ሆስኒ ሙባራክ ከሥልጣን ተሠናበቱ

የግብፅ ፕሬዝደት ሆስኒ ሙባረክ ከ18ቀናት ዉዝግብ በኋላ ስልጣን ለቀቁ። ለቀናት አደባባይ ወጥቶ ስንብታቸዉን ሲጠይቅ የከመዉ ህዝብ ደስታዉን እየገለፀ ነዉ።

ሙባረክ፤ ትናንት ማታ በተስፋ ሲጠብቃቸዉ ለነበረዉ ህዝብ ከፊል ሥልጣናቸውን ለምክትል ፕሪዚዳንትነት  ለመረጧቸው ዖማር  ሱሌይማን ማስተላለፋቸውን ከመጠቆም በስተቀር ከሥልጣን እንደሚወርዱ ሳይገልጹ ነበረ ዲስኩራቸውን የደመደሙ። ይሁንና ዛሬ የካይሮውን ቤተ-መንግሥት ለቀው መውጣታቸው ከተገለጠ በኋላ ፤ በአገሪቱ ሰዓት አመሻሽ ላይ ከሥልጣን መውረዳቸው ይፋ ሆኗል። እንደምክትላቸዉ አገላለፅም ለጊዜው ሥልጣኑን ይዞ የሚመራው የጦር ኃይሎች ምክር ቤት ይሆናል።

« የፕሬዚደንቱን ውክልና ህገ መንግስቱ እንደሚያመለክተው ወደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያሸጋግራል። ግብፅ ይህንን ችግር እንደምትወጣው ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ። እስከ ህይወቴ ፍፃሜ ድረስ ከግብፅ አልለይም።»

በካይሮ ጣህሪር(የነፃነት)አደባባይ ብቻ ሳይሆን በአሌክሳንድሪያ፣ ስዌዝና ሌሎችም ከተሞች፤ 17 ቀናት ሙሉ አደባባይ እየወጡ ለለውጥ ሲጮሁ፤ ሲታገሉ የሰነበቱት ግብፃዊያን፤ ትናንት ሌሊት ይህ ግልፅ ያልሆነ የሙባረክ ንግግር ሲሰሙ ይበልጥ አስቆጥቷቸዋል። ሁኔታውን ሲከታተል የነበረው የአለም ማህበረሰብም ግብፅ ወዴት እንደምታመራ ለማወቅ በጉጉት ላይ ይገኛል። በዛሬውም ቀን የግብፅ ቤተ መንግስት ከወትሮው በበለጠ በደንብ እየተጠበቀ ይገኛል።

የግብፅ አጋሮች መሆናቸውን የሚነገርላቸው ምዕራባዊያን መንግስታት ለ 30 አመት ያህል በስልጣን ላይ የቆዩት ወዳጃቸው ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፤ እስከመጪው መስከረም ወር መጠበቅ ሳይሆን ካሁኑ ለለውጥ ሂደት መንገድ ይከፍቱ ዘንድ መክፈቱ መምከራቸውንም ሆነ ማሳሰባቸውን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሰምተናል። የአለም ኃያል መንግስት መሪ ፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ « በግብፅ ታሪክ ይሰራል ሲሉ» ትናንት ሙባረክ ስልጣናቸውን አስረክበው እንዲወርዱ ለማግባባትም ይሆን እንጃ፤ በጉጉት ይጠበቅ ከነበረው የሙባረክ ንግግር በፊት ይህንን ብለው ነበር። « የዛሬዋን የግብፅ ምሽት በጥሞና ነው የምንከታተለው። ከዛም የምንለው ብዙ ይኖረናል። ግን ግልፅ የሆነው ነገር ፤ ጊዜው ፤እየተካሄደ ላለው የሽግግር ሰዓት ነው። ምክንያቱም የግብፅ ህዝብ ለለውጥ እየጮኸ ነው። ወጣቱን ህዝብም ሆነ መላው ግብፃዊያን እንዲያውቁ የምንፈልገው፤ አሜሪካ የተቻላትን ሁሉ ከማድረግ እንደማትቆጠብ ነው፤ የተስተካከለና ትክክለኛ የዲሞክራሲ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ። »

በኃላ ግን ኦባማ የጠበቃቸው ሌላ ነበር። እንዲሁም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተ ቬለ የሙባረክ ንግግር ወደፊት የሚያራምድ እንዳልሆነ ነው፤ በግልፅ ቋንቋ ያላቸውን አመለካከት ያንፀባረቁት

«ይህ የፕሬዚዳንት ሙባረክ ንግግር ፤ አዲስ የወደፊት ተስፋ አያሳይም። ወደፊት ያራምዳል ተብሎ የተጠበቀውም አልነበረም። በግብፅ ያለውን ሁኔታ የሚመጥን አይደለም። የጀርመን መንግስት ከዚህ ንግግር በኋላ ያለው ስጋት ይበልጥ የሚጨምር ነው የሚሆነው።በግብፅ አደባባይ ወቶ በአሁኑ ሰዓት ተቃውሞውን የሚያሰማው ህዝብ ሊደመጥ ይገባል። ለነፃነት፤ ለዲሞክራሲና ለተሻለ የወደፊት ተስፋ ጥሪ፤ እንዲሁም የስልጣን ሽግግሩ በተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል።»

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ምንም እንኳን በፁሁፍ ቢሆንም፤ ከሙባራክ ንግግር በኋላ ያላቸውን አመለካከት ለህዝብ ይፋ አደርገዋል። እሳቸውም፤ «የግብፅ መንግስት የሙባረክን የወደፊት እቅድ በትክክልና በግልፅ ለህዝቡ ማስታወቅ እንዳለበትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ይረዳል ብሎ የሚያስባቸውን መንገዶች እንዲያብራራ አሳስበዋል። ምናልባት የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ አዲስ ለውጥ ያመጣ ይሆናል።

ያዳምጡ [podcast]http://dw-world-od.streamfarm.net/Events/dwelle/dira/mp3/amh/0D0347FF_3.mp3[/podcast]

ልደት አበበ፣ ተክሌ የኋላ፣ እና አርያም ተክሌ