ህንድ ከኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ለም መሬት መውሰዱአ ታወቀ

ኢትዮጵያ ለህንድ በሊዝ ኪራይ የሰጠቺው ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ለም መሬት ህንድ የዜጎቹዋን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያከናወነች ላለው ተግባር ትልቅ አስተዋጾ ይኖረዋል በማለት ኢኮኖሚክ ታይምስ በመባል የሚታወቅ ጋዜጣ ዘገበ::

ኢኮኖሚክ ታይምስ በመባል የሚታወቀው ጋዜጣ ባወጣው ጽሁፉ ኢትዮጵያ ለህንድ እስካሁን 1.8 ሚሊዮን ሄክታር ለም መሬት በሰባ ዓመታት የሊዝ ኪራይ ማስረከቡዋንና ይህም ለህንዳዊያን የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጹአል:: ዘገባው ይህ ከኢትዮጵያ የተገኘ ድንግል የእርሻ መሬት ከፍተኛ የግብርና ሰብል አምራች የሆነቺውን የፑንጃብ ክፍለግዛት 50 በመቶ የሚሆነውን የቆዳ ሽፋን የሚሸፍን እንደሆነና ይህም ህንድ 25 ከመቶ የሆነውን የሩዝ ፍጆታዋን የምታገኝበት እንደሆነ ከዚህም የተነሳ የህንድ ባለስልጣናት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ዘግቡአል::

የመረጃ ድረገጹ በህንድ አገር ጉብኝት እያደረገ ያለውን የኢትዮጵያ ግብርና ሚንስትር ተፈራ ደርበውን በመግለጽ እንደዘገበው የወያኔ አገዛዝ እስካሁን ድረስ ለህንድ ሃገር ቃል ከገባውና ካስረከበው የለም መሬት ሽያጭ በተጨማሪ ለውጭ ሃገራት ኢንቨስተሮች ለመሸጥ ካዘጋጀው ተጨማሪ 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ የህንድ ኢንቨስተሮች የፈለጉትንን ያህል ቢወስዱት ወይንም ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው ቢይዙት ደሳታቸው እንደሆነ መግለጹን አያይዞ ዘግቦአል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የተሻሉና ለም በሆኑ ክልሎች የሚገኘውን ሰፋፊ የርሻ ቦታ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል የመሬት ሽያጩን የጥድፊያ ዘመቻ በስፋት እንደቀጠለበት ስንዘግብ መቆየታችን አይዘነጋም:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በግዳጅ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ የሚገኙት አርሶ አደሮች ጥያቄ ሲያነሱ እስከ ሞት ድረስ የሚደርስ እንግልት እንደሚጠብቃቸው መግለጻችን ይታወሳል::