸውም ባልበዛ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ባልተሞረደ የጫካ ሥነ-ምግባርና አንደበት ተረት ተረት ማለቱ ከፋ እንጂ፡፡ ለእነርሱ አገርን የማልማት ቀላሉ የመጀመሪያ ተግባር ይህ ሆነ፡፡ የምንስ ባንዲራ ነው? ያንን ጨርቁን ተባልን ከሁሉ የከፋ የሀፍረት ካባ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲከናነነብ ግድ ሆነ፡፡ ባለጌ ልጅ በወላጆቹ ላይ ይጫወታል እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን አባቶች ለአንዳች ነገር ሳይሳሱ፣ ዘር ሳይቆጥሩ የተዋደቁለት ዳር-ድንበር ባለቤቶቹ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ባድማ ያሻው የሚገባበት ያሻው የሚወጣበት ያሻው ቆርሶ የሚወስደው ምድረ-በዳ ሆነ፡፡ ይህ የታሪክ ታላቅ ስላቅ ነው፡፡ እነ ቴዎድሮስ፣ ዬሀንስ፣ ሚኒሊክ፣ እነ አብዲሳአጋ እና እነ አሉላ አባ ነጋ ዘመናቸውንና ሕይወታቸውን በሙሉ የገበሩለት አገር በእነርሱ እግር እንካችሁ “አገራችንን” አስገንጥሉልን በሚሉ መሪ ተብዬዎች ተተኩ፡፡ እነዚህ ጀግኖች የሞቱላት ሀገር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅኝ ገዢ ተብላ በእነአቶ መለስ የሀሰት ድርሳን ተከተበላት፡፡ ይህንን ሁሉ ሲሉ የሚገድባቸው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ ፈሪሀ-ፈጣሪም ሆነ ፈሪሀ-ሕዝብ አልታየባቸውም፡፡ ሌላም ጥያቄ አክዬ ወርውሬ ልለፍ ለመሆኑ ይህንን መሠሉ ሥነ-ልቦና ከየት አመጡት? እሸቷን ቅመውና ውሃዋን ጠጥተው ያደጉበትን አገር ይህን ያክል ለመጥላት፣ ባንዲራዋን ለማርከስ፣ ከዚያም በላይ ዳር-ድንበሯን ለመቁረስና ለማስቆረስ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም የተፃፈውን ታሪኳን ለማጉዳፍ ምንድነ ነው የሚያተጋቸው? ምንስ ይሆን የሚገፋፋቸው? እነ አቶ መለስ ከኢትዮጵያ፣ ከሕዝቧ፣ ከጥቅሟ እና ከታሪኳ ጋር የተጣባቸው ጥላቻ እኛ የማውደም ተልኮ ከየት ነው የሚፈልቀው? ምን አልባት የልጅነት ሥነ-ልቦናቸው ቢጠና ወደ ምላሹ መቅረብ ይቻል ይሆን?
ከላይ ካነሳናቸው አንኳር የእነአቶ መለስ ተልኮዎች መካከል ምን አልባት የአንዳንዶቹ አባቶች ታሪክ በስፋት ከሚቆራኘው ከጣሊያን የዓምስት ዓመት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የመግዛት የቀን ቅዥት ጋር በአያሌው የተዛመደ ይመስላል፡፡ አገርን ከፋፍሎና አዳክሞ የመግዛት ሥልት ከሁነኛ የኢህአዴግ ኢትዮጵያን የማዳከሚያ ዘይቤዎች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ይህንን መሠሉን ሰይጣናዊ ባህሪያቸው ከምን እንደሚመነጭ መልስ መስጠት ከላይ ካነሳናቸው ጥያቄዎች አንፃር ሲታይ ይኸኛው ቀለል ያለ ይመስላል፡፡ ወትሮውንም ቢሆን እነ አቶ መለስ እንደሚሉት የሕዝብ ብሶት ሳይሆን በኢትዮጵያ እና በሕዝቧ ላይ ዛሬ የሚያካሂዷቸው ለአብነት የጠቅስናቸው የባጁ ዓለማዎቻቸውና እራሳቸውን ሥልጣን ላይ አውሎ የማሳደር ቅዠት ዘንድ እንደተወላዱ መናገር ይቻላል፡፡
ከላይ የተባለውን ሁሉ ስንል ሀገራችን ከወያኔ/ኢህአዴግ በፊት ገነት ነበረች አንዳች አይነት ችግርም ተጠናውቷት አያውቅም እያልን እንዳልሆነ መግቢያችን ላይ የከፈትነው የ5ዐ እና 6ዐ ዓመቱ የሀገራችን የፖለቲካ አውድ እማኝ ነው፡፡ ነገር ግን ዘመን እየተገመደ ሲስፈነጠር በአቶ መለስ ዘመን የሀገራችን የፖለቲካ አዙሪት ከድጡ ወደ ማጡ መውረዱ ለምን ይሆን ብሎ ጥያቄ ማንሳቱ ብዙ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም የኢተዮጵያን ክብር፣ ታሪክ፣ ባንዲራ እና ጥቅሞችዋን ቆሻሻ ላይ መጣል ገና ጠዋት ዓላማ ብለው ያነገቡት ዛሬም እየፈፀሙት ያለ የአደባባይ ሚስጥር በመሆኑ ነው፡፡ የነ አቶ መለስን ዘመን እንዲህ ብለን ብንገልፀውስ ፡-
ዘመኔን አየሁት ሌላ ዘመን ሲያየው ፣
የዘመን አተላ፣
የችጋር ኮረብታ፣
የጭቆና አውድማ፣
ብሎ ሲወርፈው፡፡
ይህኛው ዘመን ካለፈው እንዲሻል ስንሻ እየባሰ መምጣቱ፣ አምባገነን ገዢዎቻችን ከቀደምት ቢጤዎቸውን ይማራሉ ብለን ጤነኛና ተስፈኛ ምኞታችንን ስንሰንቅ የተገላቢጦች መሆኑ ለምን ይሆን? እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር እና እንደ ትውልድስ የሚጎድለንስ ምን ይሆን?
በውይይታችን መግቢያ ላይ እንዳወሳነው እንደነ ገርማሜ ንዋይ አይነቶቹ ከሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል በዘመናቸው በተመሳሳይ ቁጭት አዘል የቁዘማ ባህር ውስጥ ሰምጠው እንደነበር አስታዋሽ አያሻንም፡፡ ዛሬስ በህይወት አለን ብለን የምናስበው እኛ በማያባራ ሀዘንና ረጅም የመከራ ሌሊት ውስጥ ማለፋችን ምን ያሰኛል? መቋጫውስ መቼ እና እንዴት ነው?
ቀደም ሲል ወደ አነሳሁት ሃሳብ ላምራ፡፡ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ባነገቡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ዘንድ የተፈጠረው የፖለቲካ ቁርሾ በ196ዐዎቹ ውስጥ ለምን ተፈጠረ? እጅግ በከፋ ደም መቃባትስ ለምን ተደመደመ? መንበረ ሥልጣኑ ላይ አሁን ተፈናጠው የሚገኙትስ ለምን ከዚህ ክፉ ዘመን በመማር ፈንታ እጅግ መሰሪ፣ መርዘኛ እና አፋኝ ሥርዓት ማራመድን መረጡ? ሕዝቡስ ጥቂቶች በሁለንተናው ሲዘባበቱበት፣ እንደ አንጡራ ሀብታቸው ሲቆጥሩትና በግዞት ሲነዱት አርምሞን ለምን መረጠ? ከላይ በተከታታይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች መልስ በዋናነነት ለዘመናት ተንሰራፈቶ ከባጀው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህላችን ጋር የተቆራኘ አንዳች ነገር እንዳለው መናገር ይቻላል፡፡ በተለያየ ወቅት ከሚቀያየረው የዓለማችን ፖለቲካዊ መስተጋብር ጋር ተዛማጅነት ሊኖረው እንደሚችልም መናገር ይቻላል፡፡
ከአምባገነን መሪዎቻችን ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ከተነሱት የትኩረት አቅጣጫዎች በተጨማሪ የልጅነት ሥነ-ልቦናቸውን በደንበኛው መዳሰስ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢሉ ወደ መሪነት የሚወጡበት መሰላል እና የመሪነት እርካቡን መርገጥ ሲጀምሩ በሕዝብ፣ በታሪክና በሀገር ክብርና ጥቅም ላይ የሚሰሩት ደባም ሆነ መልካም ነገር ምን አልባት በአደጉበት አካባቢ እና ቤተሠባቸው ውስጥ ሲያድጉ የሰሙት፣ አምነው እና እውነት ነው ብለው በተቀበሉት ነገር ላይ ተመስርቶ ጥላቻም ሆነ አክብሮት የተላበሰ አስተሳሰብ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ገና በማለዳ ስብእናቸው ሲገነባ የስብእናቸው ምሶሶ ሆኖ ይወጣል፡፡ ለምሳሌ አንድ በልጅነቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍ በመፃፍት ያነበበ፣ በፊልም ያየ ልጅ በደፈናው ጣሊያንን እና ጣሊያናውያን የዘመናችንንም ጣሊያኖች ጨምሮ ግፉ ሲፈፀም ባይኖሩም አምርሮ ሊጠላ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ትክክለኛ አስተያየት ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ከሌላ ጎን እንየው፡፡ በጣሊያን ዘመን ብዙ ኢትዮጵያውያን ባንዳዎች እንደነበሩ ታሪክ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ከድል በኋላ እነዚህን አባቶች እና እናቶች ንጉሱ እንዳልኮነኗቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በህዝቡ ዘንድ ተመሳሳይ አቀባበል እንደማይጠብቃቸው እንዳውም ባንዳዎች እየተባሉ የመሠደብ እጣፋንታ እንደሚጠብቃቸው ልጆቻቸውም የባንዳ ልጆች እየተባሉ በየደረሱበት ሊሰደቡ እና ሊረገሙ ይችላሉ፡፡ በዘመኑ ዘይቤ፡፡ የሁለቱ ልጆች ሥነ-ልቦና አንድ አይነት እንዲሆን አንጠብቅም፡፡ ከአስተዳደጋቸውና ከታሪካቸው አንፃር ሥልጣን ላይም ሲመጡ የመጀመሪያው ጣሊያንን ሁለተኛው ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሊሰሩ እንደሚችሉ መገመት ብዙም አያዳግትም፡፡
ቀዳሚ አድርገን ወደ አስቀመጥነው ጥያቄ እናምራ፡፡ በታሪካችን አልፎ አልፎም ቢሆን የአንዳንድ መሪዎቻችን ብልህነት እናስታውሳለን፡፡ እንደ አቶ መለስ አይነቱን ከብልህነት የራቀ ጮሌነት ማለቴ ግን ፈጽሞ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በዩሀንስ እና በሚኒሊክ መካከል የነበረው ግንኙነት የፖለቲካ ጥበብ ምን እንደሚመስል የመሪዎችንንም ደረጃ የምናይበት መስታወት ሊሆነን ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ነገሮችን ወደ ኋላ እና ወደፊት እየሄድን መጥቀስ ይቻለን ይሆናል፡፡ የታሪካችንን ትልቁን ስፍራ የሚይዘው ግን የችግር አፈታት ባህላችን ጉልበትን ተንተርሶ የሚመጣ ሆኖ እናገኘዋልን፡፡ በታሪክ ካለንበት ዘመን ተነስተን የኋልዩሽ በአይነ- ልቦናችን ብንገሰግስ የሀገራችን ገዢዎችና ገዢ ለመሆን ራሳቸውን ያጩ አጤዎች በየዘመናቱ በየኮረብታው እና በየሸለቆው ደሀውን ኢትዮጵያዊ አሰልፈው ያጫረሱባቸውን ዘመናት ልክ እንደ ፊልም ይታዩናል፡፡ በአይዲኦሎጅ ልዩነት ምክንያትም አልነበረም፡፡ ይልቅስ የአምባገነንነት ምእሳቸውን በሕዝብ ጫንቃ ላይ በመሆን ለመቋደስ እንጅ፡፡ በጓድ መለስ እና በጓድ መንግስቱ መካከል የትኛውን የአይዲኦሎጅ ልዩነት ማንሳት ይቻለናል? ስድቦቻቸውና የአነጎገረ ዘይቤዎቻቸው አነጋገሮቻቸውም ሳይቀር መመሳሰል ከጀመሩ ሰነባበቱ፡፡ ልዩነት አለ ከተባለ ቢባል እንኳን በጥቂቱ ነው፡፡ ጓድ መንግሥቱ ኢምፔሪያሊዝም ሲሉ፣ ጓድ መለስ አሻሽለውት ኒዎሊብራሊዝም ማለታቸው ብቻ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በቅርብ እንዳየነውና እንደሰማነው የጓድ መንግሥቱን ተግባር ብቻ ሳይሆን ስድቦቻቸውንም በአደባባይ እየተዋሱ ነው ፡፡
አምባገነኖች በሚፈበርኩት ጦርነት የኢትዮ-ኤርትራን ለአብነት ማንሳት ይቻላል የሚማገደው፣ በጦርነት ጊዜ የሚዘመርለት፣ ከጦርነት በፊትና ማግስት ግን የሰይፋቸው ሰለባ የሚሆነው የሕዝብ ልጅ ግን እንደረጋ ውቅያኖስ ሁሉን ነገር በጽሞና ይከታተላል፡፡ ያው በገሌ ነው ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ በጦርነት ወቅትም የጠላት ጥይት ሠለባ ጦርነት በሌለበት ወቅትም የአምባገነኖች ሰይፍ ሰለባ፡፡ እስከመቼ ይቀጥላል? በታሪካችን አምባገነኖችን ለምን ብሎ የመጠቅ ባህል እምብዛም የለንም፡፡ ይህም ጫንቃችን ለአምባገነኖች የተመቸ ኮርቻ እንዲሆን አድርጎታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህን በመሠለው ሥነ-ልቦና ላይ የእነጓድ መለስ የዘር መርዝ ሲነሰነስበት ጥርጣሬን ማንገሱ አይቀሬ ነው፡፡ አምባገነኖችን መቀየር ይቻላል ብሎ እምብዛም እምነት በማያድርበትና የጥርጣሬ ድባብ በነገሠበት ሁኔታ እንዴት በአንድነት ለነፃነት መብቃት ይቻላል? ሌላው ከጥንት ጀምሮ በአምባገነኖቻችን ላይ ቅኔ መቀኘትና በግጥም መጎንተል የተለመደ ቢሆንም ከዚያ አልፎ እያንዳንዱ ዜጋ በአመዛኙ ሌሎችን ሳይጠበቅ የመታገል ተነሳሽነት አያሳይም፡፡ እራሳችንን እንደ አቅመ ቢስ፣ ረዳት አልባ፣ ብቸኛ እና ሀቀኛ ከማድረግ ዘለን ሌላውን ዜጋ ምንም አስተዋፆ የማያደርግ፣ እምነት የማይጣልበት እና ሌላም ሌላም በማለት በመካከላችን አጉራ አስቀምጠን ላንገናኝ ተማምለን ለአምባገነኖች ይባስ ጎብጠን እንገኛለን፡፡ በእንዲህ አየነት ምቹ ጀርባ ላይ ወያኔ ሽህ ዓመት ለመፈናጠጥ ነጋሪት ቢያስጎስም ለምን እንገረማለን? ስንቶች ኢትዮጵያውያን ነን ይህን ረጅም የመከራ ሌሊት ለማሳጠር ሌላውን ሳንጠብቅ የህሊና እዳችንን ለማወራረድ በመትጋት ላይ የምንገኘው?
ስንቱስ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የሀገርን ጉዳይ አስቀድሞ ልዩነቱን በማጥበብ ኃይሉን ለማሰባሰብ እና ትግሉን ዳር ለማድረስ እንቅልፍ አጥቶ የሚሠራው? ስንቱስ ምሁር ነው መላምት ከመሠንዘር እና የሌሎችን ገድል ከማውራት በዘለለ ለሀገሩ እና ለሕዝቡ አለሁ የሚለው ? በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ የሚገኘው ኢትዮጵያዊስ የነጓድ መለስን የማማለያ ሙልሙል ከመግመጥ ወጥቶ የባሰ አታምጣ ከማለት ባሻገር ለማንነቱ፣ እራሱን በህይወት ለማኖር፣ ለነፃነቱ እና ለህፃናት ልጆቹስ ተስፋ እምቢ ብሎ የሚቆመው መቼ ነው? እኛ የእነዚህን ጥያቄዎች ውል ስንፈልግ እነጓድ መለስ ሌሎች ጥያቄዎችን ሊጨምሩልን ደፋ ቀና እንደሚሉ ማሰብ ይቻላል፡፡ ደግሞስ በውሸት ቀሰው በውሸት የቆረቡ ሰዎች ምን የሚሉት ያጣሉ የትኛውስ የሞራል ህግ ግድ ይላቸውና?
የሀገራችን የፖለቲካ ባህር ለአለፉት 6ዐ ዓመታት የደፈረሰ ነው፡፡ ለአለፈት 2ዐ ዓመታት ደግሞ ድፍርሱ ፖለቲካችን ወደ ጭቃነት እየተቀየረ ስለመሆኑ ምስክር አያሻውም፡፡ ከሀገር ሉዓላዊነት እስከ ታሪካችን፣ ከባንዲራችን እስከ እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር ያለን ደረጃ መቀመቅ መውረድ በፀፀትም ቢሆን እንገነዘባለን፡፡ አንዳንዶቻችን እንደዚህ ዘመን ትውልድ አባልነታችን ያለፈውን መለወጥ፣ ዛሬን የሰውነት ደረጀችን በጠበቀ ሁኔታ መኖርና ነገንም ላልተወለዱ ልጆቻችን መልክ አስይዞ ለማውረስ ከቁጥጥራችን እየወጣ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ በሌላ ወገን ተረኞቹ አምባገነኖች የአለፉት 2ዐ ዓመታት የአንድ ጀምበር ያህል አጥረውባቸዋል፡፡ ስንራብ መጥገባችንን ይነግሩናል፡፡ ስንታረዝ ደራርበን መጎናፀፋችን ይታያቸዋል፡፡ ሀገራችን ከሀገሮች ተርታ በሁሉም መስኮች ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በማይታመን ፍጥነት እየወጣች ወደ ግርጌ ስትወረወር ሀገራችሁ ተሞሸረች አማራች ይሉናል፡፡ በአጭሩ ጥጋባቸው አይናቸውን ጋርዷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲረግጡት የሚደቅን ቅጠል ያህል ቆጥረውታል፡፡ ከህግና ከአመክንዮ ውጭ በማን አለብኝነት ሕዝባችንን በንግድ ድርጅቶቻቸው እየገፈፉ እርቃኑን አስቀርተውታል፡፡ ይህንን ርቃኑን የቀረ ደሀ ሕዝብ መልሰው ፋናን በመሰሉ “መገናኛ ብዙሃን” የወርቅ መጎናፀፊያ እንደደረበ ሊያሳምኑት ቀን ከሌት ያደነቁሩታል፡፡
አላግባብ ሥልጣን ላይ የባጀ፣ በንፁሃን ደም የጨቀየ አመራርና በሌሎች ረሀብና ሞት የደለበ ጥሪት ባለቤት የሆነ ስብስብ ከዚህ ውጭ ምን እንዲል፤ ምንስ እንዲሰራ ይጠበቃል? በነገራችን ላይ ጓድ መለስ ንብረታቸውን አስመዘገቡ መባሉን በቴሌቪዥናቸው ሰማን፤ ስንት እንዳስመዘገቡ ግን አልተነገረንም፡፡ ምክንያቱም መረጃዎች ከየቦታው እንዳይወጡ በመስጋት እንደሚሆን ብዙም የሚያወላዳ አይሆንም፡፡
መፍትሔው ስለደፈረሰው ፖለቲካ እያወሩ ፈጣሪ ባመጣው ይመልሰው ማለት አይደለም፡፡ መፍትሔው እርስ በእርሳችን ስንወጋገዝ መኖርም አይደለም፡፡ መፍትሔው የእነጓድ መለስን አረመኔነት ሲያወሱ መኖር አይደለም፡፡ መፍትሔው ልዩነቶቻችን በማጥበብ፤ ጠብታዎች ባህር እዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ መፍትሔው እጅን አጣምሮ ጥቂቶች ታምር እንዲሰሩ መጠበቅም አይደለም፡፡ መፍትሔው ከያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ሌላውን ሳንጠበቅ መወጣት ነው፡፡ አምባገነኖችንም መካብ ዙፋናቸውን መሸከም መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔው አምባገነኖችን ከጫንቃችን ወደ መሬት ማውረድ ነው፡፡ የነጓድ መለስን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱትንና እያደረሱ ያሉትን ታሪካዊ በደልና አፈና ስናይ ብዙ ነገር ከእኛ መጉደሉን እናያለን፡፡ የእኛ ድካም የእነርሱ ጥንካሬ ነውና፡፡ የእኛ ፍርሃት የእነርሱ ማንአለብኘነት መሠረት ነውና፡፡
ከዚህ በኋላ ብዙ ማኖ ነክተዋል፡፡ ብዙዎችን ገድለዋል ወይንም አስገድለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እግር ከወርች እያሰሩ ድምፁን ነጥቀዋል፡፡ በድህነት ውቅያኖስ ውስጥ የራሳቸውን የብልጽግና ደሴት ፈጥረዋል፡፡ ይኸ እና ሌሎች ሕልቆ መሳፍርት የሌላቸው ወንጀሎቻቸው ፍፁም ፈሪዎች አድርገዋቸዋል፡፡ ፈሪ ደግሞ ይህን ሰሞን በቴሌቪዥን እንዳዬነው ዘራፍ ማለቱና መወራጨቱ አይቀርም፡፡ ፈሪ ሁሌም በማስፈራራት አልያም ሁሌም የማማለያ ዳቦ በማስገመጥ ሥልጣን ላይ ተንሰራፍቶ ለመዝለቅ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ መፍትሔው አንድ ብቻ ነው፡፡ ቅድሚያ ለሀገር ጉዳይ በመስጠት፡፡ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ወገብን አስሮ መታገል፡፡ ዛሬን እጅግ ለከበረ ነገር ያውሉት፡- ለነፃነት ትግል፡፡