ለነገሩ፡ ለብርቱካንም ለኛም መታሰሯ ይበጀናል
አንዳንድ ሰዎች፡ እንዲሁም ቤተሰብ
እናቷ እንኩዋን፡ መቼም የናት አንጀት ነውና፡ ትፈታልኝ እንጂ፡ እንኳን ታሰረች ሊሉ አይችሉም። አንዳንድ ሰዎች ግን፡ በግልም ባደባባይም ከብርቱካን ጋር በተያያዘ የሚያሰሙት ከንፈር መምጠጥና፡ አይ “ይህቺ ሴት ተጎዳች” ንግግር ስህተት ነው ብዬ ነው ሀተታዬን የምጀምረው፡ ዛሬ። ብርቱካን ለመረጠችው የፖለቲካ ሕይወት ነው የታሰረችው። እንደኔ እንደኔ፡ ብርቱካን፡ የወጣላት፡ በሳልና፡ የበቃች መሪ እንድትሆን፡ በእስርና በእንግልት መፈተን አለባት። ስለዚህም፡ በምእራባዊያን መንግስታት ፊት የሕወሀትን ሕገ ወጥነት ከማሳየት አንጻር እስራቷን እንኮንነው እንጂ፡ ከዚህ በታች ቀጥዬ ከምዘረዝራቸው ምክንያቶች አንጻር፡ ሕወሀት ተሳስቶና እንደተለመደው አንድምታውን አዙሮ ማየት ተስኖት ብርቱካንን ማሰሩ፡ ለትግላችን ፖለቲካዊ በረከት አለው እላለሁ።
ምክንያት አንድ፡ ያልታሰረ ማንዴላ፡ ከኛ በምን ይለያል?
የሰው ልጅ የሚድነው በመከራና በመስዋእትነት ነው። እሱ ባይሞት የሚሞትለት ይፈልጋል። በእስልምናና በሌሎች ሀይማኖቶች ላይ ለጽህፈት የሚያበቃ እውቀት የለኝም። በክርስትና ግን ትንሽ ሽርፍራፊ ነገሮች ታጥቄያለሁ። ክርስቶስ ራሱ እዚያው ከሰማያዊ ከመንበሩ ቁጭ ብሎ የምንድንበትን ቁልፍ ጠቅ ማድረግ ሲችል፡ የለም የሰው ልጅ ይድን ዘንድ የሰው ልጅ መሰቀል አለበት ብሎ መዳናችንን በሞት፡ ሞታችንን በመስቀል ነው የሻረው ተብሎ ተጽፏል። ሞት ብቻማ ቢሆን ቀላል ነው። ግርፋቱ፡ መወጋቱ፡ መጎተቱ፡ መንገላታቱ። ራሳቸው እነዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የያዙትን ሰዎች ብንመለከት፡ 17 አመታት በሺህ የሚገመቱ ጓዶቻቸውን ሰውተው ነው እዚህ የደረሱት። ስለዚህ በአመጽና በትጥቅ ትግል ከሄድን መጋደላችን፡ በሰላማዊም ትግል ከሄድን እንዲህ እንደብርቱካን መታሰራችን መንገላታታችን አይቀርም። እንድን ዘንድ የግድ ያ ይሁን እያልኩ አይደለም። የአለምም ይሁን የኛ ታሪክ የሚያሳየው ግን ያንን ነው። ስለዚህ የአለም ሕግ በኛም ላይ ይፈጸም ዘንድ፡ ስለኛ ድህነት ብርቱካንም ባትሆን እንደ ብርቱካን ያለ ሰው መሰዋቱ፡ መንገላታቱ፡ መታሰሩ አይቀርም ነበር።
ከዚህ ቀደምም ብያለሁ፡ እስኪ ለአመታት ያልታሰረን ማንዴላን አስቡት። ከመታሰሩ በፊት ስለሞከራቸው ጥቂት እንቅስቃሴዎች ሰምቻለሁ። ከእስራቱ በፊት ስለሰራቸው አብይ ስራዎች ግን ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። ማንዴላን ማንዴላ ያሰኘው፡ ያው የ27 አመታት እስራቱ፡ ከእስራቱም መልስ የነበረው ፖለቲካዊ ስራ መሰለኝ። ልክ እንደ ብርቱካን ሁሉ አቶ ማንዴላም፡ በጎዶሎና ዘረኛ የፍትህ ስርአት ተዳኝቶ ነው፡ መንግስት በአመጽ ለመጣል በመሞከር ተፈርዶበት የእድሜ ልክ እስር የገባው። ማንዴላ በእስራቱ፡ ቀጥሎም ከተፈታ ወዲህ፡ ሁሉም ባይሆኑም፡ ብዙዎች የሚከተሉትና የሚያደምጡት እንዲሁም እንደ አርአያ የሚመለከቱት የሞራል ልእልናና ሰብእና ተከለ። ማንዴላ በእስራቱ እንዲሁም ከተፈታ በኋላ ባሳየው፡ መሀሪነት የመልካም መሪነትንና የታላቅ ሰውነትን መስፈሪያ አበጀ። ሰዎች፡ ህዝቦችና አገሮች በሱ ይዳኙና ይታረቁ ዘንድ፡ ማንዴላ ምክንያት ሆነ። በእስራቱ። በ27 አመት እስራቱ።
የሰብእና መስፈሪያ፡ የሞራል ልእልና
በኢትዮጵያ ውስጥ በስብእናዋና በግብሯ ልእልና ያገኘች መሪ ታስፈልገናለች። የሰማኒያ አመት ሽማግሌዎች ርስ በርሳቸው ሲባሉ፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ርስ በርሳቸው ሲሻኮቱ፡ እኔ እበልጥ እኔ እመራ ተባብለው ሲፈነካከቱና መሳቂያ ሲያደርጉን፡ “የለም፡ ከናንተ የተሻለች፡ ከሁላችሀም የበለጠች፡ በመከራና በእስራት የተፈተነች፡ በእስር በቆየችባቸው ወቅቶችም ያነበበችና፡ ብዙ የተመራመረች መሪ አለች” የምንላት፡ የምናፍራት፡ የምናከብራት፡ የምናደምጣት መሪ ታስፈልገናለች። ብርቱካን ራሷ የመረጠችው ሕይወት ስለሆነ ነው ይሄንን የምለው እንጂ አኔ ያንን እየጫንኩባት አይደለም። በቃሌ ላይ፡ “የህግ የበላይነት ሁሌም የምኖርለት፡ የምቆምለት፡ አንዳንዴም የምታሰርለትና ቁም ነገር ነው።” ብላለች። ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ ግድ እንደሆነው ሁሉ፡ እሷም እንዲከበርና በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን ለምትፈልገው ሕጋዊነትና ሕገ መንግስታዊነት፡ የሰብአዊ መብትና የህግ የበላይነት መታሰር፡ ከዚያም የከፋ መስዋእትነት ሊከፈል እንደሚችል የምታውቅ የገባት ታጋይ ነች። ብርቱካን፡ ልክ እንደ ክርስቶስ ሁሉ፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ እነሆ ከዚህ ቀን ጀምሮ ድነሀል ብሎ” በመፈወስ እንዳላቆመው፡ እነሆ የዚህችን ሀገር ድህነት ለማምጣት፡ ሰው አልገድልም፡ እኔ ግን መሞት ካለብኝ እሞታለሁ፡ ብላ ለመስዋእትነት የተነሳች ሴት ነች። ስለዚህ ያ ይሆን ዘንድ ታሰረች።
ይልቅስ የሚያሳስበኝ፡ ይልቅስ የሚያስጨንቀኝ
ይልቅስ፡ እኔ የሚያሳስበኝና ተግተን ልንከታተለው የሚገባው፡ ዘወትርም የምጸልየው፡ እንዳይመርዟትና በከንቱ እንዳይገድሏት ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች መግደል በሚያስፈልግበት ግዜ ሁሉ ከመግደል ወደኃላ እንደማይሉ የጫካውም የከተማውም ታሪካቸው ይናገራል። የዚህች ሴት በእስር መቆየት፡ ሰማእትነቷን እየጨመረው፡ በክብር እየሰቀላት፡ እየሰቀላት፡ እነሱን ደግሞ እያወረዳቸው፡ ሰላም እየነሳቸው፡ በየሄዱበት ሁሉ እየረበሻቸው እያወካቸው ስለሚሄድ፡ ይሄንን ለመገላገል ብለው በተራ መርዝ መርዘው ሊገድሏት ይችላሉ ነው ስጋቴ። ስለዚህ፡ ለትግላችን ምክንያት ትሆን ዘንድ በመታሰሯ ውስጥ ውስጡን እየተደሰትን፡ ለዓለም ማስጠንቀቅና እለት እለት መናገር ያለብን ብርቱካን ያለችበትን አደጋ ነው። ይህቺ ሴት ሕይወቷ በምንም መልኩ ቢያልፍ ተጠያቂዎቹ እነዚህ ሕወሀት/ኢህአዴጎች እንደሆኑ ማሳሰቡ ላይ ነው። በሌላ አነጋገር፡ እኛ ኢትዮጵያንም እሷንም የረሳናቸው እንደሆነ ነው የሷ ትግል ከንቱነት። እንጂ፡ እስራቷ አይደለም።
ሌላው የሚያሳስበኝ
እኔን የሚያሳስበኝ ሌላው ነገር፡ ብርቱካንን ቶሎ እንዳይፈቷት ነው። ይሄንን የምለው፡ ይሄንን ጽሁፌን ምስኪን እናቷ ወይንም ቤተሰቦቿ እንደማያዩት በመገመት ነው። ለነገሩ፡ ቢያዩትም፡ ብርቱካን ከዚህ በኋላ የቤተሰቦቿ፡ብቻ ሳትሆን የአገር ነች። የህዝብ ልጅ። ይህቺን የህብ ልጅ ቢፈቷት እኮ አለቀ፡ እኛንም “በመቀመጫችን” ቁጭ ሊያደርጉን ነው። አንደኛ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ እስረኞች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፡ አንድ ተጨማሪ የምንጠራው የታዋቂ እስረኛ ስም ልናጣ ነው። ጠላቶቻችን ደግሞ በተቃራኒው ብርቱካንን በመፍታት ማርክ ሊያሲይዙ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማሳደግ በጎ እርምጃ እንዳሳዩ ሊቆጠር ነው። ለተወሰነ ግዜም ቢሆን በአለም መንግስታት ዘንድ በጎ እርምጃ አሳዩ ተብለው ሊወደሱበት ነው። ስለዚህ ስጋቴ፡ ወጥታም ምንም መንቀሳቀስ እንደማትችል እየታወቀ፡ ቢፈቷት ነው። በተለይ ደግሞ ያንን የሀጢያት ደብዳቤ መልሰው ካስፈረሟት፡ ለጠላት ድርብ ድል ነው። ምንም ይሁን ምን፡ የብርቱካንን ሉአላዊ ውሳኔ አከብራለሁ። ነገ እንድትመራኝ የምመኛት ሴት ግን የምመርጠው እጅ ባትሰጥ ነው። ቢቆይም ከጸናች በመጨረሻ ድል የሷ በዚያም የኛ ነውና።
ሌላው ስጋቴ
ብርቱካን ብትፈታም ምንም የምትፈናፈንበት የፖለቲካ ሁኔታ እንደሌላ ግልጽ ነው። ይሄ ኢህአዴግ በፈጠረው ችግር ብቻ ሳይሆን የራሷ የብርቱካን ድርጅት ሰዎች በፈጠሩት ንትርክና ግብግብ ማለቴ ነው። እንደውም ተዉት፡ ኢህአዴግ ብዙ አያሳስበንም፡ አሁን ብርቱካን ብትፈታ እኮ፡ ትልቁ ራስ ምታቷ “እንዴት ትግሉን እንቀጥል” ሳይሆን፡ እንደገና ሽማግሌ ፍለጋ ልትንከራተት ነው። ፕሮፌሰር መስፍንነና ኢንጂነር ግዛቸውን ልትሸመግል። አቶ ታምራት ታረቀኝና አቶ አስራት ጣሴን ልትሸመግል። ብርቱካን ተፈትታ ከፖለቲካ ሕይወት ውጪ ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተፈትታ ልጇን ብታሳድግ ይሻላታል። ብርቱካን ግን ከዚህ በኋላ ያ ቀዳሚ ሕይወቷ፡ አይመስለኝም። ብርቱካንና ፖለቲካ ፖለቲካና ብርቱካን በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ላይፋቱ በተክሊል የተጋቡ መሰለኝ። ወይም ቆርበዋል። እግዚአብሄር አንድ ያደረገውን ደግሞ ማንም አይለያየውም። አሜን እንበላ። ብርቱካን የታጨችው ለታላቅ ተልእኮ ነው። እኛንና አገራችንን ለመምራት። ስለዚህ፡ በዚህ አሁን ባለው የአንድንት ድርጅት ሁኔታ ውስጥ ብትፈታ የሚቀጥለው የፖለቲካ ሕይወቷ ተራ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን በማስወገድ የተወታተበ ሊሆን ነው። በዚህ አኩራፊ በበዛበት ፖለቲካችን ውስጥ ደግሞ፡ አንዱን ወገን አስቀይማ አንዱን ወገን ልታሳዝን ነው። ስለዚህ ልክ እንደማንዴላ ወሳኝ የሆነ የተሰሚነት ደረጃ ላይ ሳትደርስ እንዳይፈቷት ነው ጸሎቴ።
ወደፊርማው ልውሰዳችሁ
ሌላው ስጋቴ ደግሞ ያንን ከዚህ ቀደም ፈርማ አሁን ካደች የሚሉትን ነገር ፈርማ የወጣች እንደሆነ ነው ብያለሁ፡ ከላይ። በፍጹም። “ምርጫ 1997 ዓ.ምን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት ሕገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገ መንግስቱ የተደራጁ የመንግስተ አካላትን ለመለወጥ ያደረግኩት ሙከራ ስህተት መሆኑን አምኜ… የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ በፈጸምነው ስህተት መጸጸታችንን ተገንዝበው በአገራችን ባህል መሰረት ለፈጸምነው ስህተት ይቅርታ እንዲያደርጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን።”የሚለውን ወረቀት ፈርማ እንዳትወጣ ነው። ያላደረገችውን? ያልፈጸመችውን? ማንዴላንና መሰል ታሪካዊ መሪዎችን መሆን ካለባት፡ በፍጹም እንዲህ ያለው ቅሌት ውስጥ መግባት የለባትም። ምክንያቱም፡ ማንዴላ ያንን አላደረገም። እንደውም እሱማ፡ በዘረኛው የአፓርታይድ ፍርድ ቤት ዳኛ ፊት፡ ደረቱን ነፍቶ፡ በኩራትና በልበ ሙሉነት፡ ነው ቃሉን የሰጠው። ምክንያቱም፡ ለነጻነቴ መታገል የሰውነት ግዴታዬ ነው አይነት ነገር ነው። ስለዚህ ብርቱካን፡ ያደረገችዉን እንጂ ከእስር ለመፈታት ስትል ብቻ፡ ያላደረገችዉን ማመን መፈረም የለባትም። እዚህ ጋር ግን ከዚህ ቀደም የፈረሙበት ሁኔታ ካለ፡ ያ የተደረገበት ሁኔታ የተለየ ስለሆነ፡ ከዚህ ቀደም ያንን ባደረጉት ሰዎች ላይ በምንም መልኩ ሞራላዊ ፍርድ መስጠቴ አይደለም። ድሮ ለስልት ነበር ልንል እንችላለን። አሁን ግን ሽንፈት ነው የሚሆነው።
ባይሆን መልካም ነበር፡ ከሆነ ግን መታሰሯ ለኛ ትርፍ ለጠላት ደግሞ ኪሳራ ነው
በነገራችን ላይ፡ ከቫንኩቨር እስከ ቶሮንቶ፡ ከሲያትል እስከ ዲሲ፡ ብርቱካን ሚደቅሳና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ብለው ከሚጮሁት ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነኝ። እኔ፡ ኢህአዴግ/ሕወሀትን ከማሳጣትና የሰሩት ስራ ስህተትና ብላሽ እንደሆነ ከማሳየት አንጻር በየሰልፉ “ፍሪ ብርቱካን ሚደቅሳ” ብዬ ልጩህ እንጂ፡ እንደውም ኢህአዴግ ብርቱካንን ማሰሩ ለኛም ለራሷም ለብርቱካንም እንደውለታ ነው የምቆጥረው። ይህቺ ሴት ባትታሰር እኮ፡ አስቡት፡ የት ትሆን ነበር ይሄንን ግዜ? እንኩዋንስ ለሳካሮቭ ሽልማት ልትታጭ፡ እንኩዋንስ ልንሰለፍላት፡ እንኩዋንስ ስሟን ይዘን እንደ ነጻነት ታጋይ ልንዘምርላት፡ እንኩዋንስ ልናጨበጭብላት፡ እንኩዋንስ ልንዘምትላት፡ እንደውም አንዳንዶቻችን እንዘምትባት ነበር። በታሰረች ማግስት እንኩዋን ባንድ ድረ ገጽ ላይ ተለጥፎ ወዲያዉኑ የተነሳውን አሳፋሪ ጽሁፍ አታስታውሱትም? ካላስታወሳችሁ አላስታውሳችሁም። ዋናው ነገር፡ ለብርቱካን መታሰሯ ይበጃታል። ለኛም ጭምር።
በርግጥ ትጎዳ ይሆናል። ግን ደግሞ አንደኛ፡ ያ የኛ ግምት ነው። ይሄ ግምታችን እስር ቤታ ባጠቃላይ ጎጂና ላተፉ ብቻ የሚገባ ነው ከሚል ግምትና እምነት የመነጨ ነው እንጂ፡ እስር ቤት ከገቡበት በኋላ፡ ብዙ ደራሲዎችን ያፈራ፡ ብዙ ፈላስፋዎችን የወለደ፡ ብዙ መሪዎችን ያበቀለ ተቋም ነው። ማንዴላን አስር ግዜ አልጠቅስም። የማንዴላ ስብእና ሙሉ በሙሉ እስር ቤት ተገነባ ማለቴም አይደለም። የእንግሊዙን ፈላስፋና ጸሀፊ በርትራንድ ረስልን እያነበብኩት ነበር ሰሞኑን። በአንደኛ የአለም ጦርነት ማለቂያ ሰሞን፡ የእንግሊዝን በጦርነቱ መሳተፍ ተቃውሞ በመጻፉ ምክንያት፡ ለስድስት ወር ታስሮ ነበር። መጽሀፍ አይከልክሉኝ እንጂ፡ መታሰሬ ባንድ በኩል መልካም ነገር ነው ሲል ይናገራል። አንዱ ምክንያቱም በመታሰሩ ምክንያት፡ በእስር ቤት ብዙ መጽሀፍትን ለማንበብና ለመጻፍ ችሎ ነበር። ብርቱካን መጽሀፍ እንድታገኝ፡ ይፈቀድላታል ወይ? እኔ እንጃ። ይፈቅዱላት ይሆናል ብዬ ገምቼ ነው እንጂ፤ በምንም መልኩ የዚያን ዘመኑን የእንግሊዝ እስር ቤት፡ ከአሁኑ ዘመን የኢህአዴግ እስር ቤታ ጋር አንድ አድርጌ አይደለም። በተለይ ረስል የታሰረበት የእንግሊዝ እስር ቤት ለኛ ቤተ መቅደስ አይነት ነገር ነበር።
ብርቱካን ባትታሰር ኖሮ፡ ከታሰረች በኋላ ያመለጧትን/ያመለጠቻቸውን ፖለቲካዊ ክስተቶች ስንመለከት፡ እንደውም እስር ቤት ከነበረው በባሰ ትሰቃይበቻው ነበር። ምርጫው አይቆጫትም። ሌላው መድረክ ነው፡ እሱም አይቆጫትም። ስተፈታ የሷ ነው። መረራም፡ በየነም፡ ገብሩም፡ ስዬም፡ ነጋሶም አጎንብሰው የሚቀበሏት መሪ ሆና ነው የምትወጣው። ብርቱካን በመታሰሯ፡ የሰላማዊ ትግል ስልቷን ይነቅፉ የነበሩ ቡድኖች ትችትና ጭቅጭቅም ቀረላት እንጂ፡ ባትታሰር ብዙ የሁለትዮሽ ፍዳ ይጠብቃት ነበር። ብርቱካን በመታሰሯ ነው ከዚህ በታች ያሉት አለማቀፍ ጸሀፊዎች ሁሉ ይሄንን ያሉት። የአውሮፓዋ አጋራችን ሀና ጎበዜም ለሳካሮቭ ሽልማት ያጨቻት በመታሰሯ ነው። ባትታሰር፡ ከኛ በምን ትበልጣለች? ከኛ እንዳንዱ ሆና ትቀር ነበር እንጂ። እስኪ ብርቱካን ከታሰረች በኋላ በአለምአቀፍ መድረኮችና መገናኛ ብዙሀን ከተጻፉላትና ከተባሉላት ጥቂቶቹን፡ እንመልከት።
የተለያዩ ጸሀፊዎችና ዜና አውታሮች ስለብርቱካን ምን አሉ?
በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ጋዜጠኞች፡ ጸሀፊዎች፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ዜጎች ስለብርቱካን የተለያዩ ነገሮችን ብለዋል። ጃኑዋሪ 9፡ 2010 ባወጣው Jailed but not Forgotten: Birtukan Mideksa, the Most Famouሰ Prisoner in Ethiopia (የታሰረች ግን ያልተረሳች፤ ብርቱካን ሚደቅሳ፡ ታዋቂዋ የኢትዮጵያ እስረኛ) በሚል ጽሁፍ፡ “ሜይል ኤንድ ጋርዲያን” የተሰኘው ታዋቂ የእንግሊዝ መጽሄት፡ ስለብርቱካን በሰፊው አትቷል። የእናቷን፡ የጓደኞቿን፡ የቤተሰቦቿንና የመንግስትን አስተያየት የያዘው ይህ ጽሁፍ፡ የብርቱካን እስር ምክንያት በመንግስት የተጠቀሰው እንዳልሆነ ይጠቁማል። የሮይተረሱ ባሪ ማሎን፡ ለመጀመሪያ ግዜ ብርቱካንን በ2007 ከእስር እንደተፈታች ሲያናግራት በጣም ጠንቃቃ ከመሆኗ የተነሳ፡ “ከአምስት ደቂቃ ንግግር በኋላ ውይይታችን ምንም ታሪክ እንደማይወጣው ገምቼ፡ የድምጽ መቅረጫ ቴፔን ዘጋሁት” ይላል። ስለዚህም “የዚያንግዜው የብርቱካን ጥንቃቄ ትክክል እንደነበር ያሁኑ እስራቷ ይመሰክራል” ብሏል። ባሪ ማሎን ቀጥሎም፡ ብዙ ደጋፊዎቿ ብርቱካንን “የኢትዮጵያዋ ኦንግ ሳን ሱ ኪ” ብለው ይጠራቷል። በማያስገርም መልኩ፡ የመንግስት ባለስልጣናት ግን ይሄንን ማመሳሰል አይቀበሉትም ሲል ጽፏል።
አምነስቲ አለማቀፍ ብርቱካንን “የህሊና እስረኛ” ብሏታል። ሜይል ኤንድ ጋርዲያን፡ “ብርቱካን ለአድናቂዎቿ በኢትዮጵያ መራራ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደአስታራቂ አምሳል ትታያለች” ሲል ጨምሮ ዘግቧል። የጠላትንም አስተያየት ብንዘግብ የኛን ዘገባ ሚዛናዊ ያደርገዋል። ሜይል ኤንድ ጋርዲያን፡ ብርቱካን ለአድናቂዎቿ አስታራቂ ትሁን እንጂ፡ ለተቃዋሚዎቿ ግን “በመታሰሯ ብቻ የገዘፈች ነገር ግን ይህቺን ትልቅ አገር ለመምራት የእውቀት ብቃቱም ይሁን ስትራቴጂክ ክህሎቱ የሌላት ሰው ነች” ይሏታል ሲል አትቷል። እኛም የምንፈልገው እኔ የምከራከረው ይሄው ነው። የብርቱካን መታሰር፡ ይሰቅላታል። መታሰሩ ማንዴላን እንደሰቀለው ማለቴ ነው። አንዳንዴ ከመታኮስ፡ መተሳርም ትግል ወይንም ስራ ነው።
የእንግሊዝ ዜና አውታር ቢቢሲ፡ ብርቱካን በታሰረች ማግስት “ይቅር የተባለችው ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ታሰረች” ብሎ ባወጣው ዘገባ የአዲስ አበባ ዘጋቢውን፡ ኤሊዛቤት ብለንትን ጠቅሶ “በ2005 ምርጫ ታላቅ ውጤት ያስመዘገበው ቅንጅት አንደኛዋ ወጣትና ግርማ ያላት መሪ” ብሎ አሞግሷታል። የካናዳው ታዋቂ መጽሄት መክሊንስ ጸሀፊ ናንሲ ማክዶናልድ፡ በ2010 ሚያዚያ ኢትዮጵያን ጎብኝታ ከተመለሰች በኋላ ስለ ብርቱካን ስትጽፍ፡ ልክ እንደ እንግሊዙ መጽሄት፡ እሷም “ብርቱካንን ታዋቂዋ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ” ትላታለች። ናንሲ ብርቱካንን፡ “ላለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲና የለውጥ ምልክት ሆናለች” ብላታለች። የውቦች ስደት የሚለው ፊልም ደራሲ አሜሪካዊው ክሪስ ፍላህርቲ፡ ልክ እንደ በርማዋ ኦንግ ሳን ሱ ኪ በታሰረችበት እስር ቤት ወደ ሰማእትነት እያደገች የመጣች ሴት ይላታል። በነገራችን ላይ፡ ክሪስ ፍላህርቲ፡ የብርቱካን ሰማእትነትና ፍቅር ያፈራው ታጋይ አሜሪካዊ አጋራችን ነው። ስለዚህም ነው በግንቦት 2010 ዓ.ም. ብርቱካን እንድትፈታ የመጠየቅ የአንድ ሳምንት የረሀብ አድማ ያደረገው። ባትታሰርስ ኖሮ?
እስክድር ነጋ፡ ብርቱካን ሚደቅሳን “የማትበገረዋ አንበሳ” ይሏታል ይላል። ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና፡ የብርቱካንን እስር በተመለከተ ሲጠየቁ “ብርቱካን የኢትዮጵያ ማነዴላ ነች” ብለዋል። በDecember 2009 Amnesty International የብርቱካን ሚደቅሳን እስር “አግባብ ያልሆነና በፖለቲካ የተነሳሳ “unjust and politically motivated” ብሎ ፈርጆታል። በተጨማሪም አምነስቲ አለማቀፍ፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ከእስር እንድትፈታ በመጠየቅ አለማቀፍ ዘመቻ ጀምሯል።
ኢህአዴግ ግን፡ የብርቱካን እስር የህግ እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም ብሏል።[8] አቶ መለስ ብርቱካንን አምርው ከመጥላታቸው የተነሳ፡ የሷ ጉዳይ ሲነሳ የሚይዛቸውን ደንፎ ሌላ ቦታ አላየሁትም ሲል ይናገራል፡ የቀድሞው አዲስ ነገር፡ ታምራት ነገራ። አቶ ዜናዊ በመስከረም ወር በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር ላይም የብርቱካንን መታሰር ትክክለኛና ህጋዊ ለማስመሰል ቢሞክሩም፡ ምናለ ድጋሜ ይቅርታ ጠይቃ በገላገለችን አይነት ስሜት አንጸባርቀዋል። የብርቱካን መታሰር ብቻ እኮ፡ መለስን ራሱን በሄደበት እየተከታተልን ለማሰቃየት ረዳን። ብርቱካን መታሰሯ አግባብ አይደለም። በመታሰሯ ግን ከፍተኛውን ኪሳራ የከሰረውና ያንን ያደረገበትን ቀን የሚረግመው ሕወሀት/ኢህአዴግ ነው። ብርቱካንን ማሰሩ ለኛና ለብርቱካን ትልቅ ፖለቲካዊ ትርፍ ነው ባይ ነኝ። ለነገሩ፡ ስለብርቱካን መታሰር ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከዚህም በላይ ማለት ይቻል ነበር። ግን ይበቃኛል። እስከዚያው ግን፡ ቶሎ ሳይፈቷት፡ ኢትዮጵያ የአያሌ ኢትዮጵያዊያን እስር ቤት መሆኗን በብርቱካን እናስመስክርበት። እንደውም ኢህአዴግ ሳይሆን ብርቱካንን ለመፍታት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ያለበት፡ ብርቱካን ራሷ ለመፈታቷ የሌሎች ፖለቲከኞችን መፈታት እንደቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አለባት። ለዚያ ሁሉ ግን የኛ እንቅስቃሴ ይወስነዋል። በያለንበት እንበርታ።
አለቃ ተክሌ ነኝ። ከቫንኩቨር-ኦታዋ፡ ካናዳ። መስከረም፡ 2003