ኃይሌ ምን አገባው ! ( ሄኖክ የሺጥላ )

ኃይሌ ምን አገባው ! ( ሄኖክ የሺጥላ )

ኃይሌ ወንድማችን ፣ ቆጣቢው ኃይሌ ፣አባ ሃናው ኃይሌ ፣ ባለፎቁ ኃይሌ ፣ ባለ ሲኒማ ቤቱ ኃይሌ ፣ የኦሎምፒክን ሜዳይ ደግሞ ደጋግሞ ያጠለቀው ትልቁ ሰው ኃይሌ ተሳሳተ ይላሉ ። አሁን ኃይሌ ምኑ ጋ ነው የተሳሳተው ? እኔ እስከሚገባኝ ኃይሌ የሚያውቀውን ነው ያወራው ፣ የገባውን ነው የተናገረው ! እኛ እኮ ኃይሌን ያወቅነው ኢትዮጵያውን ወክሎ ስለ ዲሞክራሲ ሲያወራ አይደለም ። እኛ ኃይልዬን የምናውቀው ሲሮጥ ነው ። አዎ ተዘጋጅ -ቷ ! ከዛ በቃ ሀይልዬ ፍልቅልቅ እያለ ሲሮጥ !

ኃይሌ ለኢትጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲ እንደ ቅንጦት ነው ፣ መልካም አስተዳደር እንጂ ዲሞክራሲ አያስፈልጋትም ሲል ስህተቱ ምኑ ላይ ነው ? ተሳሳተ እንዴ ?እንደውም ኃይሌ ከተሳሳተ የተሳሳተው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም አስተዳደር ችግር ሊኖርበት ስለሚችል ፣ የመልካም አስተዳደር ያስፈልገዋል ማለቱ ነው ። እኔን እስከሚገባኝ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም አያስፈልገውም ! ምንም !

ቆይ መልካም አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይሰራለታል ? ምን ሊያደርገው ? የት ሊያስቀምጠው ? አሁን ማን ይሙት ለአንድ ገበሬ ዲሞክራሲ ብትሰጠው ምን ያደርግበታል ? አያርስበት !? አይጎለጉልበት !? አይዘራበት !? ምን በወጣው ። እዛው ዲሞክራሲውንም እንደ መሬቱ እርስ በእርሳቸው ይከፋፈሉት ! ኃይሌ ልክ ነው ባካችሁ !

አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ጥያቄ መጠየቁ አግባብ ነው ነው የምትሉት ? ነጻነት ምን ይሰራለታል ? ግዛ ብትሉት ዋጋውንስ ይችለዋል ወይ ? ነጻነት እኮ ብዙ ያስከፍላል ? ዲሞክራሲ እኮ ” እንደ ሾላ ፍሬ በድንጋይ ተመቶ የሚለቀም ነገር አይደለም !” ። እንደውም ሳስበው የኛ ሕዝብ ችግር ስለማያውቀው ነጻነት ማውራቱ ላይ ይመስለኛል ። ይሄ ሕዝብ ነጻ ሆኖ ያውቃል እንዴ ? ታዲያ ያለመደበትን ነጻነት ማንን ለመመስል ነው ” ነጻነት -ናጽነት – ፕሊሱማ –” እና ወዘተ እያልን የምንደሰኩረው ። «ከየት አባቱ ያመጣውን ነጻነት !» እንደውም የዚህ ሕዝብ ችግር ቂጥኝ ነው ! የዚህ ሕዝብ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ሳይሆን ፣ ያልተመጣጠነ «ወሲብ» ችግር ነው !

ይሄ ሕዝብ እኮ ዓመት ሙሉ እህል ሳይበላ ፣ ለአምት-በዓል በግ የሚያርድ ሕዝብ ነው ። ታዲያ የዚህ ሕዝብ ችግር ከዲሞክራሲ እጦት ጋ ምን አገናኘው ? የዚህ ህዝብ ችግር የመስ’እዋት ችግር ነው። ለምሳሌ የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት በያ ሰሞን ሲሰረዝ ፣ የአስቴርን የሙዚቃ ኮንሰርት ተቀላቅሎ ይህ ብርቅ ሕዝብ ሲጨፍር እንዳደረ ሰምቻለሁ። ምን ማለት እንደሆነ ይተርጎም ? እሺ ይህንን ስንተረጉመው ምን ማለት ነው የ- አንድነት ፓርቲ በምንወደው መንግስታችን በጉልበት ሲፈርስ ፣ ሄዶ ሰማያውን መቀላቀል ማለት ነው ። ታዲያ ለዚህ ሕዝብ ዲሞክራሲ ያስፈልገዋል ? በምድር ላይ ከዚህ ሕዝብ በላይ ያለ ዲሞክራሲ– ዲሞክራሲን የተረዳ ይኖራል ?

ሀይሌ እውነቱን ነው ፣ ለዚህ ሕዝብ ዲሞክራሲ ሳይሆን ካልሲ ነው የሚያስፈልገው ! ለዚህ ሕዝብ ነጻነት ሳይሆን ፣ ፓንት ነው የሚያስፈልገው ። የዚህ ሕዝብ ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር ሳይሆን ፣ የመልካም ምድራዊ አቀማመጥን በትክክል ያለመረዳት ችግር ነው ። ምን ማለት ነው ? ይሄ ሕዝብ ሃገሩ ራሷ የቱ ጋ እንዳለች እንኳ በቅጡ አያውቅም! ለዚህም ነው በአራቱም አቅጣጫ ሃገሩን ለመፈለግ ካገሩ የሚወጣው ! የዚህ ሕዝብ ችግር የመንግስት ባለ ስልጣናት የሚያደርሱበት በደል አይደለም ! የዚህ ሕዝብ ችግር ያንን በደል ችሎ ( ዋጥ -ሥልቅት አድርጎ ) መኖር መቻሉ ላይ ነው ። ታዲያ ህዝቡ ረሃቡ ከተመቸው ፣ ድንቁርናው ከደላው ፣ ስደቱ ከከየፈው ፣ ኃይሌ ምን አገባው ! ደሞ ኃይሌን እናውቀዋለን እንጂ እሱ አያውቀንም ! ቢያውቀን ኖሮ እንዲህ አይለንም ! እመኑኝ ኃይሌ አያውቀንም !

Henoke Yeshetlla's photo.