ብርቱካን የአንድነት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ መሪ ነሽ- በቫንኮቨር ካናዳ የአንድነት የድጋፍ ኮሚቴ

ውድ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የአንድነት ለዴሞክራሲና የፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር
አዲስ አበባ
እኛ በቫንኮቨር ካናዳ ነዋሪ የሆን ኢትዮጵያዊያንና ተውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአንድ አመት ከዘጠኝ ወራት የእስር
ጊዜ በኍላ ከኢትዮጵያ ህዝብ፤ ከልጅሽ፤ ከወላጅ እናትሽና ከመላ ቤተሰቦችሽ ብሎም ከትግል አጋሮችሽ ጋር በመቀላቀልሽ
እንኵን ደስ ያለሽ እንላለን።
ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የማስተካከል ትግል፤ የሕዝብ በነጻ ሀሳብን
የመግለጽ መነፈግ፤የመደራጀትና የመሰብሰብ እንዲሁም ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል የሚዳኝበት ስርአት እንዲሰፍን፤
ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ ክልሎች ከቦታ ቦታ በነጻ በመዘዋወር የመኖርና የመስራት ብሄራዊ መብታቸው እንዲከበር በግንባር
ቀደም ተሰልፈው ከሚታገሉት ውድ ወገኖቻችን አንዷ በመሆንሽ በዚህ ሂደት ለምታደርጊው ትግል ልባዊ ድጋፋችን ስንገልጽ
በታላቅ ደስታ ነው።
መታሰርሽ፤መንገላታትሽ፤ በጨለማ እስር ቤት መማቀቅሽ ለፖለቲካ ስልጣን ብቻ የታቀደ ሳይሆን ህዝብ መሰረታዊ
መብቱ ተከብሮ፤ እርስ በእርሱ ተፈቃቅሮ፤ ተከባብሮ ተመካክሮ የሀገሩን መጻኢ እድል እንዲወስን የማስቻል አላማ ላይ
ያነጣጠረ መሆኑን ሰፊ ግንዛቤ ተገኝቷል። በዚህም አላማ ላይ ተመስርቶ ነው ሕዝቡ ለአንቺና ለፓርቲው ከሀገር ቤት እስከ
ውጭ፤ከሊቅ እስከ ደቂቅ የድጋፍ ድምጹን እያሰማ ያለው። በአገዛዙ ስትታሰሪም ሕዝቡም አብሮ በመንፈስ ታስሯል።
በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተቃውሞውን ከአጥናፍ አጥናፍ አስተጋብቷል።የኢህአዴግ ባለስልጣናት በተንቀሳቀሱበት አቅጣጫ
ሁሉ እየተከተለ አንቺና ሎሎች የፖለቲካ እስረኞች ከስር እንድትፈቱ ወጥሮ ይዟል።
በዚህ ወቅት አንቺና መሰሎችሽ በእነርሱ የጸጥታ ኃይሎች በየእስር ቤቱ ስትንገላቱ መለስ ዜናዊና አቋራሾቹም
በበኩላቸው ጧት ማታ ሰላማቸው ደፍርሷል፤ በህዝብ ጥያቄ አምሮአቸው ተወጥሮ የህሊና እስረኞች እንደነበሩና አሁንም ገና
በሽዎች የሚቆጠሩት ቀሪ እስረኞች እስኪፈቱ ደረስ ሰላም አያገኙም እየተካሄደ ያለው ትግልም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤
የህብረት ትግል ውጤቱን በትንሹ በአንቺ መፈታት ምልክት ታይቷል። አሁንም የኢህአዴግን ሹሞች የምንጠይቃቸው
እራሳችሁን ኮድኩዳችሁ ሕዝቡን አትሰሩት ነጻ ሁናችሁ ህዝቡን ከጥቅል እስር ቤት ፍቱ የሚል ነው ።
አንቺና ሌሎች ታሳሪዎች የአካል ጉዳት ደረሰባችሁ። በተቃራኒው የኢህአዴግ ባለስልጣናት ግን በራሳቸው መጥፎ
ውሳኔ የህሊና እና የአካል ነጻነት ተገፈፉ። በዚህ የተነሳ በደረተ- ደንዳና ዘበኛ መውጫ መግቢያቸው ይጠበቃል፡ በዚህም
ሳያበቃ የጥይት ማስታገሻ ብረት ለብሰው ይንቀሳቃሳሉ፤ በቅርብ ሰዎቻቸው ላይ እምነት በማጣታቸው የተነሳ የሚበሉት
ምግብ ሳይቀር ይፈተሻል፤ እየተቀመሰ ይሰጣቸዋል፤ በዚህም አላቆሙም ባደረባቸው ፍራቻ ምክንያት እንደ ጫካ አውሬ
በብረት ተከበው ይጠበቃሉ።ይህን ነጻነት ብለው የሚጠሩት ከሆነ ፍርዱን ለራሳቸው መተው ብቻ ነው። ብርቱካን አንቺ ግን
ነጻ ሰውና የህዝብ አለኝታ ነሽ፤ ህዝቡ ባለፈው ድምጹን ሰቶሻል ለዚህም ክቡር ዋጋ ከፍለሽበታል፤ ወደፊቱም የተዛባው
ስርአት እስኪቃና ድረስ ገና ይኽው ትግል ይጠብቅሻል። በዚህ ረገድ ከእኛ የሚጠበቀውን ዲፕሎማሲያዊ፤ የገንዘብና
የማቴሪያል ድጋፍ ባለንበት ሀገር አጠናክረን እንቀጥላለን።
ከእስር እንድትወጭ በተደረገው የህብረት ትግል ገዥወቹ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሳይወዱ በግድ ከመዳፋቸው
መውጣትሽን በሚገባ እንደምትረጅው ይገባል። እንደነርሱ ፍላጎትማ ቢሆን የአንቺ የመፈታት ጉዳይ ያከተመ ነው፤ ብለው
ተስፋ ሊያስቆርጡን ከጅሎአቸው ነበር። መለስ ዜናዊ ይህንኑ ከደሰኮሩልን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ነው እንደ እግር ሳት
ተለብልበው ውሳኔአቸውን እንዲአጥፉ የተገደዱት። አሁንም አሳሪ፤ ደብዳቢ፤ አንገላች፤ መብት ገፋፊ፤ የሆኑት የኢህአዴግ
ኃላፊዎች ላደረሱብሽ በደልና ግፍ ይቅርታ መጠይቅ ሲገባቸው፤ “ይቺ ወንፊት አዙራ ነፋች እንዲሉ” ለፈጸሙብሽ ግፍ አንቺ
ተመልሰሽ ይቅርታ ጠያቂ እንድትሆኝ ሲደረግ ይህ አሰራር የስርአቱን ሰብአዊት መብት ገፋፊነትና ጨቋኝነት ከሚያረጋግጥ
ውጭ ሌላ የሚፈይደው እውነታ እንደሌለ የተረጋገጠ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ አንቺን ብርቱካን ለብርቱካን ሳትሆን ብርቱካን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት፤ ንብረት፤ ክብር፤
የፍትህ ፤ የአንድነት፤ የአብሮ መኖሩ መለኪያውና ምልክቱ አድርጎ እየተከተለሽ ነው። በዚህ በፈተና ወቅት ሕዝብ
የአሳደረብሽንና የሰጠሽን አደራና ሀላፊነት እንደምትወጭ ሙሉ እምነታችን ነው።
ስለሆነም መጭው የትግል ጊዜሽ መራራና ፈታኝ እንደሚሆን ይበልጥ ተዘጋጅተሽ የሰላማዊ ትግሉን አጠናክረሽ
ከአጋሮችሽ ጋር ለመቀጠል በእስር ላይ በነበርሽበት ጊዜ በድርጅቱ ላይ የደረሰውን ውጫዊና ውስጣዊ ችግር እንደ አንድ ዳኛ
የዳኝነት፤ እንደ ፖለቲከኛ የበሰለ ፖለተካ ስልት ተጠቅመሽ ክፍፍሉ ለሀገር የማይጠቅም ትግሉንም የሚጎዳ በመሆኑ ሁሉንም
ሊያግባባና የአንድነት ፓርቲውን ሊያጠናክር የሚችል መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ አለን። ከሁሉ በላይ ግን በጠመንጃ
አፈሙዝ ሲቀማማ የኖረን የስልጣን ውርርስ በሰላማዊ መንገድ የማሸጋገር ፖለቲካ ምን ያህል ጉንጭ አልፋና አድካሚ
እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይህንን ውጣ ውረድና መራራ ትግል ከትግል አጋሮችሽ ጋር አመራር በመስጠት ለግብ ታደርሳላችሁ
የሚል እምነትና ከፍተኛ ተስፋ ሰንቀናል።
በመጨረሻም አንቺ እንድትፈቺ ሌሎችም ለመፈታት እንዲችሉ በምናደርገው ትግል በካናዳ የሚገኙ የሀገሪቱ
የሕዝብ ተመራጮች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ ላደረጉልን ግፊት ከልብ እያመሰገን አሁንም
ቀሪዎቹ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በሚደረገው ሕዝባዊ ትግል ድጋፋቸው እንዳይለዬን በድጋሚ ጥሪ እያቀረብን
በሀገራችን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እስኪፈቱ ትግላችን ከናንተጋር አብረን እንቀጥላለን።
ከሰላምታ ጋር!
በቫንኮቨር ካናዳ የአንድነት የድጋፍ ኮሚቴ