በዓረና ላይ ስለተፈፀመው ሕገ ወጥ ተግባር ማዕከላዊ ኮሚቴው የወሰደውን አቋም መግለጫ

የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ በጥር 27/2003 ዓ/ም በመቀሌ ከተማ ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ድርጅታችን ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነትን ለማፍረስ ጥር 21 ቀን 2003 ዓ/ም “አስቸኳይ የዓረና ጉባኤ” በሚል ሽፋን በመቀሌ ከተማ በሚገኘው አብሲንያ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የዓረና እውቅና በሌላቸው ግለሰቦች የተደረገውን ስብሰባ በተመለከተ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቶበታል፡፡ ይህ ስብሰባ በማንኛውም መልኩ ሕጋዊነት እንደሌለውና ዓረናን ለማፍረስ ሆን ተብሎ የተደረገ ስለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎች ለማቅረብ የሚቻል ሲሆን ከእነዚህ ማስረጃዎች መካከል የተወሰኑትን ከዚህ በመቀጠል ቀርቧል፡፡

1. ዓረና ከነሐሴ 21-22/2003 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው አሻሽሎ ባቀረበው ሕገ ደንብ ዓንቀፅ 26 ተራ ቁጥር 1 ሰ፥ ላይ እንደተመለከተው “የአስቸኳይ ጉባኤ ጥያቄ ያለው አካል የድጋፍ ድምፅ ለማሰባሰብ ከመንቀሳቀሱ በፊት የአስቸኳይ ጉባኤ መጠራት አስፈላጊነት በተመለከተ በአካባቢው ለሚገኘው የፓርቲ አካልና የፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡” ይላል፡፡ ሕገ ደንቡ በግልፅ ይህን ቢልም በጥር 21 ቀን 2003 ዓ/ም አስቸኳይ ጉባኤ ተብሎ የተካሄደው ስብሰባ ግን በማንኛውም አካባቢ ለሚገኝ የዓረና የፓርቲ አካልና የቁጥጥር ኮሚሽን የቀረበ ድጋፍ የማሳሰብ ጥያቄ ሳይኖር “አስቸኳይ ጉባኤ ተካሂዷል” ማለት ፍፁም ኢ-ሕጋዊና የውንብድና ተግባር መሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አስምሮበታል፡፡

2. አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ ድጋፍ የማሰባሰብ መብትና በሚጠራው ጉባኤ ላይ የመሳተፍ መብት ለዓረና ሙሉ አባላት የተሰጠ መብት መሆኑ በሕገ ደንቡ አንቀፅ 26 -1 ተደንገጓል፡፡ ድንጋጌውም እንደሚከተለው ሰፍሯል “አስቸኳይ ጉባኤ የሚጠራው መደበኛ ጉባኤ ከመድረሱ በፊት በማዕከላዊ ከሚቴ ሊፈቱ የማይችሉ ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳምን ምክንያት ሲኖር ይሆናል፡፡ የአስቸኳይ ጉባኤ ጥያቄ በማንኛውም አባል ወይም አካል ሊነሳ ይችላል” ይላል፡፡ ድንጋጌው ይህ ሆኖ እያለ ጥር 21/2003 ዓ/ም ተካሄደ በተባለው አስቸካይ ጉባኤ ግን ዓረና በአባልነት ፍፁም የማያውቃቸው ሰዎች ስብስብ እንደነበር ደርሰንበታል፡፡ እነዚህ ጭራሸ የድርጅቱ አባላት ያልሆኑ ሰዎች በአስቸኳይ ጉባኤው ከመሳተፋቸውም ባሻገር ለአመራርነት እንደተመረጡም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ታውጃዋል፡፡ ለአብነት ያህልም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት ነሐሴ 21/2003 ዓ/ም ዓረና ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ከአመራርነትና ከአባልነት በሙሉ ድምፅ የተባረረው አቶ ገ/አረጋይ አስናቀ በሕገ ወጡ አስቸኳይ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር ሆኖ እንደተመረጠ ታውጀዋል፡፡ እንዲሁም የዓረናን ሕገ ደንብ በመጣሳቸው ከፓርቲው የተባረሩና በፍቃዳችው ከፓርቲው የተሰናበቱ ሰዎች በአመራርነት እንደተመረጡ ታውጀዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም መምህር ይኩኖ አምላክ ወልዱ፣ አቶ አድሐኖም በርሀ (ካሕሳይ)፣ አቶ መዝገበ ካሕሳይ ፣ አቶ ሃይለ ማርያም አሰፋና አቶ ሙሉ ብሰራት ይገኙበታል፡፡ የድርጅቱ አባላት ያልሆኑ ሰዎች አስቸኳይ ጉባኤ ተብየውን ከማደራጀት ጀምሮ ራሳቸውን በአመራርነት እስከማስቀመጥ መድረሳቸው ምን ያህል ኢ-ሕጋዊነትና የውንብድና ተግባር እየተካሄደ መሆኑ ያመለክታል፡፡

3. የዓረና ሕገ ደንብ የአስቸኳይ ጉባኤ ጥያቄ ያለው አካል የድጋፍ ድምፅ ለማሰባሰብ ከመንቀሳቀሱ በፊት በአከባቢው ለሚገኘው የፓርቲ አካልና የቁጥጥር ኮሚሽን ማሳወቅ እንዳለበትና ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ አግባብ ባለው መንገድ አባላቱን በማሳመን ድምፅ ማሰባሰብ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ሆኖም እነዚህ “አስቸኳይ ጉባኤ አካሄደናል” የሚሉት ሰዎች ለአካባቢ የፓርቲ አባላትና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ካለማሳወቃቸው ባሻገር ምንም ዓይነት የድርጅቱ አባላትን ያካተተ ውይይትም አላካሄዱም\ ተጠራ በተባለው አስቸካይ ጉባኤም የድርጅቱ አባላት አልተሳተፉም፡፡ ይህም ሕገ ደንቡ በአንቀፅ 13-4 እና በአንቀፅ 13-3 አባል ሀሳቡንና እምነቱን በማንኛውም የፓርቲው መድረክና ልሳን የመግለፅ መብት አለው ሲል፣ አንቀፅ 13-3 ደግሞ በተለያዩ የፓርቲ ሃላፊነቶች የመመረጥና የመምረጥ መበት አለው” ይላል፡፡ ይህ በጥር 21 ቀን 2003 ዓ/ም የተካሄደ አስቸኳይ ጉባኤ ተብየው ግን የዓረና ፓርቲ አባላት አልተሳተፉበትም፣ አልመረጡም፣ አልተመረጡም፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ ደንቡን በመጣሱ ሰብሰባው ኢ-ሕጋዊና የውንብድና ተግባር እንደነበር ሕጋዊው የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ ተገንዝቦታል፡፡

4. መቀሌ ላይ ያለው የዓረና ፅ/ቤት ይህ ሕገ ወጥ ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት ስብሰባው እንደሚካሄድ መረጃ ደርሶት ስለነበር ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአስተዳደር፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላት ሕግ ያስከብሩ ይሆናል ከሚል እምነት በመነሳት በዓረና ምክትል ሊቀመንበር የተጻፈ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይህ ዓረና ትግራይ የጠራው የአባላት ይሁን የህዝብ ስብሰባ እንደሌለ ማሳወቅ በሚል ርእስ የተፃፈው ደብዳቤ ለመቀሌ ከተማ አስተዳደር፣ ለትግራይ ክልል ፖሊስና ፀጥታ ቢሮ፣ ለመቀሌ ከተማ ፖሊስና ፀጥታ ክፍል እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ የዚህ ደብዳቤ ቅጅም ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የትግራይ ቅርጫፍና ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና የስብሰባ አዳራሾች ለሚያከራዩ ሆቴሎች ተልኳል፡፡ ደብዳቤ የተፃፈላቸው የክልሉ መንግስት አባላት ግን በተጠየቁት መሰረት ሕግን በማስከበር ፈንታ ኢ-ህጋዊ የሆነውን ስብሰባ ላካሄዱት ወገኖች ድጋፍ ሲሰጡና ሲከላከሉ ታይተዋል፡፡ በርካታ ፖሊሶችቸና ሌሎች የፀጥታ አስከባሪዎች ይህን ሕጋዊ እውቅና የሌለውን በዓረና ስም የተካሄደውን ስብሰባ ሲጠብቁ ተስተውለዋል፡፡ እንዲያውም ስብሰባው የዓረና እንዳልሆነና ፍፁም ሕገ ወጥ እንደሆነ ለማሳሰብ በአከባቢው የተገኘውን የዓረና ትግራይ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነውን አቶ አሥራት አብርሃምን በቁጥጥር ሥር በማዋልና በማሰር የሕገ ወጡ ስብሰባ ተባባሪዎች መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ይህ ተግባር የተወሰኑ ዓረና የማያውቃቸው ሰዎች ሴራ ብቻ ሳይሆን በመንግስት አካላት አስተባባሪነትና መሪነት የተጠነሰሰ መሆኑ ይፋ አድርጎታል፡፡ የመንግስት አካላት ሕጋዊ እውቅና ያለውን የዓረና ድርጅት ሰብሰባ እንዳልሆነ እያወቁ ለዚህ ሙሉ ድጋፍና ከለላ መሰጠታቸው የሕገ ወጡ ተግባር ፈፃሚዎች መሆናቸው በግልፅ ያመለክታል፡፡

ይህ ሕገ ወጥ ሰብሰባ በተካሄደ ማግስትም የመንግሥት ሚድያዎችና ከገዥው ፓርቲ ጋር የተቆራኙት ሚድያዎች ሰብሰባውን ሕጋዊ እንደሆነና ሕጋዊው ዓረና እንደፈረሰ ሲለፍፉ ተደምጠዋል፡፡ እንዲያውም የኢትዮጰያ ቴሌቭዥን በሕገወጡ ስብሰባ የተመረጠውን ሰው የዓረና ሊቀ መንበር በማለት ሲያስተላልፍ ሕጋዊ ም/ሊቀ መንበሩን ደግሞ የቀድሞ የዓረና ም/ሊቀ መንበር በሚል አቅርቦታል፡፡ ይህም በሴራውና ሕገ ወጥነቱ የመንግስት ሚድያዎች ጭምር ተሳታፊ እንደሆኑ ይመሰክራል፡፡ የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ የመንግስት አካላት በዚህ ህግ ወጥ ተግባር በመሳተፋቸው እጅግ የተገረመ ሲሆን ድርጊቱንም በጥብቅ ያወግዛል፡፡

5. ጥር 21 ቀን 2003 ዓ/ም የተካሄደው ህገ-ወጥ ስብሰባ ነሐሴ 21 እና 22 በተካሄደው የዓረና ትግራይ ሁለተኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የተመረጡ ማእከላይ ኮሚቴና የቁጥጥር ኮምሽን አካላት ጭራሽ የማያውቁት ሴራና ውንብድና ነበር፡፡ የዓረና ሕጋዊ ተቋማት ሳያውቁት በስመ ዓረና የሚካሄድ ማንኛውም ስብሰባ ደግሞ ህጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ድርጊቱ በዓረና ላይ የተፈፀመ ሕገ ወጥነት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገራችን የሕግ የበላይነት መጣሱን የሚያመለክት ነው፡፡ በሕግ የተቋቋሙትን ተቋማት አጥፍቶ ሕገ ወጥነትን የሚያነግስም ነው፡፡

የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ በድርጅቱ ላይ የተፈፀመውን ውንብድና የተሞላበት ጥቃት በአገራችን የህግ የበላይነት ምን ያህል እንደተጣሰና ዋስትና እንዳጣ የሚያመለክት መሆኑን ግንዛቤ ወስደዋል፡፡ ይህ ድርጊት የሕግ የበላይነት ከመፃረሩ ባሻገር ሌሎች መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮች እንዳሉም ያመለክታል፡፡ ገዥው ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ይሁን በክልላችን ውስጥ ነፃና ጠንካራ አማራጭ ድርጅት ኖሮ ህዝብ አማራጭ ቀርቦለት እንዲመርጥ እንደማይፈለግ ከተገነዘብን ሰንብተናል፡፡ በአገራችን ሕገ መንግስት ውስጥ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር የሚፈቀድ ድንጋጌ ቢኖርም ገዥው ፓርቲ ግን ይህን ድንጋጌ አይቀበልም፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚመራው የአንድ ፓርቲ አውራነት ወይም አምባገነንነት በሚሰብከው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያ የአውራ ፓርቲ አስፈላጊነት ያለምንም ሃፍረት ማወጁም ሕገ መንግስቱን የሚያከብር ሳይሆን ሕገ መንግስቱን የሚፃረር ነው፡፡ መነሻውም ደጋግሞ የሚገልፀውና መሰረታዊ መመርያው የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ በዓረና ላይ የተደረገው ፍፁም ሕገ ወጥ ተግባርም የዚህ አስተሳሰብ ውጤት መሆኑን ተገንዝበናል ፡፡

ገዥው ፓርቲ ከሚከተለው አምባገነንነት የሚያነግሰው መርህ በመነሳት በዓረና ትግራይ ላይ ብርቱ ጥቃት ማካሄድ የጀመረው ዓረና ከተመሰረተበት ማግስት ጀምሮ ነበር፡፡ “ትግራይ ከአንድ ፓርቲ በላይ ልትሸከም አትችልም፣ የተለያዩ ፓርቲዎች መኖራቸውን ህዝቡን እንዲከፋፈል፣ ልማት እንዲደናቅፍ፣ ሰላም እንዲደፈርስ ሊያደርግ ይችላል” በማለት ህዝቡን ሲያስፈራራና ሲያደናግር ቆይቶዋል፡፡ የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸራቸው የእድገትና ብልፅግና መሰረት ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን ዘመናዊ አስተሳሰብ ወደ ጎን በመተው የተለያዩ ሃሳቦች ማራመድ ለክፍፍልና ጥፋት መንስኤዎች አድርጎ ማቅረቡ ገዥው ፓርቲ ምን ያህል ወደ ºላ እንደቀረ ከማመልከቱ ባሻገር የአንድ ፓርቲ አገዛዝ አምነቱ ተግባራዊ ለማድረግና ለዘለአለም በስልጣን ለመቆየት ፍላጎት ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ በዓረና ላይ እየተፈፀመ ያለው የውንብድናና ጥቃት ትግራይ ውስጥ ከገዥው ፓርቲ ውጭ ሌላ ፓርቲ እንዳይኖር የሚያደርገው እንቅስቃሴ አካል እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡

አንድ አገር ውስጥ ነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ሲቭል ማሕበረሰብና የብዙሃን ፓርቲዎች ስርዓት ከተረጋገጠ፣ ሙስና በቁጥጥር ስር እንደሚውል፣ ፍትህ እንዲሚሰፍን ፣ ብልሹ አስተዳደር እንደሚወገድ፣ ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እንደሚያገኙ ፣ዴሞክራስያዊ መብቶች እንደሚከበሩና የአምባገነንነት ዕድሜ እንደሚያጥር ግልፅ ነው፡፡ ይህን በውል የሚገነዘበው ገዥ ፓርቲ ሙስናን አስፍኖ ፣ ፍትሕን ረግጦ፣ ብልሹ አስተዳደርን እንሰራፍቶ፣ ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶችን ረግጦ፣ የአንድ ፓርቲ አምባገነን ስርአቱን በማስቀጠል፣ በብዙሃን ፓርቲ ስርአት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ማድረሱ አይቀሬ ነው፡፡ የህዝቡ ተቆርቃሪ በመምሰል የብዙሃን ፓርቲ ስርአት አደጋን በመስበክ ሃቀኛ ፓርቲዎች ለመደምሰስ የሚጥረው፣ ብቻውን በስልጣን ኮረቻ ለመቆየት ካለው ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡ ዓረና ከነዚህ በገዥው ፓርቲ ሞት ከተፈረደባቸው ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ ነው፡፡ የህዝቡ ፍላጎትና ድጋፍ ጫና ሆኖበት ፍላጎቱን ሳያሳካ ቢቆይም ገዥው ፓርቲ ዓረናን ገና ከእንጭጩ ለማጥፋት ወስኖዋል፡፡ ዓረና በተመሰረተ ማግስት በገዥው ፓርቲ የተፃፈና ለህዝቡ የተሰራጨ ባለ 14 ገፅ ጽሑፍ ይህን የገዥውን ፓርቲ ፍላጎትና ውሳኔ በግልፅ ያመለከተ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ መሰረታዊ ይዘት የዓረናን ስም በማጥፋት ህዝቡ ውስጥ ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ ያለመ ነበር፡፡ አሁን በዓረና ላይ እየተፈፀመ ያለው ሕገ ወጥ እርምጃን ቀደም ብሎ በዓረና ላይ ሲካሄድ የነበረው ሴራ ቅጥያ እንደሆነ ማእከላይ ኮሚቴው ተገንዘቦታል፡፡ የገዥው ፓርቲ አመራሮች ትግራይ ውስጥ አማራጭ ሊኖር እንደማይፈልጉ በየአደባባዩ ሲለፍፉ ተደምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ልፈፋያዎች አንዱ በ2002 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ የህወሀት 35ኛ የልደት በዓል ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ የተናገሩት ግልጽ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ትግራይ ውስጥ የሆነ ሰንጥቅ እንዳይፈጠር ተጠንቀቁ ከማለት ጀምሮ፣ በተቃዋሚነት የተሰለፉትን ወገኖች ግርድ፣ ጭቃ፣ እብቅ፣ ወዘተ በማለት ሲወርፉ ተደምጠዋል፡፡ ዓረናን በስም አይጥቀሱ እንጂ ተራው ዜጋ ሳይቀር የተገነዘበው ነገር ቢኖር ያነጣጠሩት በዓረና ላይ እንደነበር ነው፡፡ ህዝብ አማራጮችን ሰምቶ መወሰን አለበት የሚል ዓላማ ያራምድ የነበረውና ለዚህም ከፍተኛ መስዋአትነት የከፈለው ህወሃት “ትግራይ ከአንድ ድርጅት ውጭ ልትሸከም አትችልም” ብሎ በአደባባይ መለፈፉ ምን ያህል የተሸነፈና ያበቃለት እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚህ ሌላም፣ አማራጭ ካስፈለገ እኔ ልምረጥላችሁ ሲሉም ይደመጣል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫውም አልፎ አልፎ “አማራጭ አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታመንም እንኳ ዓረና አማራጭ ሊሆን አይችልም” ሲሉ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባላት ይደመጣሉ፡፡ አማራጭ አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታሰብ “ዓረና አማራጭ ሊሆን አይችልም” ማለት የሚያመለክተው ነገር ቢኖር የህዝብ አስተሳሰብና የማመዛዘን ብቃት ዝቅ አድርጎ በምትካችሁ እኔ የሚበጃቹህን ፓርቲ ልምሪጥላችሁ እንደ ማለት ነው፡፡ ሕጋዊው የዓረና ፓርቲ እያለ ሕገ ወጥ የሆነ ቅጥቅጥ ፓርቲ ተፈጥራል ብሎ ማወጁና ማስተጋባቱም ገዥው ፓርቲ ለህዝቡ የሚበጅ አማራጭ ፓርቲ ፈጥሮለታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህ ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲ የሆነ ተግባር ደግሞ የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ያወግዘዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ የዓረናን አባላት አንድ በአንድ በማግኘት ሊያባብላቸውና ከቆሙለት ዓላማ ሊያገላቸው ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ስራ እሰጣቸዋለሁ፣ ዕድገት ታገኛላችሁ፣ የውጭ ትምህርት ዕድል ልሰጣቹሁ እችላለሁ፣ ወዘተ በማለት ለማታለልና ለማባበል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ከስራ የተፈናቀሉ ዕድገት የተከለከሉ የትምህርት ዕድል የተነፈጉ፣ የዕርዳታ እህል የተከለከሉ፣ የታሰሩ የተደበደቡ የተሰደዱ አባላት በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ የገዥው ፓርቲ ተግባር ዓረናን በማዳከም ረገድ ድርሻ ቢኖረውም የፈለገውን እቅድ ግን ሊሳካለት አልቻለም፡፡ እንድያውም ህይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ በርካታ አባላት እንዲፈጥር ምክንያት ሆኗል፡፡ የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ ይህን ሁሉ መስዋእትነት ከፍለው የፓርቲ ህልውና ያረጋግጡትን ሲያመሰግን ፣ በገዥው ፓርቲ በኩል በአባሎቻችን የተፈፀመው ወደር የለሽ ግፍና በደልን ግን አጥብቆ ያወግዛል፡፡

ገዥው ፓርቲ እስከአሁን ድረስ ሲያካሄድ የቆየውን ዓረናን የማፍረስ እንቅስቃሴ ስላልተሳካ የከፋ ውንብድና በመፈፀም ሊያፈርስው እንደወሰነ ግልፅ ሆኗል፡፡ የአውራ ፓርቲ ወይም የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት እውን ለማድረግ ራሱ ያወጣውን ሕግ እንኳ ሳይፈቅድለት ዓረናን ለማፍረስ ያስችለኛል ያለውን እርምጃ እየወስደ ነው፡፡ ይህ እርምጃ እንደሚወስድ ቀደም ብለው ከፍተኛ የገዥውፓርቲ አባላት ስያወሩ የተደመጡ ሲሆን ልክ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማለት እንዳወጡት ሁሉ በዚህ የአምስት ዓመት ጊዜ ትግራይ ውስጥ ተቃዋሚ የሚባል ፓርቲ ሊኖር እንደማይችል እየተናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው ሕገ ወጡ አስቸኳይ ጉባኤ ተብየው የተገነዘብነውም ይኸው ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችና በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ያሉ ሚድያዎች ይህን ሕገ ወጥ ስብሰባ በስፋት ከማስተጋባታቸው በተጨማሪ ሕጋዊው ዓረና ፓርቲ ፈርሰዋል በማለት አቋም ወስደው አውጀዋል፡፡ ሕግ እንዲያከብሩ የተጠየቁት የመንግስት አካላትም አሻፈረኝ ብለው ኢ-ህጋዊውን ስብሰባ ደግፈው ቆመዋል፡፡ የዓረና ማእከላይ ኮሚቴ ይህ ሁሉ ሕገ ወጥነት እንዲቆምና ቢያንስ ገዥው ፓርቲ በነደፈው የጨዋታ ሕግ እንዲስራ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡

ገዥው ፓርቲ ዓረናን በማጥላላት በህዝቡ ህሊና ውስጥ ሊያስፍነው የሚፈልገው አሉታዊ አመለካከትም በጥብቅ ያውግዛል፡፡ ዓረና ከደርግ-ኢሰፓ ጋር በማመሳሰል የዜጎችን ዴሞክራስያዊና ሰብአዊ መብቶችን ለመንፈግ እንደተነሳ፣ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለመርግጥ እንደቆመ፣ ሰላምን ለማወክ አንዳቀደ፣ ዕድገትና ለውጥን እንደሚፃረር አድርጎ የሚያቀርብ ዘመቻ ፍፁም መሰረተ ቢስ መሆኑን ሊያስገነዝብ ይወዳል፡፡ እንድያውም በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉትን ከፍተኛ በደሎች ለማስቆምና ለመፍታት ከፍተኛ መስዋዕትነት በመከፈል ላይ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ዓረና በአገራችንና በክልላችን ለማስፈን የሚፈልገው ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና ዕድገት በተመለከተ በነደፈው ፕሮግራም አስፍሮዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ዓረና፤

1. የዜጎች ነፃነትና ክብር ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ
2. ሕገ ወጥነት ተወግዶ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ
3. ብልሹ አስተዳደር ተወግዶ መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ
4. በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋው ሙሱና እንዲወገድ
5. በየጊዜው እየጨመረ ያለው ስራ አጥነት እንዲወገድ
6. አስከፊው የዜጎች የኑሮ ውድነት አንዲቃለል
7. ስር የሰደደው ድህነት እንዲቀርፍ

እንደሚታገል በፕሮግራሙ ውስጥ አስፍራል፡፡ ዓረናን ለማፍረስ የተሻረበው ሴራም፤ ህዝቡ ይህን የዓረና ዓላማ አዳምጦ በአማራጭነት እንዳይወስድና እየደረስበት ያለውን የኑሮ ምስቅልቅልና ብልሹ አስተዳደር እንዳያስተጋባ ካለው ስጋት የተነሳ መሆኑ ተገንዝቦታል፡፡

አማራጭ ሀሳብ እንደጦር የሚፈራ ፓርቲ የተሸነፈ ፓርቲ ነው!
የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉአላዊነትን ፓርቲ ማእከላይ ኮሚቴ
ጥር.27.ቀን 2003 ዓ/ም
መቐለ