የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ቤታቸው አላግባብ እየፈረሰባቸው መሆኑን አስታወቁ

በታምሩ ጽጌ | ሪፖርተር

በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የጋምቤላ ከተማ አስተዳደርና በቀበሌ 04 እና 05 ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች በከተማው ማስተር ፕላን ምክንያት እየተወዛገቡ ነው፡፡ በአስተዳደሩና በሁለቱ ቀበሌዎች መካከል ውዝግቡ የተፈጠረው፤ የከተማው አስተዳደር በቀበሌ 04 እና 05 ውስጥ ነዋሪዎቹ የሠሩዋቸው ቤቶች የከተማውን ማስተር ፕላን ያልጠበቁና “ሕጋዊነት የሌላቸው ነው” በማለት እንዲፈርስ በማድረጉ ነው፡፡

በጋምቤላ ከተማ ቀበሌዎች ውስጥ የተሠሩ ቤቶች ሕጋዊ ሰነድ ወይም ካርታ የተሰጣቸው ተሠርተው ከተጠናቀቁ በኋላ ለከተማው ማዘጋጃ ቤት በማመልከት መሆኑንና በእነሱ ላይ የተወሰደው ዕርምጃም አግባብነት የሌለው መሆኑን ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ከ138 በላይ አባወራዎች ቤት ሲገነቡ ዝም ብሎ ከመመልከት መከልከል ሲገባው፣ ቤቱ ተጠናቆና እያንዳንዱ ነዋሪዎች እስከ 100 ሺሕ ብር ድረስ ወጭ ካወጡ በኋላ ያለምንም ማስጠንቀቂያ በአፍራሽ ግብረ ኃይል እንዲፈርስ አድርጓል ሲሉ እነዚህ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የጋምቤላ ከተማ ካሉት አምስት ቀበሌዎች ውስጥ በቀበሌ 01፣04 እና 05 የሠሩ ነዋሪዎች ቤታቸውን ከመሥራታቸው በፊት ማዘጋጃ ቤቱን ሲጠይቁ፤መሀንዲሶችን ልኮ እንዲመለከቱት ካደረገ በኋላ “ቤት ሳይሠራበት ሕጋዊ ማድረግ አይቻልም፤” እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡

ነዋሪዎቹ ቤቱን ሠርተው ሲጨርሱ ሕጋዊ ለመሆን ማዘጋጃ ቤቱን በድጋሚ ሲጠይቁት መሀንዲስ ልኮ እንዲያየው ካደረገ በኋላ “ለጊዜው ታግዷል፤ የሕጋዊነት ማረጋገጫ ሰነድ አይሰራም፤” ብሏቸው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ የቀበሌ 01 ነዋሪዎችን ሕጋዊ አድርጐ የቀበሌ 04 እና 05 ግን በመከልከል እንዲፈርስ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ቦታው የኢንዱስትሪ ቦታ በመሆኑ መነሳት እንዳለባቸው አስተዳደሩ ቢነግራቸውም፣ የኢንዱስትሪ ቦታ ከዋና መንገድ 200 ሜትር ፊት ለፊቱን ይዞ እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ መሠራት እንዳለበት በማስተር ፕላኑ ላይ ስለሰፈረ፣ ነዋሪዎቹ ከዚህ ውጭ እንዲሠሩ በማድረግ ቦታው የኢንዱስትሪ ነው መባሉን በመቃወም ይከራከራሉ፡፡

“እንዴት በአንድ ከተማ ውስጥ ላሉ ቀበሌዎች የተለያየ መመሪያ ይወጣል?” በማለት ነዋሪዎቹ ጠይቀው፤ ሕገወጥ ያደረጋቸው የክልሉ የልምድ አሠራር መሆኑንና በማኅበር ተደራጅተው የተወሰኑ ቤቶች በቅድመ ሕጋዊነት ከሠሩት ውጭ ሁሉም በሕገወጥ መንገድ የተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በደንብ ስለሚያውቀውና ያወጡትን ወጪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕጋዊ እንዲያደርጋቸው ወይም ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ያነሱትን ቅሬታ በቅርብ ያውቁታል የተባሉትን የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ቦል ኬትን በስልክ አግኝተናቸው ለማነጋገር ብንሞክርም፣ “ለግል ጋዜጣ ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጥም” በማለት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኡመድ ኡቦንግን አነጋግረናቸው፤ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ገልጸው፣ ቅሬታ እያሰሙ የሚገኙት በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት ቤት ያልሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ቀበሌ 05 “ቀበሌ” እየተባለ ይጠራ እንጂ ገና በወረዳ ሥር መሆኑን፣ “ቤት ፈረሰብን፣ ተበደልን” የሚሉት ነዋሪዎችም፣ ከሕግ ውጭ የሠሩ መሆናቸውን፣ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ጥያቄ አለማቅረባቸውንና እሳቸው የሊዝ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆናቸው ሁሉንም ነገር እንደሚያውቁ አረጋግጠዋል፡፡

በሕገወጥ ተሠርቶ ለፈረሰ ቤት ምንም ዓይነት ካሳ እንማይከፈል፣ በአሁኑ ጊዜ የከተማው ማስተር ፕላን እየተሠራ በመሆኑ ሁሉም ነገር ሲጠናቀቅ ዜጐችን በአግባቡ እንደሚያስተናግዱ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ቀበሌ 05 ከፊሉ በቀበሌ 02 ሥር ከፊሉ ደግሞ በቀበሌ 04 ሥር በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ቀበሌ 05 ማለት ስለማይቻል የማስተካከል ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን አቶ ኡመድ ተናግረዋል፡፡