አቡጊዳ – መድረኩ በአዲስ አበባ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ
መስክረም 5 ቀን 2003
በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ጨምሮ የበርካታ ድርጅቶች ጥምረት የሆነዉ መድረክ፣ መስክረም 8 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያመልከታል። መድረኩ ከአዲስ አበባ ባለሥልጣናት የሚያስፈልገዉን ፍቃድ ያገኝ ሲሆን በስብሰባዉ ከፍተኛ ሕዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
መድረኩ ስብሰባዉን የጠራዉ በመክሲኮ አደባባይ በሚገኘዉ የመብራት ኃይል አዳራሽ ሲሆን፣ አርብ መስከረም 7 ቀን፣ የመድረክ አባል ድርጅቶች አባላትና ደጋፊዎች በአዲስ አበባ በአራቱም ማእዘናት ህዝባዊ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉም የደረሰን ዜና አክሎ ይገልጻል።
የ2002ትን ምርጫ እንደ አጋጣሚ በመቆጠር፣ ገዢዉ ፓርቲ ከፍተኛ እንግልትና ወከባ እያደረሰም ቢሆን ሕዝቡን የማደራጀትና የመቀስቀስ ትልቅ ሥራ ሲያደርግ የነበረዉ መድረክ፣ አሁንም የምርጫዉ ሂደት በተጠናቀቀበት ሁኔታም፣ ህዝብን የማስተማርና የማደራጀት ሥራዉን ከመቀጠል ዉጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለም የአመራር አባላቱ ይናገራሉ። \ለዉጥ የሚያመጣዉ ህዝብ እንደሆነና፣ በምርጫ ሰበብም ሆነ በማናቸዉም መንገድ ከሕዝብ ጋር መነጋገር፣ በአገሪቷ የሚሰራዉን ግፍ ለሕዝብ ማስረዳት፣ ህዝብ በራሱን እንዲተማመን ማድረግ፣ ህዝብን ማደራጀት፣ ሰላም የሚታገሉ ፓርቲዎች ብቸኛ ተግባር እንደሆነ የሚገልጹት የመድረክ አመራር አባላት በኢትዮጵያ ለዉጥ እንዲመጣ ከተፈለገ በድርጅቶች ዉስጥ ያሉ ጥቂት አባላትን ብቻ ሳይሆን መላዉ ህዝብ መነሳት እንዳለበት፣ ለዚህም በመብራት ኃይል የሚደረገዉ አይነት ስብሰባ በሰፊዉና በተጠናከረ መንገድ መደረግ እንዳለበት ያስራድሉ።
መድረኩ የአዲስ አመት እንኳን አደረሳችሁ መልእክት ባስተላለፈበት ወቅት ገዢዉ ፓርቲ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በአስቸኳይ እንዲፈታ በመጠየቅ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ በሆነ መንገድ የሚዋቀሩበትን መንገድ ለማመቻት ይቻል ዘንድ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር ለመናጋገር ፍቃደኛነቱን መግለጹ ይታወቃል። ነገር ግን ገዢዉ ፓርቲ እስከአሁን ለመድረኩ የእርቅና የእንነጋገር ጥሩ ምላሽ አልሰጠም።