ድክመቶቻችንን የሚቀሰቅሱ ድክመቶች በዋልተንጉስ ዳርጌ

በዶስቶዬቭስኪይ የካራማዞቭ ወንድማማቾች ላይ በደንብ ጎልተው ያልወጡ፣ ሆኖም ግን በጠንካራ ባህሪያቸው አስደናቂ ስለሆኑ ስለ ሁለት ገጸባህሪያት እናነባለን፡፡ አንደኛው ወጣቱ የቲዎሎጂ ተማሪ (እና ሶሻሊስቱ) ራኪቲን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አዛውንቱ አሪስቶክራት (እና ሊበራሉ) ሚዩሶቭ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት ግለሰቦችን እንደዋዛ ለቃኛቸው ሰው ምንም የሚጋሩት ባህሪያት የሏቸውም፡፡ አንደኛው መንፈሳዊ ነው፣ ሌላው አለማዊ ነው፤ አንደኛው ድሀ ነው፣ ሌላው ባለጸጋ ነው፤ አንደኛው የተማረ ነው፣ ሌላው እምብዛም አልተማረም፡፡ አንደኛው በእርግጥ ብሩህ አእምሮ አለው፣ ሌላው ደግሞ የለውም፡፡ ሆኖም ግን ፍለጋቸውን በትዕግስት የተከተለ ሰው ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ልዪነቶች ውጫቂና የመልክ ልዩነቶች ብቻ እንደሆኑ ይረዳል፡፡
ከሚያመሳስሏቸው ጥልቅ ስሜቶች አንዱ፣ በሁለቱም ሰዎች ልብ ውስጥ ታላቅ ቁጣና ጥላቻ በቀላሉ ሊቀሰቀሱ መቻላቸው ነው፡፡ ራኪቲንን የአሌክሴይ ጥንካሬ፣ ይህም፣ ቅንነቱ፣ ንጽህናው፣ ፍቅሩ ያስቆጡታል፡፡ የሱ ልብ እነዚህን ስሜቶች መስጠትም ይሁን መቀበል አይችልም፡፡ እናም፣ ወደ አሌክሴይ በቀረበ ቁጥር በውስጡ እንደ አሸን የሚፈሉ ስድቦችና እርግማኖች፣ ነፍሱን ጠስቀው የያዙ እስኪመስሉ ድረስ ይጎርፋሉ፡፡ ሚዩሶቭን ደግሞ የፊዮዶር ካራማዞቭ ድክመት፣ ይህም፣ ብልግናው፣ ወራዳነቱ፣ ክብር ማጣቱ፣ ግልጽነቱ፣ መሳለቂያ መሆኑ ያስቆጡታል፡፡ እነዚህ ድክመቶች በሱም ውስጥ ስላሉ፣ ሆኖም ግን ስለሚጸየፋቸውና ዘወትር በታላቅ ጥንቃቄ ሊያምቃቸው ስለሚጥር፡፡ እናም፣ በውስጡ የሚቀሰቀሰው መንገሽገሽና ረዳት የለሽነት፣ ምንም ነገር ለማሰብም ይሁን ለማድረግ አቅም ያሳጣዋል፡፡

መልካም ሰው ባለመብዛቱም ይሁን፣ ወይንም ደግሞ በተፈጥሯቸው ውስብስብ ስለሆኑ፣ እንደራኪቲን ያሉትን ባህሪያት በቀላሉ መለየት ያስቸግር ይሆናል፡፡ እንደ ሚዩሶቭ ያሉት ባህሪያት ግን የተገለጡ መጻሕፍት ናቸው፡፡ በባህሪያቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች እንደአፈር በሞሉባት አለም፣ የነሱ ስሜት በቀላሉ ሲቆሰቆስና ሲታመስ፣ እነሱም ሲነዱና ሲከስሉ፣ ውድና አጭር እድሜያቸውን ያገባድዳሉ፣ በሰው ግራ እንደተጋቡ፣ ሰውም በነሱ ግራ እንደተጋባ፡፡

ያለጥርጥር በአገራችን የጎሳ ፖለቲካ የተቀፈቀፈበትና በየስፍራው እየፈላበት ያለው ዋናው ምክንያት በስልጣን ላይ ካሉት የሚበዙቱ በባህሪያቸው እንደ ሚዩሶቭ በመሆናቸው ነው፡፡ በርግጥ በአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ መንግስት የነበሩ ጥቂት ደካሞች የነዚህን ሰዎች ደካማ ስሜት በእጅጉ ጎድተዋል፡፡ እነሱም የችግሩን እውነተኛ ስርና መሰረት ዘልቀው መፈተሽ ሲገባቸው፣ በብዙ ቁጣ፣ በብዙ ምሬት፣ በብዙ በቀል፣ በብዙ ንቀት፣ በብዙ ስድብ፣ በብዙ ኩራት፣ ካልቆመ ነገር ጋር ሲታገሉ ብዙ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ስለዚህም ይመስለኛል፣ የቀደመውን ስርአት የሚያስታውሳቸው የሚመስላቸውን ሁሉ ማፈራረስና መልሰው እንደ አዲስ ማነጽ የወደዱት፡፡

የሚገርመው ነገር ግን፣ ይህ በሽታ በእነሱ ላይ ብቻ አለመገታቱ ነው፡፡ እውነተኛ ሆኖ ራሱን ለመመርመር ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ በቀላሉ መገንዘብ የሚችለው ነገር ቢኖር፣ ከኛ የምንበዛው በጎሰኝነት በሽታ መለከፋችንን ነው፡፡ ምናልባትም ከምናውቀውና ከምንገምተው በላይ፡፡ እርግጥ ነው፣ የጎሳ ፖለቲካን ባለ ሀይላችን ሁሉ እንጸየፈዋለን፡፡ ብዙ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እናወራለን፣ ወይንም እንጽፋለን፡፡ ይሄ ግን ሚዩሶቫዊ ነው፡፡ መራራው እውነት፣ የህውሀቶች ድክመት፣ ድክመታችንን በእጅጉ ቀስቅሶታል፡፡ ስለዚህም፣ ከመቸውም ጊዜ በላይ፣ ለ“አማራው”ና ለ“ኦሮሞው” ተቆረቆርን ባዮች፣ በታላቅ ምሬትና ስድብ እየጻፉ፣ በእነሱ አስተሳሰብ “ሌላ” ያሉትን ጎሳ በጀማ እየተቹ፣ እየነቀፉና እየዘለፉ፣ ያልተመዘነችን ቀልብ ባደባባይ በነገር የሚያስቀድሙ ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡ በመሰረቱ በእርግጥ “አማራ” ወይንም “ኦሮሞ” የሚባል ነገር ካለ፣ የህውሀቶች ፖለቲካ በራሱ ተነቃፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ሆኖም ግን አንድ ቋንቋ ሊወለድ፣ ሊያድግ፣ ሊለወጥና ሊሞት እንደሚችል ካመንን፣ ለሰዎች አብሮ መኖር፣ አብሮ ለመነሳታቸውም ይሁን ለመውደቃቸው፣ ብቸኛው አሳሪ ምክንያት እሱ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን መሰረታዊና ነጠላ እውነት ሊያረጋግጥም ይሁን ሊያስተባብል የሚችል አንድም ምሁር አያስፈልገንም፡፡ ቋንቋ ብቻውን አንድ ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ሊለያይም አይችልም፡፡ ለዚህ ነው፣ የጎሳ ፖለቲካ በባህሪው ሚዩሶቫዊ ነው ብዬ የማምነው፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ስናገር የማላውቀውን፣ ያልኖርኩትን፣ ወይንም በአይኖቼ ያላየሁትን አልናገርም፡፡ ከአገር ቤት እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ (በሰላሳ አመቴ)፣ በአንድ ቦታ ላይ ከአምስት አመት በላይ አልኖርኩም፡፡ ከወለጋ፣ ከትግራይና ከጎንደር በስተቀር ያልኖርኩበት የአገሪቱ ክፍል የለም፡፡ የልጅነት ወራቶቼን ያሳለፍኩት በደብረማርቆስ፣ በነጌሌ ቦረናና በኮምቦልቻ ነበር፡፡ ፈረስ መጋለብ የተማርኩት በዳገታማዋ አንቻሮ ጠባባብ መስኮች፣ በገርቢና በአስረጅ፣ እንዲሁም በገዳም ሰፈር ሸለቆዎች ውስጥ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የጨረስኩት በነጌሌ ቦረና አፈራማ ትምህርት ቤት ውስጥ፣ የሚበዛውን ጊዜ በባዶ እግሬ እየተመላለስኩ ነበር፤ከቀበሌ በአሳር በመከራ የሚገዙት ሸራ ጫማዎቼ ከሶስት ወራት የሚበልጥ እድሜ ኖሯቸው አያውቅም፣ ሊሞት ከማይችል የእግር ኳስ ፍቅር የተነሳ፡፡ ለድፍን አራት ወራት የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ የዘመትኩበት ቦታ፣ ከዛን ጊዜ በፊት ማንም ሰው አስተምሮባት የማያውቅ፣ ከገናሌ መንደር ጥቂት ኪሎሜትር ርቃ፣ ብቻዋን በደንና በቋጥኝ ተከባ በምትገኝ፣ መዳ ድኑን የምትባል ገጠር ውስጥ ነበር፡፡ ሕዝቡ ትምህርት እንዳይማሩ በብርቱ ሲያሳምጽብኝና ሲያስፈራራኝ የነበረ የጎበዝ አለቃ፣ በመጨረሻ ልጁን ሊድርልኝ እየለመነኝ፣ መንደሯን ለቅቄ እንዳልሄድ በብዙ ተማጸነኝ፡፡ እኔም ብሆን፣ እንደዛ ሕዝብ ያለ የዋህና ለጋስ ህዝብ እስከዛሬ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በየቀኑ ያመጡልን የነበረው ወተትና ቅቤ ተጠራቅሞ ከመበላሸቱ የተነሳ፣ ተራ በተራ እንዲያመጡልን ፕሮግራም ያስኩላቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር የያዘኝ፣ በአስራ ስድስት አመቴ ሲሆን፣ ጎረቤቴ ከነበረች የሶማሌ ወጣት ጋር ነበር፡፡ እናቷም እስከዛሬ ድረስ የቤተሰቦቼ የልብ ወዳጅ ናት፡፡ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ አንድም ቀን ባይተዋርነት ተሰምቶኝ፣ አንድም ቀን የሌላው ውጫዊ ማንነት ረብሾኝ አያውቅም፡፡ አሁን እንደዚያ ያለው ህይወት አይታሰብም፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ወደ አደግኩባት ከተማ ብመለስ፣ እሷ ለኔ፣ እኔም ለሷ ፍጹም ባዕዳን ሆንን፡፡

ናፍቀሽኝ እንደገሰገስኩ
አጠገብሽ በደረስኩ
ጭቃ፣ ኮረት
አፈር፣ ዝገት
ሆነሽ ባገኝ
ምን ይዋጠኝ

ብሎ፣ ደበበ ሰይፉ ለይርጋለም እንዳለቀሰላት፡፡

እንግዲህ የነበረውን ወደስፍራው ለመመለስ ከተፈለገ፣ ሀሰተኝነትንና ጥላቻን አስወግደን መጣል ይኖርብናል፡፡ አንድ ለመሆን ሌላ አማራጭ ወይንም አቋራጭ መንገድ የለንም፡፡ በተጨማሪም የተዋስናቸውን የሀሰት የጎሰኝነት ቃላት አንቅረን ልንተፋቸው ያስፈልገናል፡፡