ለ”ፉርሽ ባትሉኝ” ነዉ ወይ ሽጉዱ?
ከሸንቃታዉ ዘካሊፎረኒያ
ታሪክ ራሱን በአዲስ መልከ እንደሚደግም ከኢትዮጵያ ታሪክ እንኳን ብዙ ተምረናል። ቁጥሩ አንድ መቶ ሀያ የነበረዉ የደርግ አመራር አባላት በመፈንቅለ አገዛዝ ሙከራና በዉስጥ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ወደ ከሰላሳ በታች ያሽቆለቆለዉ ያለ ምክንያት አልነበረም። ባለስልጠናት ሲሾሙና ብዙም ሳይቆዩ ይሻሩ እንደነበረ ብዙ ታይቷል። “ማን ነህ ባለሳምንት ያስጠምድህ በአስራ ስምንት እኔ ነኝ የምትል የመንጌ ወዳጅ” እየተባለ ሲቀለድ የነበረዉ ትዝ ይለኛል። መንግስቱ ሀይለማርያም ያካሂድ የነበረዉ የመሾምና የመሻር ዘመቻ የስልጣን እድሜዉን ማራዘም ይችል ዘንድ ታማኝ ሎሌዎችን በዙሪያዉ በማሰባሰብ ለስልጣኑ ደግሞ አስጊ ናቸዉ ብሎ የሚጠረጥራቸዉን ደግሞ መንጥሮ ለማዉጣት እንዲያስችለዉ ነበር። ይህን ካላደረገ ደግሞ የእነተፈሪ ባንቲ እጣ ፈንታ ለእርሱም እንደሚደርሰዉ ያዉቅ ነበር። በእንደዚህ አይነቱ ዘዴ ነበር መንግስቱ ሀይለማርያም የደርግን ስልጣን ከመቶ ሀያ አባላቱ እጅ በአብዮትና በብሔራዊ ደህንነት ስም ወደ ራሱ እጅ አስገብቶ ለፈላጭ ቆራጭነት በቅቶ የነበረዉ። ትርፉ ጠላት ማብዛትና አላፊ አግዳሚዉን ሁሉ እንደጠላት መቁጠር ብቻ ሳይሆን የስነ ልቡና ቀዠት የሚያስከትል ሆኖ መገኘቱ ነዉ። ከመንግስቱ ሀይለማርያም “ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ሆኖ መቅረት መለስ ዜናዊ የተማረዉ ነገር አለ ብዬ ለመናገር በጣም እፈራለሁ፤ ማለትም ስልጣን ላይ ለመቆየት ከሚነደፈዉ ስትራቴጂያዊ ፕላንና ከሚወሰዱት እርምጃዎች አንጻር።
ከታሪክ እንደምንረዳዉ አምባገነኖች አንድ ሁለንተናዊ ባህርይ አላቸዉ። ያም ደግሞ ሀቅን “አለመቀበል” (denial) ተብሎ የሚታወቀዉ ነዉ። ነባራዊና ስሜታዊ ሁኔታዎች የሚያስከትሉትን የፖለቲካ ጠንቆች አምኖ መቀበል ለአምባገነኖች የሚዋጥ አይደለም። ጠላት እንዳያበዙ የሚመክራቸዉን እንኳ እንደ ጠላት የሚቆጥሩና የሚወቅሳቸዉን ደግሞ እንደ አገር ከሀዲ የሚያዩ ወፈፌዎች ናቸዉ አምባገነኖች። በራሳቸዉ የደህንነት ጠባቂዎች፣ በመፈንቅለ አገዛዝና በወታደራዊ ንቅናቄዎች ህይወታቸዉ ያለፈ አምባገነኖች ቁጥር ትንሽ አይደለም። ከእብሪትና ከማንአህሎኝነት ጋር በደምና በስጋ የተዋሀዱ ናቸዉ።
የመለስ ዜናዊ ሚስጥራዊ ስተራቴጂ ቀስ በቀስ እርቃኑን እየተጋለጠ ነዉ። የሶሪያ ፕሬዚደንት የነበረዉ ሀፌዝ አሳድ ልጁን ባሻር አል አሳድን በፕሬዚደንትነት ተክቶ ሞተ። የግብጹ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ ደግሞ የመጨረሻ ልጁ የሆነዉ ገማል ሆስኒ ሙባረክ በፕሬዚደንትነት እንዲተካዉ ለማድረግ ትልቅ ጥረት እያደረገ ነዉ ያለዉ። የሊቢያዉ ወፈፌ ፕሬዚደንት ሙአማር ጋዳፊ እንዲሁ ልጁ የሆነዉ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ የሚቀጥለዉ የሊቢያ ፕሬዚደንት እንዲሆን ጥርጊያ መንገድ እያበጀለት ነዉ። እንዲህ አይነቱ አይን ያወጣ ድርጊት የሚከሰተዉ በየአገሩ ታማኝ መሪ ጠፍቶ ሳይሆን ከራስ ወዳድነትና ማንንም ካለማመን የተነሳ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም። ዲሞክራሲያዊ አሰራርና የህግ የበላይነት የሌለበት አገር ሁሉ እንዲህ አይነቱ ሳይነግሱ ንጉስ መሆን አይቀሬ ክስተት ነዉ። መለስም በዚህ የፖለቲካ አዝማሚያ ሲያንዣብብ የነበረ መሆኑ እንዳይታወቅበት ነዉ መሰለኝ አንዴ ስልጣኔን እለቃለሁ፣ አንዴ ደግሞ ጡረታ እወጣለሁ እያለ ለህዝብ የማዘናጊያ ወሬ ሲያስወራ የነበረዉ።
ዘርና ታማኝ አገልጋይነት እንኳ ዘለቄታ የሌላቸዉ መሆኑ በግልጽ የምናየዉ ነገር ሆኗል። ስንቶቹ የትግራይ ልጆችን መለስ ጥግ እንዳስያዛቸዉ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ሰንበት ብሏል። ለቁልፍ ስልጣን ሊታመን የሚችለዉ ግለሰብ በተግባር የተፈተነ የቅርብ ዘመድ ወይም የቤተሰብ አባል ወይንም በጋብቻ የተሳሰረ ብቻ እንደሆነ መለስ ከሚወስዳቸዉ እርምጃዎች መረዳት ይቻላል። በረከት ስምኦን ላይ መለስ ሙሉ እምነት ባይኖረዉም ይወደዋል ብዬ እገምታለሁ። እንዲሁም ወዲ ኤርትራም ስለሆነ አሁን መለስ ኢሳያስን ለመፈንገል ሲል ለሚያደርገዉ የፖለቲካ ሽር ጉድ በኤርትራዉያን ተቃዋሚዎች ዘንድ ርካሽ ህዝባዊ ገናናነት (cheap popularity) ለማግኘት እንደሚረዳዉ አልጠራጠርም። ከዚያም ኤርትራ ዉስጥ የመንግስት ለዉጥ ለማምጣት የወጠናቸዉ ነገሮች ከግባቸዉ ሲደርሱ ያኔ በረከት ስምኦንን በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ያደርገዋል ወይንም አንድ ትልቅ ሹመት ይሰጠዋል ወይንም ይፈነግለዋል። መለስ አፍ አዉጥቶ አይናገር እንጂ በተግባር ለሁሉም እያስተላለፈ ያለዉ መልእክት ቢኖር ከአሁን ወዲያ ያለዉ አሰራር “እንደ ንጉሱ አጎንብሱ” ነዉ፤ እናም “ከተቀበላችሁ ተቀበሉ እምቢ ካላችሁ ደግሞ ገደል የመግባት መብታችሁ የተጠበቀ ነዉ” አይነት ነገር ነዉ የሚመስለዉ። ማን ያዉቃል ይኼኔ “ተጋዳላይ ጓዴ አይበልህ ከፋ፣ ሁሉም ይለቃል በየወረፋ” እያለ የወያኔና የኢህአዴግ የፖሊት ቢሮዎች አባል ከሆነቺዉ ከቀዳማዊቷ ባልተቤቱ ከአዜብዬ ጋር በምጸት አስረሽ ምቺዉን እያስነካ ይሆናል። አያደርገዉም አልልም።
የአዲሱ ለገሰ፣ አርከበ እቁባይ፣ ስብሀት ነጋ፣ አባ ዱላና ስዩም መስፍን የመሳሰሉት በጡረታ መልክ ከቁልፍ የወያኔና የኢህአዴግ ስልጣን መገለል ምንም አይነት የስልጣን ስጋት እንደማያስከትልበት መለስ ጠንቅቆ እንደሚረዳ አልጠራጠርም። ሁሉም ራሳቸዉን በገንዘብ ሀብት ያዳበሩና የሙስና ታናሽ ዘመዶች ለመሆናቸዉ የኢትዮጵያ ህዘብ ጠንቅቆ ያዉቃል። ይሄኔ መለስ መረጃ አሰባስቦ በእያነዳንዳቸዉ ስም ፋይል ከፍቶ ሳያስቀምጥ አይቀርም ብዬ እገምታለሁ። ከእነርሱ አንዳቸዉ እንኳ ቢያንገራግር እንደመንግስቱ ሀይለማርያም የፍየል ወጠጤ ባያስዘፍንም የታምራት ላይኔን እጣ እንደማይነፍግ ጥርጥር የሌለዉ ነገር ነዉ የሚመስለኝ። መለስ ታምራት ላይኔን መተረቻ ሳያደርገዉ እንደማይቀር እገምታለሁ “በሬ ሆይ ሞኙ በሬ ሆይ፣ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ፣ እልም ካለዉ ገደል ገብተህ ቀረህ ወይ” እያለ። እነአዲሱ ለገሰም “ጎመን በጤና” እያሉ የዘረፉትን ገንዘብ በሰላም መብላትን እንጂ ከአሁን በሗላም እስር ቤት መግባትን የሚፈልጉ አይመስለኝም። ጮሌዉ መለስ ማኖ (hand) ያላስነካዉ ሰዉና ቁስሉን ያልደረሰበት ሰዉ እንደሌለ ነዉ የምረዳዉ። ይህ ስትራቴጂ ደግሞ እያንዳንዱን ባለስልጣን ለመቆጣጠርና ክህደት እንዳይፈጽምም ጭምር ለማድረግ ያስችለዋል። መለስ የቀረዉ ነገር ቢኖር “አሻፈረኝ፣ አሻፈረኝ፣ ዋስም አልጠራ ናና ሞክረኝ” እያለ መዝፈን ብቻ ነዉ። የመለስ ደጋፊዎችና አጨብጫቢዎች ደግሞ “ነገሰ ወይ መለስ ነገሰ ወይ፣ መች ነገሰና፣ መች ነገሰና፣ ያስባል ገና” እያሉ መዝፈን ብቻ ነዉ የቀራቸዉ።
ኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ ባደረገዉ ንግግር የህዝብ ግኑኝነት ፖለቲካ ኪሳራዉ የበለጠ ኪሳራ ዉስጥ እነደገባ በብዙ ድህረ ገጾች ተዘግቧል። የስታርባክ እና የሀምበርገር ጀግኖች እያለ የሚወርፋቸዉ ዲያሰፖራ ኢትዮጵያዉንን እያማረረ መነጫነጩ አይቀርም ምዕራብ አዉሮፓዉያንና አሜሪካ ፊት በነሱት ቁጥር። የህዝብ ትኩረት ወደ ተለያየ አቅጣጫ እንዲሄድ በየጊዜዉ የመነጋገሪያ አጀንዳዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን እያፈራረቀ መጠቀሙ አይቀርም። እነዚህም እርምጃዎች የስልጣን ሸምቆቆዉን እንዲያጠብቅ ጊዜ ለማግኘት ይረዱታል ብዬ እገምታለሁ።
ለካስ ቅጥፈት ኖሯል እስከ አሁን ድረስ መለስ ስልጣኔን እለቃለሁ፣ ጡረታ እወጣለሁ፣ እንዲሁም አመራር መስጠቱ ሰልችቶኛል፣ ምንጥሴ ቅብጥርሴ እያለ ሲያስወራ የነበረዉ። አይኑን ያፈጠጠ ጥርሱን ያገጠጠ ቅጥፈት እንደሆነማ አየነዉ እኮ። መለስ ካልቀጠፈ የሚያመዉ ይመስለኛል። ከአሁን በሗላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ሗላ እንደማይል ይገባኛል። ጭካኔዉም የዚያኑ ያህል ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ሱሪ የለሽ የሆኑት የፓርላማ አባላትም መለስ ያለዉን ከማጽደቅ በስተቀር ምንም ልዩ ነገር አይሰሩም፤ ትርፉ ምን ጣጣ እንደሚያስከትል አሳምረዉ ስለሚያዉቁ። ህወሀትን፣ ብአዴንን፣ ኦሆዴድንና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችን አሞሌ ጨዉ ከሚያመላልሱት የእንደርታ ብረት ለበስ አህዮች ባላነሰ ደረጃ ነዉ መለስ የተጠቀመባቸዉ። ያ በትጥቅ ትግል ያለቀዉ ሰዉ ሁሉ ለካስ መለስን ለማንገስ ነበር። መለስ ዲሞክራሲ እያለ ሲለፍፍ የከረመዉ አፄ መለስ ተብሎ ለመጠራት ነበር ለካስ። እግዚኦ የሚያሰኝ ቅጥፈት ነዉ። አይን ያወጣ ፉርሽ ባትሉኝነቱ ግን በጣም ያሰተዛዝባል። ሀቁን ተናግሮ የመሸበት ማደሩ ይሻለዉ ነበር። ሆኖም ግን ቅጥፈቱ ደሙ ዉስጥ ያለ መሆኑን ዘግይተን አወቅን። ለካስ ለፉርሽ ባትሉኝነት ነዉ ሽጉዱ። አፄ መለስ ለመባል።