ካፈርኩ አይመልሰኝ ወይስ ሌላ ድብብቆሽ? – በዮሐንስ እ ተመስገን
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) ባለፈው ኦክቶበር 17 ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳን በክብር እንግድነት ለመጋበዝ የቦርዱ አባላት በድምጽ ብልጫ ካጸደቀው በኋላ በተነሳው የጥቂት የቦርድ አባላት ተቃውሞና በተደረገው የሞቀ ንትርክ የውሳኔው እንደገና መቀልበስ በዳያስፖራው የሚገኙ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ደረጃ ያሳዘነ ያስቆጣና ያነጋገረ ጉዳይ ሆኖ ከርሞአል::
ይህ ዜና በድረ ገጾች ከወጣ በኋላ ከቦርዱ አባላትና እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉ የቦርዱን አባላት ውሳኔ ደጋፊዎች የተሰጡትን መግለጫዎችና ጽሁፎች እንዲሁም የውሳኔው ተቃዋሚዎች ከሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀሳብ የገለጹበትን ድረ ገጾችና በብሎግ የወጡትን ጽሁፎች በጥሞና ተከታትዬአለሁ:: በመጀመሪያ ከበርካታ በስደት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሰነዘረው የቅሬታ የሀዘን የዘለፋና የቁጣ አግጣጫ ይህን ዳያስፖራውን በኢትዮጵያ ስም ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሲያሰባስብ የቆየው ታላቅ ድርጅት ህልውና ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ዳያስፖራው በጥንቃቄ ሊመረምረውና ሊያየው የሚገባ መሆኑን ለመግለጽ ነው የዛሬው ጽሁፌ መነሻ:: ለESFNA በአመራር ደረጃ ግዜአቸውን ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን መስዋዕት አድርገው በቅን ያገለገሉ ተመራጮችን ድካምና አስተዋጽዖ በዚህ አጋጣሚ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ::
ስደተኛውን ኢትዮጵያዊ ላለፉት ሩብ ምዕተ አመታት ሲያሰባስብ የቆየውን ይህን ታላቅ ድርጅት በአንድ ወገን በእውነት ለተመረጡበት አላማ ግዜአቸውንና ዕውቀታቸውን ሰውተው የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ ለመወጣት በቅን የሚያገለግሉትን ደግሞ በሌላ ወገን የነቀዙትን የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላትን ወይም በኢህአድግ ደጋፊነታቸው በሼኩ ለጋስነት ወይም በሌሎችም ጥቅማ ጥቅም የተማረኩ ጥቂቶች የአብላጫውን ድምጽ ለመሻር ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱትን በሌላ ሶስተኛ ክፍል መለየትና ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ እንዳይሆን መጠንቀቅ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት ሊሆን ይገባል::
የችግሩን መንስኤ ለመፍታት የጅምላ ፍርድ መስጠትና ሳያነጣጥሩ በሁሉም አግጣጫ መተኮስ የኢህአድግን አላማ ማራመድና መርዳት ነው:: ዳያስፖራው በያለበት ከአውስትራሊያ እስከ አውሮፓ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ ከካናዳ እስከ ኤዥያ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነታቸው የተሰባሰቡበት ማንኛውንም የሀይማኖትም ሆነ የስፖርት ወይም የመረዳጃ ማህበር ስብስብ ወያኔን የሚያባንንና እንቅልፍ የሚነሳ በመሆኑ የወያኔ ኤምባሲዎች ተቀዳሚ ተግባር ይህን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለ ማንኛውንም የህዝብ ስብስብ ማዳከም መከፋፈልና ማፍረስ ነው:: በዚህ አግጣጫም ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው:: ለዚህም እንደመረጃ የማቀርበው ዳያስፖራው በሚገኝበት ሁሉ ያሉትን በዘር ግንድ ቆጠራ የተመሰረቱትን የትግሬ የአማራ የኦሮሞ የጉራጌና የሌሎችም እንደአሸን የፈሉትን ማህበሮች ማየት በቂ ነው:: በቅርቡ ከወደ ሲያትል የተጻፈ የሰፈር ልጆች ስብስብ ወግ አንብቤ የሁሉም ዘር በፍቅር በመተሳሰብ በመከባበር በአንድነት መኖሪያ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን የተገለጸበት ውብ ጥንቅር ነበር:: ወያኔ ያልደረሰበት ስብስብ በመሆኑ ከወያኔ አይን ይሰውራችሁ ብያለሁ አንብቤ እንደጨረስኩ:: ኢትዮጵያ የሚለው ቃል እንደሚኮሰኩሳቸው የዛሬዎቹ መሪዎች ፍላጎት ቢሆንማ የሀይማኖት ማምለኪያ ቦታዎች ሳይቀር በዘር ይከፋፈል ይሉ ነበር ያ ስለአልተቻለ ግን በየቤተ ክርስቲያኑ በየመስጊዱና በየድርጅቱ ውስጥ የየራሳቸውን ሰዎች በመሰግሰግ የተፈጠረውን መናከስና እሰጥ አገባ ሁላችንም በያለንበት የምናየው የቀን ተቀን ክስተት ሆኗል:: የሚያሳዝነው ግን ወያኔ በየግዜው በያለንበት በሚወረውርልን ስንራኮት ስንከፋፈል ስንጋጭና ስንፈራርስ ዘና ብሎ ተቀምጦ ከፍ ላለ ሌላ ከፍፍል ሲያሰናዳን በተላከው ነገር ዙሪያ ስንሽከረከር የጎሪጥ ስንተያይና ለወያኔ ወጥመድ ስንመቻች ማን እንደላከብን ምን ለማግኘት እንደተላከብን ትልቁን የባለጋራችንን ስእል ሳናይ ጀርባ ለመሰጣጣት ፈጣንና የተመቻቸን ሆነናል:: በአጭሩ ለወያኔ ስራውን አቀለልንለት:: በሰሜን አሜሪካ ያለው ይህ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ ከያሉበት ተሰባስበው የሀገራቸውን አንድነት የሚገልጹበትን መድረክ ለማፍረስ በማር የተለወሰ መርዛቸውን በተኑት:: እኛም ተንጫጫን:: አሜሪካ እንዳይገቡ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሼክ ወፈር ወፈር ያለ ቼክ አስይዘው የላኳቸው ታማኝነታችን ምንም ላልከፈለው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ብዙ ለከፈለ የሳዑዲ ከበርቴ እናደርጋለን ያሉት ኢትዮጵያውያኑን ዳያስፖራ ቢያስከፋም የተከፋው ሁሉ ሊያደርግ የሚጠበቅበት በተራ ዘለፋ ያልተረጋገጠውን ሁሉ መቀባባት ሳይሆን በባይሎዉ መሰረት ኦዲት ተደርጎ መርጠን ላስቀመጥናችሁ ቦታ ስለማትመጥኑ ባየነው ሪፖርት ስለተከፋን ስለመረጥናችሁን ጉዳይ ሳይሆን ስለጥቅማችሁና ስለተዛባው አስተዳደር የድርጅት አመራር ብቃት ማነስ ወዘተ የያዛችሁትን ቦታ አዲስ ለምንመርጣቸው እንድታስረክቡ ማለት እንጂ ኢህአድግ ሌባ ሆዳም ሌሎችንም የማይነገሩ ማለት ተገቢ አይመስለኝም:: ለምሳሌ ተነስቼ በኢትዮጵያ አንድነት የጸና አቋም አራምዳለሁ ብል ሌላው አንዱ የሀገሬ ሰው መጥቶ የወያኔ ፖሊሲ ትክክል ነው ሃምሳ ትንንሽ መንግስት መሆን ነው ያለባትያቺ ሀገር ቢል ለራሴ ለመምረጥ የሰጠሁትን መብት ለርሱ ብነፍገው ወይም ጦር ብማዘዝ ተገቢ ባለመሆኑ ለወያኔ ያደረ ቢገጥም ሳንጋጭ ወይ ሳንዘላለፍ ወይ የጎሪጥ በጠላትነት ሳንተያይ በሃሳብና በእምነታችን ተለያይተን መኖር ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ነው:: ወይም ባለንበት የሰለጠነ በሚባል ሀገር ያልሰለጠነ ንግግርና የስድብ ውርጅብኝ ተገቢ አይደለም:: የመረጥነው እኛ ካጠፉ ደግሞ እኛም ስንመርጥ ስለተሳሳትን በሚቀጥለው ምርጫ መቀየር እንጂ እኔ የማምነውን ስላላመንህ እንደአባቴ ገዳይ ጠላቴ ነህ ብሎ መፈረጅና ያሉትን ሁሉ መጥፎ መጥፎ ቃላት ተጠቅሞ መወንጀል እንደማንኛውም ሰው ሊሳሳት የሚችለውን የነገውን ተመራጭ ማስፈራራት ይሆናል:: ESFNA በአመራር ላይ ያሉት ጥቂት ሃይለኞች ላይ ያለው ችግርም ተጠያቂነት ግልጽነት ጥርት ያለ የሂሳብ አያያዝ መኖሩን ያለማወቅ ወይም ኦዲት እንደሌለ መካድ ከብዙዎች ጥቂት ተብሎ የሚጠቀስ ነው:: በስብሰባ ደንብ በድምጽ ብልጫ ያለፈውን ጉዳይ በመጣስ እዚህ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት የሰው መብት በተከበረበት ሀገር እኔ ያልኩህን እንጅ ብሎ ለዱላ መጋበዝ ወይም ማስፈራራት እውቀት ስልጣኔና ብስለት የጎደለው የሚያሰኝ እንጅ ከመጀመሪያውኑ ለአመራር የሚታጭ ሊሆን ባልተገባ ነበር::
ከተመራጮችም በድርጅቱ አላማ ሙሉ ዕምነት የሌላቸው ቢታዩ መፍትሄ የሚያስፈልገው ትልቅ ችግር ነው::
ተመራጭም የህዝብ አገልጋይ እንጂ በሀገራችንና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች እንዳለ መሪ ራስን መቁጠር: ከኔም በላይ አመራር ላሳር አይነት ትምክህት ማሳየት: የህዝብን ድምጽ መናቅና ማጣጣል የት ሊያደርስ እንደሚችል ግምቱን ተመራጭ የሆነ ሁሉ ጠንቅቆ የሚያውቀው ይመስለኛል:: ለምሳሌም የህዝብ ግንኙነት ሃላ ፊው ብሩህና አንደበተ ርቱእ ብጤ ነው ነገር ግን በአንድ መግለጫው ላይ የዳኛ ብርቱካንን የክብር እንግድነት ግብዣ መቀልበስ አንስቶ ሲያብራራ ነገ አንዱ ተነስቶ መለስ ዜናዊ ይጋበዝ ቢል ብሎ አንካሳ ክርክር አንስቶ ምን ያህል የአብላጫ ድምጽ አሸናፊነት እውቀቱ ውሱን መሆኑን ሲያሳይ የሰማውን ሁሉ እንዳሳዘነ ስገምት አዘንኩ:: የትምክህት አመላለስ ወይም ንግግር ያለማወቅ አስመስሎበታል:: ተወካዩ በእኔ አውቅላችኋለሁ የተወጠረና ብስለት የጎደለው ንግግር አንዴ ባይሎው ሲል አንዴ አይ አር ኤስ ኮድ 501 ሲጠቅስ ሌላ ግዜ መለስ ዜናዊን ያለቦታው ሲያስገባ አሳፋሪ ነበር:: ምናልባት ይህ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መናገር ይቻል እንጅ የሚናገረውን የሚያውቅ አይመስልም:: ለማለት የፈለግሁት ለአብላጫ የመገዛት ህግጋት ከመጀመሪያዎቹ የዴሞክራሲ መሰረቶች አንዱና ትልቁ ነው:: አብላጫው ዳያስፖራ ከተስማማ መሪዎችን ይቀይራል ባይሎውን ይቀይራል ያሻሽላል መለስ ዜናዊ ይጋበዝ ካለም ይጋበዛል:: ባይሎው ከESFNA ድረ ገጽ ላይ ለምን እንደተነሳና እንደገና ድረገጹ ላይ ይውጣ ተብሎ የቀረበውን የብዙ ሰዎች ጥያቄ ለምን እንዳልተመለሰ ስናስበው በአመራሩ ላይ ያለንን ጥርጣሬ ከፍ አድርጎታል:: በደካማ ምክንያት የታጀለና ድብቅብቅ ያለ አሰራር የውድቀት መጀመሪያ ነው:: በተከፋፈሉ ራሳቸውን በጥቅም ካስገዙና በደከሙ መሪዎች ምክንያት ይህ ታላቅ ኢትዮጵያውያንን በየአመቱ የሚያሰባስብ ድርጅት ስራው ለአፍታም መቋረጥ የለበትም:: የESFNA የዛሬ ጥቂት መሪዎች ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው አንድን ስህተት በሌላ ስህተት ለማስተካከል ከመሞከር የህዝብን ድምጽ አክብረው ያጠፉትን እንዲያስተካክሉ ዳኛ ብርቱካንን በክብር እንግዳነት እንዲጋብዙ ጥሪዬን አቀርባለሁ:: በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን የምንሰባሰብበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ባመት አንዴም ቢሆን የምናውለበልብበት የአንድነታችን መግለጫ የሆነውን ይህን ብቸኛ የስፖርት ድርጅት ወያኔ ሊያጠፋው ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑን ተገንዝበን በንቃት እንጠብቀው:: ይህ የወያኔ ረጅም እጅ ተመቶ ያጠፋውም ታርሞ መስተካከል ያለበትም ጉዳይ ተሰተካክሎ የኢትዮጵያውያን አመታዊ የስፖርት በአል ከምንግዜውም በላይ አምሮና ደምቆ በመጪው ጁላይ 2011 ጆርጂያ አላንታ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ::
ዮሐንስ እ ተመስገን
November 10, 2011
[email protected]