የሰማዕታት ቀን በደቡብ አውስትራሊያ ተከበረ
“ ሁላችንም ባንድነት ግንባር ፈጥረን ካልታገነው አገራችንንና ወገናችንን ከወያኔ የግፍ አገዛዝ ነፃ ልናወጣ አንችልም!” (የቀድሞው የሕወሃት የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገ/መድህን አርዓያ)
የደቡብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ በሆነችው አድላይድ የሚኖሩ ኢትዪጵያውያን በ1997 ዓ.ም በአገራችን የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በአምባገነኑ የወያኔ መንግስት በግፍ የተጨፈጨፉትን ወገኖቻችንን 5ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ባለፈው ቅዳሜ ታሕሳስ 2/2003 ዓ.ም አከበሩ።
ለዝግጅቱ ታዳሚዎች ምስጋናቸውን በማቅረብ የበዓሉን አስተባባሪ አካል ወክለው የዕለቱን መርሃ ግብር በንግግር የከፈቱት አቶ መኮንን ምስጋናው አክለውም “ባለንበት ዘመን የእውነትን ታላቅነት የሚያምኑ በርካቶች ቢኖሩም ለዕውነት የሚቆሙት፤ አልፎ ተርፎም መስዋዕትነት የሚከፍሉት ጥቂቶች ናቸው። እኛም ዛሬ የተሰባሰብነው ከ80 ሚልዮን የአገራችን ሕዝብ ጋር ሲነፃፀሩ ከቁጥር የማይገቡ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችንን ለማሰብ ነው። እነዚህ ሰዎች ትናንት አፈር ቢለብሱም ስማቸውና ታሪካቸው ግን ምንጊዜም ህያው ነው። በሰው ልጆች ላይ የሚደርስን ግፍና በደል በራስ ላይ እንደደረሰ ቆጥሮ መቃወምና መኮነን ደግሞ በፈጣሪም ሆነ በሰው ተቀባይነት ያለው ታላቅ ነገር ነው።” ብለዋል።
በስነስርዓቱ ላይ በምርጫውን ተከትሎ የነበረውን እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ለማስታወስ ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀ የፊልምና የፎቶግራፍ ቅንብር፤ ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች የቀረበ ሲሆን፤ ይህም ብዙዎችን በዕንባ ያራጨ ነበር።
ወያኔ በወቅቱ በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የወሰደው የሃይል እርምጃ አግባብ እንዳልሆነ እራሱ ያቋቋመው የአጣሪ ኮሚሽን አባላት እንደመሰከሩበት ያስታወሱት አቶ መኮንን ይህንን አስመልክተው ሲናገሩ “በውነቱ በዚህ አጋጣሚ ለእውነት ሲሉ ከተገፋው ወገናቸው ጎን በመቆም የሚታወቁትንና፤ ለእውነት ሲሉም የሞቀ ቤትና ንብረታቸውን ጥለው ለስደት የተዳረጉትን የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት የነበሩትን የአጣሪ ኮሚሽኑን ሊቀመንበር አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል እንዲሁም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት የነበሩትን ም/ሊቀመንበሩ ዳኛ ወልደ-ሚካዔል መሸሻን ላመሰግናቸው እወዳለሁ። የዘመናችን ታላቅ የእውነት አርበኞች ናቸውና!” በማለት ለነዚህ ውድ ኢትዪጵያውያን ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት ገልፀዋል።
ምንም እንኳን በዝግጅቱ ላይ በአካል መገኘት ባይችሉም በክብር እንግድነት የተጋበዙት የሕወሃት የቀድሞ የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገብረመድህን አርዓያ ከሚኖሩበት ከምዕራብ አውስትራሊያ በስልክ ባስተላለፉት መልዕክትም “ዛሬ የምናከብረው የሰማዕታት ቀን በኢትዪጵያ ታሪክ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ዘላለም የሚታወስ ብቻ ሳይሆን፤ እኛም ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የከፈሉ ወገኖቻችን ፈለግ ተከትለን አገራችን ከወደቀችበት የወያኔ ፋሺሽታዊ አገዛዝ ለማላቀቅ ግንባር ፈጥረን ለመታገል ቃል የምንገባበት መሆን ይኖርበታል።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የወያኔ ጀሌዎች በየቤተክርስቲያኑ፤ በየስፖርት ሜዳው፤ በሌላም ሕዝብ በሚሰባሰብበት መድረክ ኢትዪጵያን አንድሆነው እንዳይቆሙ ከወያኔ መሪዎች በሚሰጣቸው ቀጭን ትዕዛዝ አንዳንድ የዋሃንንና ለተራ ጥቅም ያደሩ ኢትዪጵያውያንን ከጎናቸው እንዲቆሙ በማግባባት በስደት የሚኖረውን ሕዝብ እያጣሉና እየለያዩን ናቸው” ያሉት አቶ ገ/መድሕን አክለው እንደገለፁት አንዱ ካንዱ መለያየትና ማጋጨት ደግሞ የወያኔ አዲስ ስትራቴጂ ሳይሆን ቀድሞ በረሃ ሳለ ጀምሮ ይገለገልበት የነበረ ስልት እንደሆነ የራሳቸውን የበረሃ ተሞክሮ ድርጅቱ አሁን እያራመደው ከሚገኘውን ጎጠኛ ስልት ጋር በማያያዝ ተንትነው በማስረዳት፤ ሕብረተሰቡ በአንድነት ጥላ ስር እንዳይሰባሰብ እየተሸረበበት የሚገኘውን ይህንን ተንኮል ተረድቶ ሕብረቱን ለማጠናከር ይተጋ ዘንድ አሳስበዋል።
“አምላክ የፈጠረውን ነፍስ በማናለብኝነት ከማጥፋት የበለጠ ሃጢያትም ሆነ ወንጀል የለም” በማለት አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩ አንድ ተሳታፊ ሲናገሩም፤- “የዛሬ 5 ዓመት እነዚህ ወገኖቻችን ሲጨፈጨፉ በዝች ከተማ የምንኖር ኢትዪጵያውያን ባንድነት “ሆ!” ብለን በመነሳትና አደባባይ በመውጣት ይህንን ዘግናኝ ተግባር በመቃወምና በመኮነን ድምፃችንን አሰምተናል። ይህንኑ ሃዘናችችን ለመግለጽም ለሟች ቤተሰቦች በርካታ ገንዘብ በማሰባብሰብ ወደ አገር ቤት በመላክ “የልሳነ ሕዝብ” ጋዜጣና መፅሄት ባልደረባ በነበረው በጋዜጠኛ ታዬ በላቸው በኩል ለተጎዱት ወገኖቻችን ደርሶ ከነርሱ በቀጥታ የምስጋና መልዕክት ሁሉ ተልኮልን ነበር። ከዚያ በኋላ ግን እነዚህ ሰዎች የት እንደወደቁና በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንኳን ጠይቀን አናውቅም። ስለዚህ ያኔ የጀመርነውን ሰብዓዊ ርዳታ አሁንም አጠናክረን ልንቀጥልበት ይገባል።” ስሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ይህን ሃሳብ በመንተራስ አስተያየት የሰጡ ሌላ ግለሰብም፤ እርዳታው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን አንድ ላይ ሆኖ የሟቾቹን ቤተሰብ ስፖንሰር በመሆን ወደዚህ አገር እንዲመጡ መተባበርንም ቢያካትት መልካም እንደሆነ ገልጸው ይኸው ሃሳባቸው በዕለቱ ተሳታፊዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።
በፕሮግራሙ ላይ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል ያነጋገርኳቸው አንድ አባት አስተያየታቸውን ሲያካፍሉኝ
“አባት፤ እናት፤ አያት፤ ቅድመ-አያቶቻችን ለዕውነት ተፈጥረው፤ ለእውነት ኖረው፤ ለእውነት ሲሉ ክቡር የሆነው ሕይወታቸውን ሁሉ መስዋዕት በማድረግ እኛ እስከተፈጠርንበት ዘመን ድረስ ተከብራ የኖረችውን አገራችን ጠብቀውልን ቆይተዋል። ሌላው ቢቀር የዛሬ 30ና 40 ዓመት በየትኛውም አለም አንድ ኢትዪጵያዊ ማየት ትልቅና ብርቅ ነገር ነበር። ዛሬ ግን የአበሻ ልጅ ጎጆ ባይቀልስ እንኳን ሜዳ ላይ ወድቆ የማይገኝበት የምድር አካል የለም። እስኪ ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ? ይህ ሁሉ የሆነው እውነት አሁን በስደት የምንኖርበት አገር ከተፈጠርንባት ኢትዪጵያችን በልጦ ነውን? … የራሳቸውን ድሎት በማሰብ ብቻ “አዎን!” የሚሉ ብዙዎች እንዳሉ መጠራጠር ብቻ ሳይሆን አምናለሁ። ነገር ግን ይህ ሁሉ አበሳ የመጣብን ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአገራችን ላይ የተፈራረቁባት አምባገንን መንግስታት ባደረሱብንና እያደረሱብን ባለው በደል ነው። ስለዚህ የምንወዳት አገራችን ያለኛ ማንም እንደሌላት ከግምት ውስጥ አስገብተን እነዚህን የጥፋት መልዕክተኞች አስወግደን አገራችንን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርብናል።” ብለውኛል። በመጨረሻም የዕለቱ ጠቅላላ ዝግጅቱ ለሟች ወገኖቻችን በተደረገ ታላቅ የጸሎት ስነስርዓት ተጠናቋል።
(ቅዱስ-ሃብት በላቸው ከአድላይድ/አውስትራሊያ)