“በጉዲፈቻ “ስም የሕፃናት ባሪያ ንግድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጧጡፏል
(ኢትዮ እማማ)
ከስድስት አምት በፊት ወደ አሜሪካ በጉዲፈቻ የገቡ የውጪ ሕፃናት 22,990 ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 284ቱ ኢትዮጵያዊያኖች ነበሩ ።እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች 2010ዓ/ም ብቻ ከ11,000 በአጠቃላይ ከዓለም አቀፍ ወደ አሜሪካ በጉዲፈቻ ከመጡ ሕፃናት ውስጥ 2,500 የሚጠጉት ኢትዮጵያዊያኖች ናቸው።ይህም ኢትዮጵያ እንደ ቻይና ቀጥር አንድ የጉዲፈቻ ሰጪ አገር ተብላ ለመመደብ በቅታለች እንደ አሶሴትድ ፕሬስ ዘገባ።
አብዛኛዎቹ ሕፃናት ወላጅ አልባ የሆኑ ፣አሳዳጊ የሌላቸው ፣በጎዳና ላይ የሚያድሩ ከፊሎቹ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው እነሱን ለማሳደግ አቅሙ የሌላቸው ናቸው።እነዚህን ሕፃናት በጉዲፈቻ አምጥቶ እንዲያድጉ ማድረግ ለልጆቹ የወደፊት ሁኔታ ጠቃሚ መሆኑን አሜሪካኖቹ ያሰምሩበታል። እንዲያውም ባለፈው የፈረንጆች መስከረም ወር 2010ዓ/ም ላይ አንድ የአሜሪካን የልዑካን በድን ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በመነጋገር የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ካመሩት መካከል አንዱ የሆኑት የሰቴት ዲፓርትመንት በተለይ ሕፃናቶች አማካሪ የሆኑት ሱሳን ጃኮብስ ትክክለኛ ሥራ እየሰሩ እንዳሉና የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀው ፤ሌሎች ሀገሮችም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጉዲፈቻ አሰጣጥ አካሄድ መከተል እንደሚኖርባቸው ይገልፃሉ።
ከ2004 ጀምሮ የዓለም አቀፉ የጉዲፈቻ ዝውውር ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። ቻይና፣ ሩሲያና ደቡብ አፍሪካ በርካታ ሕፃናትን በመላክ ሲታወቁ ጓቲማላ፣ቬትናምና ኔፓል ከሙስና ያልፀዱ ናቸው።የአሜሪካ ቤተሰቦች ኢትዮጵያውያን ሕፃናቶችን በመርዳት ከፍተኛ አስታዋፆ ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሕፃናቶችን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ዘግጁ ናቸው ይላል ዘገባው።
ዴቪድ ማክዱራምና ባለቤታቸው ኤሚ ከ ኢትዮጵያዊ ጉዲፈቻ ልጃቸው ከኢላ ጋር ቴክሳስ ውስጥ ነው የሚኖሩት ።ኢላንን ከኢትዮጵያ በ2008 ነው ያመጧት ።አሁን ደግሞ ሁለተኛቸውን የጉዲፌቻ ልጅ ለማምጣት ተዝጋጅተዋል።ማክዱራም እንደሚሉት ልጃቸው ከቻይና የጉዲፌቻ ልጅ ለማምጣት ፕሮሰሱ አራት አመት ፈጅቷል።የኢትዮጵያ ግን ይህን ያህል አይወስድም ባይ ናቸው። አፍሪካውያኖቹ ምርጫቸው እንደሆነም ይናገራሉ።ማክዱራም እንደሚሉት ኢላ ዳላስ ውስጥ የሚገኝ የአንድ የኢትዮጵያ ሬስቱራንት ውስጥ ደንበኛ ነች። ወደዚህ ሬስቱራንት እንዲወስዷት ትሻለች። ምክንያቱም እንደሷ አይነት ያሉ ቤተሰቦችን ማየት ትፈልጋለችና፤ ሁሉም ሕፃናቶች ተመሳሳይ አይነት ታሪክ እንዳላቸው ያውቃሉ በማለት ይገልፃሉ።
ቤታንያ ክሪስቲያን ሰርቪስና ግላድናይ የጉዲፌቻ ማዕከል በወኪልነት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰራሉ። ግላድናይ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ውስጥ በ2005 የተመዘገበ ድርጅት ሲሆን ከ 500 በላይ ሕፃናትን በጉዲፌቻነት ለአሜሪካውያን አስረክቧል።
የአፍሪካ ፕሮግራም ማኔጂንግ ዳሪክተር የሆኑት ስኮት ብራውን ሕፃናትን በጉዲፌቻነት ከመስጠት ባሻገር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆን የሥራ ስልጠና ፕሮግራምና በየመንገዱ የሚያድሩ ሕፃናቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ የገለፃሉ።”አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥፎ ጫዋታ የሚጫወቱ አሉ፤ ከዚህ መውጣት አለብን ፤ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነን ከሰራን ከሌሎች አገሮች ሀገሪቷ በተሻለ መልኩ ተፈላጊ በመሆን መሪ ትሆናለች “ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የጉዲፌቻ ዝውውር አሳዛኝ ከመሆኑም ባሻገር ሌላው ቀረቶ ከሌሎች አገሮች ጋር የሕፃናቶቹ ቤተሰቦቻቸው የሚያገኙት ገቢ ተመጣጣኝ ካለመሆኑም ሌላ አባዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጁን አሳልፎ የሚሰጠው ለማሳደግ ጠልቶ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነትና ችግር፤ እንኳን ሕፃኑን ሊያሳድግ ቀርቶ ለራሱም የሚቀምሰው በማጣቱ በረሀብ ከሚሞት፤ ያብራኩን ክፋይ በጉዲፌቻነት መስጠት ግዴታ ስለሆነበት ነው።በእንፃሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕፃናት ስም የከፈቱ የተለያዩ ድርጅቶች ከነጌቶቻቸው ጋር በመሆን ከብረዋል።
አንዳንድ የአሜሪካ የኮንግሬስ አባላቶች ጉዲፌቻነትን በጥብቅ እየተቃወሙ ይገኛሉ። “ሕፃናቶች ከቤተሰቦቻቸው ሳይለዩ የሚረዱበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል “ባይ ናቸው። ኩርጌይዚስታን በ2008 ከ60 በላይ የአሜሪካ ቤተሰቦች በሙስና ውስጥ በመዘፈቅ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሕፃናቶቹን በማዘዋወራቸው እገዳ ሲጣልባት በተመሳሳይ ሁኔታ ኔፓል በሙስናና በተበላሸ አስተዳደር በአሜሪካ መንግስት እገዳ ተጥሎባት የ80 ሕፃናቶች ጉዳይ እንደገና እየታየ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በአገራችንም በርካታ ሕፃናቶች ከወላጆቻቸው በትንሽ ገንዘብ ተነጥቀው አሊያም ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት አጥተው ለሌላ አሳዳጊ ሰው መስጠት እየተለመደና እየተባባሰ መምጣቱ ሁላችንም በያለንበት ቆም ብለን ልናስብ ይገባል።በተለይም ዛሬ ምንም የማያውቁ ሕፃናቶች ከእናታቸው ጉያ እየተነጠቁ እንደ ዘመናዊ የባሪያ ንግድ ሲቸበቸቡ ማየት የሀገራችን ብልሹ አስተዳደር አንዱ ገፅታ አመላካች መሆኑን ሳናሰምርበት አናልፍም።
በተለይም በአሜሪካና አካባቢው የምትገኙ ኢትዮጵያውያን፤ የወያኔ መንግስት በሕፃናት ላይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን የሕፃናት ባሪያ ንግድ እንዲያቆም ግፊት በማድረግና በጉዲፈቻ የተሰጡ ሕፃናቶችም በአሳዳጊዎቻቸው በጥሩ ሁኔታ መያዛቸውን በአካባቢያችሁ ካሉ በቅርብ ሆናችሁ ልትከታተሏቸውና ፍቅርን ልትለግሷቸው ይገባል እንላለን።