የ”ይቅርታዉ” ሰነድ ሲተነተን – በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
ይህ ጽሁፍ ጋዜጠኛ ጺዎን ግርማ በኢትዮጵያ ዛሬ ከጻፈቸዉ የተወሰደ ነዉ። ዝርዝሩን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና እና የኢንስቲትዩት ኦፍ ሂዩማን ራይት መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ይህን ሰነድን (ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ፈረመች የተባለዉን) ከአራት ነጥቦች አንጻር በመመዘን ትንታኔያቸውን ያስቀምጣሉ። የመጀመሪያ ነጥባቸው፣ ሰነዱን ከሕግ አኳያ መገምገም ነው፤ ”ከሕግ አኳያ የቀረበው ሰነድ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ናቸው በሚባሉት አገሮች ከሕጋዊነት አግባብነት አንጻር ተቀባይነት አይኖረውም። አንድ እስረኛ ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በላይ የሕግ የምክር አገልግሎት ተከልክሎ፣ ምንም ዐይነት የሕግ ምክር ከጠበቃ ጋራ ሳያደርግ መጨረሻ ላይ እንዲህ ብሎ ፈርሟል የሚለው ፍርድ ቤት ቢቀርብ ዳኛው በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥያቄ፤ ይህን ጽሑፍ ስትጽፍ የሕግ የምክር አገልግሎት አግኝተህ ነበር ወይ? የሚል ነው። ከዚህ አንፃር ለብቻዋ የታሰረች፣ ሁለት ጠበቆቿ እንዳያገኟት የተከለከለች ልጅ በመጨረሻ ይህን ሰነድ ፈርማለች ተብሎ ቢቀርብ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ሰነዱ ሕጋዊ ተቀባይነት የለውም። በሕግ ፊትም በእግሩ መሬት ረግጦ መቆም የሚችል ሰነድ አይደለም፤” በማለት ሕጋዊ አግባብነቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ መዝነው ያጣጥሉታል።
ዶ/ር ዳኛቸው የሰነዱን አግባብነት የገመገሙበት ሁለተኛው ነጥብ የሀገርን የይቅርታ ወግ እና ልማድ መሠረት ያደረገ ነው። ”በዐፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበረውን የቅርብ የኢትዮጵያ የይቅርታ ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። በዐፄው ጊዜ ይቅርታ የጠየቁ ሰዎች እንዴት ነው የተስተናገዱት? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ከራስ ጌታቸው እስከ ጄነራል ታደሰ ብሩ እና አሁን በሕይወት ያሉት እነ ታምራት ከበደ ያስገቧቸውን ሰነዶች አይቻለሁ። በምንም መልኩ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ዐፄ ኃይለሥላሴ ልከውላቸው የፈረሟቸው ሰነዶች አይደሉም። በርግጥ ይቅርታውን ጠይቀዋል፤ ይቅርታም ተሰጥቷቸዋል። ያቀረቡት ይቅርታ ግን ተሳስተናል፤ ይቅርታ እንዲያደርጉልን ዙፋኖ ሥር ወድቀናል በሚል በጥቅሉ የቀረበ እንጂ፤ በዚህ ቦታ እንዲህ አድርገናል፤ በዚህ ቦታ እንዲህ ብለናል በሚል የእነሱን ሰብዕና እና ማንነት በሚያዋርድ መልኩ የተዘጋጀ አይደለም፤” በማለት ወ/ሪት ብርቱካን የፈረመችው ሰነድ ከቆየው የሀገር የይቅርታ ወግ እና ልማድ ጋራ ተቃርኖ ያለው መሆኑን በምሳሌ ያስረዳሉ።
በሦስተኛነት ሰነዱ የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ትርጉም ይፈትሻሉ፤ “የሰነዱን ፖለቲካዊ ይዘት መዝነው ለእኔ እንደሚገባኝ ሁለት መልዕክት ነው ያለው። በተለይ መንግሥት ለሁለት ዓመት ሲያቀርበው የነበረው ክርክር፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሻኝን ብናገር ምንም አልሆንም፤ ምክንያቱም እኔ ጠንካራ የውጭ ደጋፊዎች ስላሉኝ” ብላለች እያሉ ነው ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም ደጋግመው ሲነግሩን ነበር።
እዚህ ሰነድ ላይ ይሄ የእነሱ ንግግር መካተቱ በጣም የሚገርም ነገር ነው። ከታሰረች ጀምሮ ሲያቀርቡት የነበረው ክስ እና የእነሱ ትንታኔ በእርሷ አፍ ውስጥ ተጨምሮ የቀረበ ሰነድ ነው። የታሪክ ምሳሌ ብናጣቅስ ልጅ ኢያሱ ሰልመዋል ተብለው ነው የተከሰሱት፤ ከትግራይ በረሃ በሰንሰለት ታስረው ተይዘው ሲመጡ፣ “በል እንግዲህ አሁን መስለምህን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ንገር” ብሎ ጫና የፈጠረባቸው ሰው የለም። ይኼኛው ሰነድ ግን በወ/ሪት ብርቱካን ላይ ብርቱ ጫና የተፈጠረበትን ሁኔታ ያሳየናል። ወ/ሪት ብርቱካን ይቅርታውን ጻፊ ቢሏት በራሷ አንደበት እና ቋንቋ ትጽፈዋለች፤ ነገር ግን በባለሥልጣናቱ ሲነገረን የቆየው በሰነዱ ላይ መካተቱ እነሱ የደረሱበትን ደረጃ በውል የሚያሳይ መልዕክት ነው ያለው። …
ሁለተኛውን የሰነዱን ፖለቲካዊ መልዕክት ሲያስረዱም፤ “ይሄ ሰነድ ያለፈውን ብቻ ሳይሆን ወደፊት መሆን ያለበትን የሚጠቁም ነው። ይኸውም በወ/ሪት ብርቱካን ስም ይኼ ለዜጎች የተላለፈ መልዕክት አለ፤ ”አርፌ አሮጊት እናቴን እጦራለሁ፤ ልጄን አሳድጋለሁ” የሚለውን ወ/ሪት ብርቱካን እንዲህ ካለች ሌላ ጥያቄ ያላችሁ ዜጎችም ይህን መንገድ ብትከተሉ ይሻላችኋል የሚል ለዜጎች የተላከ መልዕክት ነው። በጣም የሚገርመኝ “እናትን የመጦር” ጥያቄ አለ። እነሱ በረሃ ክላሽ ይዘው ሲገቡ እናት አልነበራቸውም? እና አሁን ለእኛ ነው ”ዐርፈህ እናትህን ጡር፣ ልጅህን አሳድግ” የሚለው የሚነገረን? ይህ ከወ/ሪት ብርቱካን ጀርባ ለእኛ ለዜጎች የተሰጠ መልዕክት መኖሩን የሚያሳይ ነው፤ … በማለት ትንታኔያቸውን ይቀጥላሉ።
የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው በአራተኛነት ያስከተሉት ነጥብ የአርስቶትልን የፍልስፍና አስተምህሮ ምስክር የሚያደርግ ነው። ”እኔ ብዙ ጊዜ የማጣቅሰው የአርስቶትልን የኢቲክስ አስተምህሮ (Nicoomachain Ethics) ነው። በዚህ አስተምህሮ መሠረት ፈላስፋው ብርታት፣ ጉብዝናና ጀግንነት (Courage) ምን እንደሆነ በዘይቤ ያብራራበት ሁኔታ አለ። በአደገኛ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብርታት፣ ጉብዝናና ጀግንነትን ማሳየት እንዴት እንደ ሆነ ሲያስረዳ፣ ”ዐሥር ሰው ሲመጣብህ ሮጠህ ካልሸሸህ (ካላፈገፈግህ) ጀርጃራ ትባላለህ። አንድ ሰው ሲመጣብህ ከሸሸህ ግን ፈሪ ትባላለህ” የሚል በጣም አስገራሚ ምሳሌ ይሰጣል። እኔ ከዚህ ሰነድ የተረዳሁት ወ/ሪት ብርቱካን እንደ ሰው እና እንደ ፖለቲከኛ ብስለትን ያሳየችበት ውሳኔ ነው። የፈላስፋው ምሳሌ እንዲያውም ዐሥር ሰው ነው የሚለው፤ እርሷ 400 ሺሕ ወታደር ካለው ሰው ጋራ ፊት ለፊት የእሳት ራት አልሆነችም። የፖለቲካ ጎርፍ በመጣበት ጊዜ እንደ አግባቡ ዞር ማለት ብስለት ነው። ይሄ ሰነድ የሷን በሳል ሰብዕና፣ ብርታቷን፣ ጀግንነቷን እና ጉብዝናዋን የሚቀንሰው አይደለም። በአጠቃላይ ይሄ ሰነድ በአንድ በኩል ስለ ኢሕአዴግ በሌላ በኩል ለእኛ ለዜጎች የተላከውን መልዕክት ከማሳየት ሌላ ፋይዳ የሚኖረው አይደለም። በሕግ ፊት ቢቀርብም የሕግ ይዘት የሌለው ሰነድ ነው” በማለት ሰነዱን ፋይዳ ቢስ ያደርጉታል።
የወ/ት ብርቱካንን መታሰር የተቃወሙ፣ ከእስር እንድትፈታም ውትወታ ይካሄድበት የነበረው አንዱ መታገያ መንገድ ፌስ ቡክ ነው። ደጋፊዎች በገፆቻቸው በምስላቸው ምትክ የሷን ምስል ተክተው ቆይተዋል። የመፈታቷ ዜና እንደተሰማም ደስታቸውን የገለፁ በርካቶች ናቸው። በስሟ እና ”ነፃነት ለብርቱካን ሚደቅሳ” በሚል የተከፈቱ መጨመርያ መድረኮች (ብሎጎች) በመፈታቷ ደስታቸውን ገልው እስካሁን ድጋፋቸውን ሲሰጡ ለቆዩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ”ወ/ሪት ብርቱካንን ያደነቅናት በእንቢተኝነቷ እና በቆራጥነቷ ነው፤ ይህን ብርታቷን አሁን በፈረመችው ወረቀት ስናጣው ሰጥተናት የነበረው ራንክ ዝቅ ይልብናል፤” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው ለእንዲህ ዐይነቶቹ አስተያየት ሰጪዎች ምላሽ አላቸው “ሕዝቡ የወ/ት ብርቱካንን የአፈታት ሁኔታ የሚረዳ ይመስለኛል፤ ምንም ዐይነት ምርጫ ያልተሰጣት ልጅ ናት። እንደ ሰው ለራሷ ጤንነት፣ እንደ እናት ለልጇ ኃላፊነት አለባት። ይህን ሰነድ ባትፈርም ከልጇ እና በተዘዋዋሪ ከእናቷ ሁኔታ አኳያ የሞራል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ይሄን ሕዝቡ ይረዳል፤ መረዳትም አለበት። አንድ ቀን ታስረው የማያውቁ ሰዎች የራሳቸውን ፍርድ ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል። አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ለብቻዋ ትንሽ አምባ ላይ ታስራ የነበረች ልጅ ናት። ወጣት ናትና ለነገ መትረፍ አለባት። እኔ ከምጠብቀው በላይ የምትችለውን ያህል ሄዳለች። መጀመሪያ ”ወዮ፣ እናቴ” ብላ ማልቀስ ትችል ነበር፤ አላደረገችውም። ወ/ት ብርቱካን እኮ ፖለቲከኛ ናት እንጂ ክርስቶስ ሠምራ ወይም አቡነ ገብረመንፈሥ ቅዱስን አይደለችም። ይህን መለየት አለብን። እርሷ የኃይማኖት መሪ ወይም የመንፈሣዊ እንቅስቃሴ ኃላፊ አይደለችም። ከሀገራችን ጳጳሳት አንዳንዶቹ ሳይቀሩ መሥራት አልቻልንም እያሉ ስደት በሚሄዱበት ሀገር ላይ አይደለም እንዴ ያለነው? የቆየው ሥርዓት እና ትውፊት እኮ ይህን አይፈቅድላቸውም። ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚፈቅደው ክርስትና ማስተማር ሳይቻል ሲቀር ነው እንጂ፤ አንድ ካህን ለሕይወቴ ያሰጋኛል ብሎ መሸሽ የለበትም። ወ/ሪት ብርቱካን ጠንካራ የሆነች የፖለቲካ መሪ ናት። አሁን ለደረሰችበት ውሳኔ እንዲያውም እኔ ብስለትን ነው ያየሁባት፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ይፈልጋታል። እነሱ ሊያደርጉ የፈለጉት ያካበተችውን የፖለቲካ አቅም (ፖለቲካዊ ድልብ) እንዳለ አምክነው ሊያስወጧት ነው፤ ነገር ግን በጫና የተፈረመ ሰነድ ይህን ያካበተችውን እና ያዳበረችውን ብርታት፣ ጀግንነት እና ጉብዝና (courage) በምንም መልክ ሊቀንሰው የሚችል አይደለም የሚል አቋም ነው ያለኝ፤” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ “ውሎ አድሮ እንዲህ ያለ ሰነድ መፈረሟ ካልቀረ ፊቱኑ የቀረበላትን አማራጭ ብትቀበል ኖሮ” በሚል ለሚሰጡት አስተያየት፤ ዶ/ር ዳኛቸው አጽንዖት ሰጥተው እያስረገጡ በሚናገሯቸው ቃላት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ። ”ጠንካራ ፖለቲከኛ ዝም ብሎ ወደ ኋላ ከመሸሽ ወደ ፊት በመምጣት ይጋፈጣል፤ ዋጋ ይከፍላል፤ እንደ አግባቡ ወደ ኋላ ያፈገፍጋል። ወ/ሪት ብርቱካን ይህን ነው ያደረገችው። ይህቺ ልጅ በመታሰሯ በሀገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ በኢሕአዴግ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዲደርስበት አድርጋለች። በእስሯም ሆነ በተፈታችበት ሁኔታ የሥርዓቱን ምንነት እንድንረዳው አድርጋናለች። ”ያኔ ነግረናት ነበር” የሚሉ ካሉ ዝም ብለው ያውሩ። እሷ ይህን መፈተሿ ፖለቲካው ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል አሳይታናለች። እነኚህ ሰዎች ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ምን እንደሚያደርጉ በወ/ሪት ብርቱካን እስር አሳይተውናል። ወ/ሪት ብርቱካን ያኔም ልክ ነበረች፤ አሁንም ልክ ናት፤” በማለት በይቅርታ ሰነዱ ላይ ያደረጉትን ምዘና እና ሒሳዊ ዕይታ ይቋጫሉ።