አሳፋሪ ከሆኑት የአሜሪካን አጋሮች መካከል፤ አንዱዋ ኢትዮጵያ መሆንዋ ተገለጸ

ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በአለም ዙሪያ ከምታደርገው ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ8 አገሮች ጋር ያላት ወዳጅነት እጅግ የሚያሳፍር እንደሆነ ፎሪን ፖሊሲ በመባል የሚታወቅ አንድ በአሜሪካን አገር የሚታተም መጽሄት ዘገበ። ከ 3 ቀን በፊት በፈረንጆች አቆጣጠር ጃንዋሪ 31 ለንባብ የበቃውን ይህንን ዘገባ ለህዝብ ይፋ ያደረገው ፎረን ፖሊሲ የሚል ድህረ ገጽ እንደገለጸው በጸረ ሽብርተኝነት ሥም የቡሽ አስተዳደር ከኢትዮጵያው ዘረኛ አገዛዝ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ጋር የመሰረተቺው ወዳጅነት ለአሜሪካ እጅግ አሳፋሪ ከሆኑት አንዱ እንደሆነና ቡሽን የተኩት አዲሱ ፕሬዝደንት ኦባማም ቢሆኑ ግንኙነቱን አለዘቡት እንጂ አልቀየሩትም ሲል ተችቶአል። ፎሪን ፖሊሲ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አሳፋሪ ናቸው ያላቸውን ሌሎች ሃገራትም የዘረዘረ ሲሆን እነዚህ ሃገራትም ሳውዲት አረብ፣ የመን፣ ዮርዳኖስ፣ ዩጋንዳ፣ ኦዝበኪስታን፣ ካዛኪስታንና ቬትናአም መሆናቸውን ገልጹአል::

ፎሪን ፖሊሲ አሳፋሪ ናቸው ያላቸውን አገራት መሪዎች ተግባራት በዝርዝር ያወጣ ሲሆን ሁሉም በየአገራቸው የዜጎቻቸውን ሰብአዊ መብት ከመጣስ ጀምሮ በሙስናና በሥልጣን ብልግና የሚታወቁ ናቸው ብሎአቸዋል። የመለስ ዜናዊን ተግባር በልዩ ሁኔታ የዘረዘረው ፎረን ፖሊሲ ባለፈው ግንቦት ወር 2002 በተካሄደው ምርጫ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ 99.6 በመቶ በሚሆን ውጤት አሸንፊያለሁ በማለት ማሳወቁን፣ ይህንም ተከትሎ በኢትዮጵያ የነበረው እጂግ ዝቅተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጭራሹን መጥፋቱን እንዲሁም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገሪቱ የፖለቲካ ስራን ለመስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ጭራሹን እንደዘጋው ገልጹአል::

ፎሪን ፖሊሲ በኢትዮጵያ እጂግ በርካታ ንጹሃን ዜጎች እንዲሁም በርካታ የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲ አባላት ያለበቂ ምክንያት እየታፈሱ ወደ እስር ቤት እንደሚወሰዱ እንዲሁም በእስረኞች ላይ የወያኔው አገዛዝ እያደረሰ ያለውን እስራትና በደል በዝርዝር አስቀምጡአል፣፣ ከዚህም በተጨማሪ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቁአማት ላይ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ የወሰዳቸውን ተገቢ ያልሆኑ ርምጃዎችን፣ በነጻ ሚዲያ ተቁአማትና ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰዱ ያሉ አፋኝ ርምጃዎችን በሙሉ በዝርዝር አስቀምጡአል:: ፎሪን ፖሊሲ በዚህም ምክንያት በአሜሪካን ሃገር የሚገኘው ፍሪደም ሃውስ ኢትዮጵያን ቀደም ብሎ በከፊል ነጻ የሆነች እያለ ይጠራበት ከነበረው ደረጃ ከአፈና ፍጹም ነጻ ያልሆነች ሃገር ወደሚለው ደረጃ እንድትወርድ ማድረጉን ጠቁሙአል::

በዘገባው አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን አፈና በግልጽ የምታውቅ በመሆንዋ የወያኔው አገዛዝ በሰባዊ መብቶች ላይ የሚያካሂደው አፈና ተገቢ እንዳልሆነ ወቀሳ እየሰነዘረች እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለሰብአዊ ርዳታ በማለት የምትልከው ገንዘብ ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ እንደሆነ መረጃው እንዳላት ቢታወቅም በየዓመቱ ወደ ስድስት መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ኦላር ማለትም ወደ አስር ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ ገንዘብ አሁንም መለገስ መቀጠሉዋ የሚያሳፍር ነው ብሉዋል::