የመለስ አገዛዝ በስጋት ተወጥሯል
(ግንቦት ሰባት) — በሌሎች መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ላይ የሚጨመረው ዋጋ ንረት ከዕለት ወደ ዕለት ህዝባችንን የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲያደርሰው “የኢኮኖሚያችን ማደግን አመልካች ነው” እያለ ሲያላግጥ የኖረው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በቱንዚያ ፈንድቶ አምባገነኖች ያሉበትን አገራት እያዳረሰ ያለውን ህዝባዊ ቁጣ በመፍራት ጊዜያዊ የሽንገላ እርምጃ መውሰዱን እንደቀጠለ መሆኑን የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለግንቦት 7 ዘጋቢ ገለጹ። እንደዘጋቢያችን ምንጮች ቀደም ሲል በአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መለዋወጥ ሽፋን በሰበብ አስባቡ ይጨምር የነበረው የነዳጅ ዋጋ ላለፉት ወራት እንዳይጨምር ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነና በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዕጥረት በአብዛኛው የነዳጅ ማደያዎች በመፈጠሩ ነዳጅ ለመሙላት ታይቶ የማይታወቅ ወረፋ በየቦታው እየታየ መሆኑ ታውቆአል።
ዘጋቢያችን ስለሰሞኑ የነዳጅ ወረፋ መራዘም ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በቱኒዚያ ተቀጣጥሎ እንደሰደድ እሳት በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት እየተዛመተ ያለው የህዝብ አመጽ እንቅልፍ እንደነሳውና ይህም በመሆኑ በቁዋፍ ላይ ባለው ህዝብ ላይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ቢደረግ አመጹ ድንገት ሊፈነዳ ይችላል ከሚል ፍራቻ መሆኑን ገልጸዋል:: ይሁን እንጂ ቀን መቁጠር ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያዊያን ብሶት አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀሬ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ገልጸዋል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ባስተላለፈልን ሪፖርት የአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘረኛው አገዛዝ የማሙአያ ምርጫ አካሂዱ በማለት ጥያቄ ቢያቀርብም ለጥሪው ማንም ጆሮ ሳይሰጠው እንደቀረ ለማወቅ ተችሎአሎ:: በዚህም ምክንያት የአምባገነኑ ወያኔ ካድሬዎች በየቦታው እየተዘዋወሩ ህብረተሰቡን ማስፈራራት መቀጠላቸውንም ዘጋቢያችን ከስፍራው ባስተላለፈልን ሪፖርት ገልጹአል::
በተያያዜ ዜና ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተደጋጋሚ እያደረገ ያለው የብር ምንዛሪን አቅም የማውረድ ርምጃ አሁንም የገበያ ዋጋ ግሽበትን እያባበሰ እንደሆነ ብሉምበርግ የዜና አውታር ባወጣው ዘገባ ላይ አሳይትዋል:: እንደ ብሉምበርግ የዜና አውታር የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በቅርብ ቀን ከደረሰበት የአስራ አራት ነጥብ አምስት በመቶ ወደ አስራ ሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ ማሻቀቡን አስታውቁአል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምግብ ዋጋ ከነበረበት የዋጋ ውድነት ደረጃ አሁንም የአስራ ሶስት ነጥብ ስድስት በመቶ እንዲሁም የምግብ እህል ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ ደግሞ የሃያ ሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጨምሮ አስታውቁአል::
ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት የተጠራቀመ ጥላቻ የተነሳ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳብኝ ይቺላል ብሎ በመስጋት ሸማቹን ህብረተሰብ ለማስደሰት ከአቅርቦት ጋር በፍጹም የማይጣጣም የዋጋ ተመን በቅርቡ እድርጎ እንደነበረ ይህም ዋጋ ማስተካካያ የተደረገባቸውን የፍጆታ ዕቃዎች ከገቢያ ላይ እንዲጠፋ እንዳደረገው ህዝብ በቅሬታ እየተናገረ ነው።