“ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች” – የትናየት ዓለሙ
ማንም ሰው ቤተሰቡን ወይም ጎሳውን ፣ እንዲሁም ሊኖረው የሚሻውን የቆዳ ቀለምና የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ተጠይቆና መርጦ እንዳልተወለደ(ወደዚህ ዓለም እንዳልመጣ) ሁላችንም የምንጋራው እውነት ነው። በዚህ መሠረተ ሀሳብ ከተስማማን፣ ሰዎች በተወለዱበት አካባቢና ጎሳ፣ ቋንቋና የቆዳ ቀለም ለጥፋትም ሆነ ለልማት በጅምላ መፈጅ አግባብ ካለመሆኑም ባሻገር‹፣ ለአንድ አገር ዕድገት እንቅፋትና ኋላቀር አስተሳሰብም ነው። ዛሬ በአገራችን ኢትዮጵያ “የትግራይ ነፃ አውጪ ነኝ” ይል የነበረው የጥቂት የትግራይ ተወላጆች ስብስብ “ወያኔ” እያራመደ ያለው ይህንኑ የአገር ዕድገት የሚገታና የዜጎችን ተፈጥሮአዊ መብት የሚረግጥና የአብሮነት የትሰስ ገመዳችንን በእጅጉ የሚፈታተን የጥፋት ተለዕኮ ነው።
ተወደደም ተጥላ የሰው ልጅ ከአንድ አገር በላይ ተፈጥሮአዊ አገር ሊኖረው አይችልም። በሥራ ወይም በሌላ ምክንያት ዜግነቱን ሊቀይርና በአልተወለደበት አገር እንደተወላጁ ዜጋ እኩል የምሥራትና የመኖር መብት ሊያገኝ ይችላል። ይህም ሆኖ ግን እንደ ተፈጥሮአዊ አገሩ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ቋንቋው፣ ባሕሉ፣ የቆዳ ቀለሙና ዓይነ ውኃው ከዚያ ሕብረተሰብ ጋር ከቶ አንድ አያደርገውምና። ተፈጥሮአዊ ዜጋ የሚያደርገው ግለሰቡ በዚያ አገር መወለዱ ብቻ ሳይሆን፣ከሥር ከመሠረቱ ጀምሮ የነበረውንና ያለውን ባሕልና የአኗኗር ዘይቤ ከሚጋሩ ዜጎች አብራክ መወለድ ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ በጠመንጃ አፈሙዝ አገዛዙን እያራመደ ያለው ወያኔ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት በመርገጥ አየርም ቢሆን መሳብና መተንፈስ የምትችሉት እኔ ስፈቅድላችሁ ብቻ ነው እስከማለት ደርሷል። ዛሬ በኢትዮጵያችን ወያኔ አውቆም ሆነ በስህተት የሚሠራውን ጥፋት መቃወም ወይም መተቸት አይቻልም። የሚፈቀድ ነገር ቢኖር በጅምላ (ብጭፍን) መደገፍና ማጨብቸብ ብቻ ነው። ከዚህ ያለፈ ነፃና ገንቢ አስተያየት ስለአገር ዕድገትም ሆነ ሉዓላዊነት ወይም ስለሰብዓዊ መብት መከበርና ስለሕግ የብላይነት መናገርም ሆነ መጻፍ በወያኔ በኩል የሚሰጠው አተፌታ በጣም ዝቅ ካለ ላልተወሰነ ጊዜ እስርና እንረግልት፤ ለሌሎች መቀጣጫ ለማድረግ ከተፈለገ ደግሞ እንደ አውሬ አሳድዶ እስከ መግድል ይደርሳል።
“ለእስሟ መጥሪያ ቁና ሰፋች” እንደሚባለው ወያኔ የዓለም ሕብተሰብንና መንግሥታትን አመለካከት ለማሳሳት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችንና ሕጎችን በሕገ መንሥቱ ውስጥ በከፊል እንዲካተቱ አድርጓል። አቶ መለስና ቱባ ካድሬቹ እንደ እንዝርት የሚያሽከረክሩዋቸው “ዳኞችም” ተሹመዋል። ሕገመንግሥቱ ለታይታ ጸድቆ እንዲወጣ ይደረግ እንጂ ሲተገበር አይታይም።ዳኞችም ቢሆኑ ነፃ ሆነው የመወሰን መብት የላቸውም። የዳኞች ዋና ተግባር በነአቶ መለስ ተዘጋጅቶ የተላከላቸውን ውሳኔ በንባብ ከማሰማት ያለፍፈ አይደለም። እናም ሕገ መንግሥቱም ሆነ የዳኞች መኖር ወያኔ በአገርና በሕዝብ ላይ በሕግና በፍትሕ ስም እያደረሰ ላለው ከልክ ያለፈ ጥፋትና ወንጀል ሽፋን ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የላቸውም።
ወያኔ ራሱ ያወጣው ሕገመግሥት ዜጎች በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ተደራጅተው መታገል እንድሚችሉ ይደነግጋል። እውነታው ግን ከዚህ ፍጹም የተለየና የሀገርና የወገን እውነትኛ ተቆርቋሪ የሆኑ ዜጎችን ነጥሎ ለመምታት የተዘጋጀ ነው። ከወጣት እስከ ሽማግሌ የወያኔ ድጋፊና አባል እንዲሆኑ ጫና ይደረጋል። እንቢ ከተባለ ገበሬው ማዳበሪያ ይከለከላል፣ወጣቱ በሚፈልገው ሙያ የመሰልጠንና ኮሌጅ ገብቶ የመማር ዕድሉ ይገደባል። ቢማርም እንኳ የወያኔ ኮር አባል እስካልሆነ ድረስ በተመረቀበት ሙያ ሥራ አያገኝም። ነጋዴም ከሆነ የንግድ ፍቃዱን ይነጠቃል። የመንግሥት ሠራተኛም ከሥራ የመባረር ሳንካ ይገጥመዋል። የወያኔ አገዛዝ ሕብረተሰቡን ምን ያህል ቀፍድዶ እንዳሰረውና መንቀሳቀሻ እንድሳጣው እንዲህ በአጭሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
የግንቦት 2002 ዓ.ም ምርጫን በተመለከተ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች በተወዳዳሪነት እንዲሳተፉ ተደረገ እንጂ ከመጋረጃው በስተጀርባ እረጅም ጊዜ የፈጀ ድራማ በወያኔ ካድሬዎች አማካኝነት ሲተወን ባጅቷል። በይፋ የድምጽ አሰጥት ሥነ ሥርዓቱ ከመካሄዱ በፊት ለሕዝብ የተሰጠው ዛቻና ማስጠንቀቂያ ወያኔን ብቻ መምረጥ እንዳለበት ነበር። ይህንን አስገዳጅ ሁኔታ አንቀበልም በሚሉ ዜጎች ላይም የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ከመከልከል ጀምሮ የእስራትና የግድያ አርምጃ ተወስዷል። የምርጫ ውጤትን በተመለከተ ተወዳዳሪዎች ያገኙዋቸውን የሕዝብ ድምጾች ከኮሮጆ አራግፎ እስከመዝረፍ ተራ ውንብድና ተካሂዷል። ይህንንም ምርጫ ተብዬው ድራማ በተጠናቀቀ ማግስት የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢዎች ቡድን መሪ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቀርበው ያረጋገጡት እውነታ ነው።
እዚህ ላይ ምንም እንኳን ወያኔ ተቃዋሚዎችን በዝረራ አሽንፍኩ እያለ እራሱን ቢያታልልም፣የተዘረረውና በስርቆቱ የተዋርደው እራሱ ወያኔና ነው። ምክንያቱ በየትኛውም አገር የምርጫ ሂደት ተመክሮ እንደሚታቀው እንኳንስ እንደ ወያኔ ያለ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-አንድነት አገር አፍራሽ ቡድን ቀርቶ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅር ያገኘና በእዲሞክራትነቱ በተግባር የተሠከረለት ፓርቲም ወያኔ አገኘሁ የሚለውን ውጤ ሦስት አራተኛ ያህል እንኳ ያገኘ በታሪክ አልታየም።
ስለወያኔ አስከፊ አገዛዝ፣ ትናንት ተራማጅና ዲሞክራት እያሉ ሲያቆላብሱት የነበሩት የምዕራባዊያን መንግሥታትና ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ድርጊቱን ካወገዙትና ከመሰከሩበት ውሎ አድሯል። የወያኔ አባሎችና ደጋፊዎቹም ቢሆኑ በፍርሃት ቆፈን ተቀፍድደው ነው እንጂ ገሐዱን እውነታ አይስቱትም።
ታዲያ እስከመቼ ነው አገር እንደ ዳቦ እየተቆረሰ ሲፈተትና ስብዕና ሲናቅ፣ሲረገጥ፣ በመፈራራትና በጥርጣሬ እየተያየን የሰቆቃ ኑሮአችንን የምንገፋው? መፍትሄውስ ምንድን ነው? እንደ እኔ እንደ እኔ መፍትሄው አንድና አንድ ብቻ ነው። ለአገራችን ለኢትዮጲያ ችግር መወገድ ከዜጋዋ የቀረበ ማንም እንደሌለ ሁሉ፤የችግሩም መፍትሄ ያለው በልጆቿ መዳፍ ውስጥ ነው። በተለይም በወጣቱ ትውልድ ትከሻ ላይ እንዲያርፍ ግድ ይላል። ምክንያቱም የነገዋ ኢትዮጲያ ተረካቢና መሪ እሱ ነውና።እናም ወጣት፣ጎልማሳና ሽማግሌ ሳንል፣ ያለምንም የጾታና የእምነት ልዩነት ሁሉም በአገሩ ጉዳይ መነጋገር ይኖርበታል።ያለፈው ታሪክ ብዙ በጎ ጎኖች እንዳለው ሁሉ ስህተቶችም ይኖሩታል። በዛሬ ላይ ሆነን የትላንቱ ትውልድ ያለፈበትን የታሪክ ሂድት ማየት ያለብን በትላንቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመሥርተን መሆን ይኖርበታል። ያለዚያ ወደተሳሳተና ለመግባባት ወደሚያስቸግር አቅጣጫ ይመራናል እንጂ ወደ መፍትሄ አያደርሰንም።ያለፈ ታሪክን በታሪክነቱ ወደ ቤተመዘክር አስገብተን ለዛሬዋና ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚበጀውን በገጽ ተቀራርበን መነጋገርና ብሎም ስምምነት ላይየሚያደርሰንን ጎዳና መከተል ይኖርብናል። ለዚህ ብሄራዊ ጥሪ አፋጣኝ መልስ መገኘት ሁላችንም ተግተን መሥራት ይኖርበታል። የቤት ስራው ከራስ ይጀምር። ከራሳችን ጋር ተኮራርፈናል፤ ከእህቶቻችን ከወንድሞቻችን ተራርቀናል። በጥቅሉ እርስ በራሳችን በጥርጣሬ እየተያየ ነው። መቅራረብና መነጋገር ከራቀን ሰነባብቷል።በዳይም ተበዳይም ያልሆንን ሰዎች የጐሪጥ እየተያዩ ነው። ስለዚህ እነዚህ ችግሮች የግድ መቀረፍ አለባቸው። ከራሳችን እንጀምር፤ ከራሳችን ጋር ለመታረቅና ራሳችንን ለመውቀስ ወኔውና የሞራል ብቃቱ ይኑረን።ራሳችንን በግለ ሂስ መግራት እስከቻልን ድረስ ደግሞ ያለምክንያት የሚሸሹንንና የሚያኰርፉንንም ይቅርታ ጠይቆ የማነጋገርና የማቅረብ ብቃቱ ይኖረናል።
በዚህ ሁኔታ ከራስ ተነስቶ ወደ ሌላው ለመድረስ በሚደረግ አገር አድን እንቅስቃሴ ማህበራዊ ግንኙነታችን ከመሰፋቱና ተመልሶም ከመጠናከሩ ባሻገር ለብሔራዊ ችግራችን ማስወገጃ መሰረት ይጥላል። የተጣለውን የግንኙነት መሠረት በመጠቀምም ከጥቃቅን ማኅበርዊ ችግሮች አንስቶ እስከ ብሔራዊ ጉዳዮች መነጋገር መወያየት ይቻላል። ቀስበቀስም በተለያዩ ርዕሶች በሰለጠን መንገድ እየተነጋገሩ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል።በተለይ የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ በዚህ ጉዳይ ላይ መሪ ተዋናይ የመሆን ኃላፊነት ይጠበቅበታል።
ውይይቱም የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ነውና ሁሉንም ያቀፈና ያሳተፈ መሆን ይኖርበታል። አንዱ ተጠያቂ ሌላው ጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠር አይኖርበትም፤ ፈቃደኞች ከሆኑ ወያኔዎችም ቢሆኑ የጋራ በሆነችው አገራችን ጉዳይ ላይ ነውና የምንነጋገረው በቅንነት ከመጡ ግደባ ሊደረግባቸው አይገባም ባይ ነኝ ።አኩራፊና አስኰራፊ ባለበት አገር እድገትና ሰላም አይጠበቅምና። ያለበለዚያ እንዳለፈ የዘመናት ታሪካችን አንዱ ወደ ቤተ መንግሥት ሲያመራ ሌላው ወደ ጫካ ይሆናል ጉዞአችን።
ስለሆነም ወገኖቼ ይህችን ወደ ገደል እየተገፋች ያለች አገር ለማዳን ቆም ብለን እናስብ።በተለይ ወያኔና ደጋፊዎቹ ለሚያልፍ ሥልጣን ስትሉ የማታልፈውን አገራችንንና፤የታሪክ ተረካቢ የሆነውን ወጣት ትውልድ ወደ ጥፋትና ውድቀት ከመግፋት ታቀቡ፤ የሰላም ጀምበር ሳትጠልቅ ለይቅርታና ለውይይት ፈጥነን እንነሳ።ጊዜው አሁን ነው፤ ቀጠሮ አናብዛ! ከደሙ ንጹሕ ንኝ ማለትን ትተን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅር ለማለት ወኔው ይኑረን። ይህ ደግሞ የብልህነት፣ የጀግንነት መገለጫ እንጂ የጂልነት ወይም የፈሪነት ባሕርይ አይደለም። ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ለሕዝቦቿ ተደጋግፎ መኖር በሁሉም ቦታና ጊዜ ይቅር መባባል ትውልድና ታሪክ ሲዘከረው የሚኖረው ቅዱስ ተግባር ነው።
ልዑል እግዚአብሔር ለአገራችንና ለሕዝባችን እድገትና ሰላሙን ያውርድልን!!