የብርቱካን መታሰር የኛንም መታሰር ነዉ የሚያመለክተዉ
ግርማ ካሳ
አቶ መለስ ዜናዊ ለጋዜጠኞች በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ የሕግ ጉዳይ እንደሆነ ነዉ የገለጹት። ከተለያዩ ማእዘናት ይችን ሴት እንዲፈቱ ጥሪ ቢቀርብላቸዉም «እምቢ አሻፈረኝ » በማለት የማንንም ነፍስ ያላጠፋችን፣ ገንዘብ ያልሰረቀችን፣ ጉቦ ያልበላችን፣ አመጽን ያልሰበከችን ወጣት ብርቱካን ሚደቅሳን ከቱሃንና ከአይጥ ጋር በቃሊቲ እንድትማቅቅ ወስነዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ይሄን ያህል በዚህ ሴት ላይ መጨከናቸዉ ለምን እንደሆነ በርግጥ ሊገባኝ አልቻለም። እርሳቸዉ እንደሚሉት የሕግ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሕጉ ስለማይፈቅድላቸዉ ነዉን ? እስቲ ወረድ እንበልና ሕጉን እንመልከት።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሌሎች የቅንጅት መሪዎች ጋር ስትፈታ፣ በአገር ሽምግልና ወግ መሰረት ይቅርታ ጠይቃ ነዉ የተፈታችዉ። ይህንንም ቃሌ በተሰኘዉ አዲስ አድማስ ላይ በወጣዉ ጽሁፏ በግልጽ አስቀምጣዋለች። ስለዚህ ክርክሩ «ይቅርታ ጠየቀች፣ አልጠየቀችም» በሚለዉ ላይ ሊሆን አይችልም።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ «ይቅርታ የጠየኩት የአገሪቷ የይቅርታ አሰጣጥ ሕግ መሰረት ሳይሆን በአገር ሽምግልና ወግ መሰረት ነዉ። ስለዚህም የጠየቁት ይቅርታ ሕጋዊ( legally binding) ይቅርታ አይደለም» ስትል ይቅርታ የጠየቀችበት መንገድ ከሕጉ መንገድ የተለየ እንደሆነ ትናገራለች።
አቶ መለስ ዜናዊ በበኩላቸዉ «የተሰጠዉ ይቅርታ ሕጋዊ ይቅርታ ነዉ» ሲሉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሕጋዊ አይደለም ማለቷን ማጭበርበር አድርገዉ ይወስዱታል።
«የይቅርታ ዉሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ዉሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ዉሳኔዉ ዋጋ አይኖረዉም”» የሚለዉን የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16 ፣ ንኡስ አንቀጽ 2 በማሰብ፣ አቶ መለስ «ይቅርታ አልጠየኩም ብላላች፤ በመሆኑም የተፈታችሁ አጭበርብራ ነዉ» በሚል የተጣመመ ሕግ አተረጓገም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የተሰጣት ይቅርታ ተሰርዞ ወደ ወህኒ እንድትወርድ አድርገዋል።
«በሽማግሌዎች የእርቅ ማግባቢያ መንፈስ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰዉን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲዉ (ቅንጅት) መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈዉ ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለዉጠዉ የማልችለዉ ሐቅ ነዉ» ስትል ወ/ት ብርቱካን ፣ ይቅርታ የጠየቀችበትን ፊርማ ሰኔ 11 ቀን 1999 እንዳሰፈረች ገልጻለች።
ይህ ወ/ት ብርቱካን የፈረመችበት ሰነድ በአዋጅ ቁጥር 395 አንቀጽ 13 በተደነገገዉ መሰረት የይቅርታ ማመልከቻ ፎርም ሳይሆን በአገር ሽማግሌዎች የተዘጋጀ ደብዳቤ ነዉ።
እንደዉ ለዉይይት ያህል ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የፈረመችበት ወረቀት በአዋጁ መሰረት፣ የይቅርታ መጠየቂያ ፎርም ነዉ ብለን ብንወስድም እንኳን፣ አሁንም በአዋጁ መሰረት፣ የይቅርታ መጠየቂያ ፎርም ከመሙላት በፊት በሕግ መሟላት የነበረባቸዉ ነጥቦች አልተሟሉም።
በአንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ 4፣ በይቅርታ ማመልከቻዉ ላይ ይቅርታ ጠያቂዉ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት፣ ተጠያቂ የሆነበት ወንጀልና የተፈረደበት ፍርድ፣ የፈረደዉን ፍርድ ቤት፣ የፍርዱ አፈጻጸም የሚገኝበት ደረጃ እና የክሱ መዝገብ ቁጥር መሙላት እንዳለበት ይደነግጋል። አንድ ተከሳሽ የይቅርታዉን ፎርም ከመሙላቱ በፊት ወንጀለኛ ተብሎ ሳይፈረድበት የይቅርታ መጠየቂያ ቅጹን ሊሞላ አይችልም። አንቀጽ 14 የበለጠ ጉዳዩን ሲተነትን «በዚህ አዋጅ አንቀጽ 12 መሰረት የይቅርታ ጥያቄ የሚያቀርብ ሰዉ የይቅርታ ጥያቄዉን ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በማናቸዉም ጊዜ ማቅረብ ይችላል» ይላል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ፊርማዋን ያሰፈረችዉ ሰኔ 11 ቀን ነዉ። ከሌሎች የቅንጅት አመራር አባላት ጋር ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ብሎ የወሰነባት ከወራት ወይንም ሳምንታት በኋላ ነዉ። ስለዚህም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰኔ 11 የፈረመችዉ ወረቀት በሕግ የተደነገገዉ የይቅርታ መጠየቂያ ፎርም ሊሆን አይችልም።
ስለዚህም ሕጉ በሚዘረዝረዉ መሰረት ያልተከናወነ የይቅርታ አሰጣት ሂደት ሕጋዊ ነዉ ሊባል የሚችልበት ሁኔታ የለም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ጠይቂያለሁ፣ ይቅርታ የጠየኩት ግን ሕጉን በተከተለ መንገድ አይደለም ማለቷ ከአዋጅ 495 ጋር አብሮ ሲሄድ እንጂ ሲቃረን አናየዉም። በምንም ሕጋዊ መስፈርትና ሚዛን አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት ያጭበረበረችበት ሁኔታም የለም። ስለዚህ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ የሕግ ጉዳይ ሊሆን አይችልም።
አሁንም ዉይይታችንን ለማስፋት ያህል አቶ መለስ እንዳሉት የወ/ት ብርቱካንን ጉዳይ የሕግ ጉዳይ ነዉ ብለን ብንወስደዉም እንኳን አሁንም ሕግ ላለመፈታቷ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ አይችለም።
እንደሚታወቀዉ ወንጀለኞች የሚታሰሩት ተመልሰዉ ወንጀል እንዳይሰሩና እርማት እንዲወስዱ ለማድረግ ነዉ። ለዚህም ነዉ ወህኒ ቤቶች «ማረሚያ ቤቶች» ተብለዉ የሚጠሩት። በሌላ አባባል የሕግ አላማ ዜጎችን መቅጣት ሳይሆን ዜጎችን ማረም፣ ሕብረተሰቡን መጠበቅና መጥቀም ነዉ።
የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395 አንቀጽ 11 የይቅርታ አሰጣጥ ዓላማ ምን እንደሆነ በማያሻማና በማያከራክር መልኩ «የይቅርታ አላማ የሕዝብን ደህንነትና ጥቅም ማስከበር ነዉ« ሲል አስቀምጦታል። በዚህ አንቀጽ መሰረት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ ቢመዘንና ምን ያህል የሕዝብን ደህንነትና የአገርን ጥቅም ያስከብራል የሚል ጥያቄን ቢነሳ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚከታተል ማንኛዉም ሰዉ በቀላሉ የሚመልሰዉ ነዉ። እራሳቸዉ የኢሕአዴግ አባላት ሳይቀሩ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ስህተትና ኢሕአዴግን እራሱን እየጎዳ እንደሆነ ነዉ የሚያምኑት።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን የአገሪቱን ሕግ በመከተል፣ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያደረገች ሴት ናት። በሕግ የተመዘገበ የአንድ አብይ የፖለቲካ ፓርቲ፣ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ናት። በ1999 ዓ.ም ማለቂያ ወቅት ከቃሊቲ እሥር ቤት ከተፈታች ጊዜ ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ እሥር ቤት እስከገባችበት ጊዜ ድረስ የተከሰሰችበት አንዳች ወንጀል የለም። የርሷ መታሰር በምንም መልኩ የአገርን ደህንነትና ጥቅም ከማስከበር አንጻር ይጎዳል፣ እንጂ የሚያመጣዉ አንዳች አዋንታዊ ጥቅም የለም።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር በአገራችን ያለዉን ፖለቲካ በብዙ መልኩ እያወሳሰበዉ በመምጣት ላይ ይገኛል። በገዢው ፓርቲና በአሥር ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የብርቱካን ሚደቅሳ አፍቃሪዎች ዘንድ ያለዉን ጠብ የበለጠ እያከረረዉ ነዉ። በኢትዮጵያዉያን ዘንድ መከፋፈሉና ጥላቻዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን ድህነትንና እንደ አልሻባብ ያሉ ሽብርተኞችን በጋራ እንዳንመክት መተማመንና አንድነትን ከመካከላችን እንዲጠፋ እያደረገ ነዉ።
ይህም ለአገር ጥቅም የሚበጅ አይደለም። ሕግ፣ አላማዉ አገርን ለመጥቀም እስከሆነ ድረስ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳትፈታ «ሕግ» ምክንያት ሊሆን አይችልም። ሕግ ምህረት፣ ይቅርታን አይቃወምም።
ስለዚህ ሕግን እንደሌጦ መተርጎም ቆሞ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ መፈታት ይኖርባታል ብዬ አምናለሁ። የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ እልባት ካላገኘ፣ ጉዳዩ የበለጠ እንደ እሳት እየሆነ ሁላችንንም ወደ ማንፈልገዉ ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል። ኢሕአዴግ ወደ ጎን አድርጎት ፣ አረሳስቶት ሊያዳፍነዉ የሚችለዉ ነገር አይደለም። ፈረንጆች እንደሚሉት የብርቱካን ጉዳይ « Hot Potato » ነዉ።
ከላይ በግልጽ ለማሳየት እንደተሞከረዉም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሕግ እሥረኛ ሳትሆን የፖለቲካ እሥረኛ ናት። ለርሷ መፈታትም የተጠናከረ ፖለቲካ ትግል ያስፈልጋል።
ጉዳዩ የሕግ ጉዳይ ቢሆንማ ኖሮ ወ/ት ብርቱካን አንድ ቀንም በቃሊቲ አታድርም ነበር። ጉዳዩ ግን የፖለቲካ ጉዳይ ነዉ። ይህ የፖለቲካ ጉዳይ ደግሞ የብርቱካን ሚደቅሳ ፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ነጻነትና የሕግ የበላይነት እንዲመጣ የምንፈልግ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጉዳይ ነዉ። የብርቱካን መታሰር የኛንም መታሰር ነዉ የሚያመለክተዉ። ስለዚህ ብርቱካን ሚደቅሳን ለማስፈታት እያንዳንዳችን ከታሰርንበት መፈታት አለብን ፤ ከፍርሃት እሥር ቤት ! ከተስፋ መቁረጥ እሥር ቤት! የራስን ጥቅም ብቻ ከማሳደድ እሥር ቤት ! ከጨለምተኛ አስተሳሰብ እሥር ቤት ! በራስ ካለመተማመን እሥር ቤት !