ኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ሕፃናትን በመላክ ከቻይና በመቀጠል ከዓለም ሁለተኛ ሆነች

(ኢትዮ እማማ)
የአሜሪካ መንግስት በያዝነው ሳምንት ባወጣው ይፋዊ መረጃ መሠረት ወደ አሜሪካ ባለፈው አመት 2010ዓ/ም ላይ በጉዲፈቻ መልክ በገቡ የውጪ ሀገር ሕፃናት ቁጥር ቻይና ቀዳሚውን ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ ትከተላለች።

ቻይና ቀዳሚ ለመሆን የቻለችው 3,401 ሕፃናትን በመላክ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ 2,513 ሕፃናትን አሳልፋ በጉዲፈቻ መልክ በመስጠት ከቻይና በመቀጠል የሁለተኛ ስፍራን ለመያዝ ችላለች።ሩሲያ 1,082 ሕፃናት እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ 863 ሕፃናትን በመላክ የሶስተኛና የአራተኛ ስፍራን ለመያዝ ችለዋል።

ሕፃናትን በጉዲፈቻ በመስጠት በ2008 ላይ 4,123 ሕፃናትን ለአሜሪካኖች በመስጠት ቁጥር አንድ የነበረችው ጓቲማላ ከሙስና ጋር በተያያዘ ሁኔታ ከእገዳ አንስቶ ከፍተኛ ቁጥጥር ስለተደረገባት ቁጥሯ ወደ ታች ለማሽቆልቆል ተገዷል እንደ አሶሴትድ ፕሬስ ዘገባ ። ይኽውም በ2009 ላይ 756 ሕፃናትን ብቻ ስትልክ ባለፈው አመት 51 ሕፃናትን ለመላክ ችላለች።

የመካከለኛዋ አሜሪካዋ ሀገር ጓቲማላ የጉዲፈቻ ኢንዱስትሪዋን እንደገና ሕገ ደንቡን እስከምታሻሽለው ድረስ መዝጋቷ ታውቋል። አጠቃላይ ሠንጠረዡ እንደሚያመለክተው በ2010 ላይ 11,059 ጉዲፈቻ ሕፃናት አሜሪካ የገቡ ሲሆን ይህም በ2009 ከነበረው ቁጥር 12,753 የወረደ ሲሆን በ2004 ከነበረው 22,884 ደግሞ 50 በመቶ መቀነሱ ተገልጿል።

ሠንጠረዡ ባለፈው ጥር ወር በሀይቲ በነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ ሀገሪቱን ከለቀቁት ከ1,100 ሕፃናት በላይ አለማካተቷ ታውቋል።የአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንቱ እንዳሳወቀው ኢትዮጵያ በ2009 ላይ ከነበረው በ200 ሕፃናት ጭማሪ ማሳየቷን ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ሌላ ወደ አውሮፓና ወደ ላቲን አሜሪካ (ስፔን) እንዲሁም ወደሌሎች ሀገሮች በመላክም ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘችም መረጃዎች ይጠቁማሉ። አይ !ያልታደለች ሀገር !!

በሌላ በኩል ዲፓርትመንቱ እንደገለፀው ባለፈው አመት 43 የአሜሪካ ሕፃናት በጉዲፈቻ መልክ ለውጪ ሀገር ተወላጆች መሰጠታቸውን ገልጿል። 19ኙ ለካናዳ ሲሆን 18ቱ ደግሞ ለኔዘርላንድ (ሆላንድ)ነው የተሰጡት።