የዚህ ዓመት የዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ውጤት አይታወቅም
ብርቱካን ፈንታ
በ2002 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸው ውጤት ምን ያህል እንደሆነ እንደማይታወቅ ተገለጸ፡፡ የመግቢያ ውጤቱ በዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበል አቅም ይወሰናል፡፡ ተማሪዎቹ የመልቀቂያ ፈተናውን ውጤት ከሐምሌ 23 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ያወቁ ቢሆንም፣ እንደቀደሙት ጊዜያት ዩኒቨርሲቲ መግባትና አለመግባታቸውን ግን አላረጋገጡም፡፡ ከዚህ ቀደም ውጤቱ በሚወሰድበት ጊዜ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባው ነጥብ ይገለጽ የነበረ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ግን በተማሪዎቹ ውጤት ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች አቅም ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ እስካሁን እንዳልታወቀ፣ የትምህርት ሚኒስቴር የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ አባተ በተለይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ከ100,000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ እከሌ አልፏል እከሌ ደግሞ ወድቋል የሚል ውጤት እንደማይገለጽ የሚናገሩት አቶ አበራ፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሏቸውን እያንዳንዳቸውን የትምህርት ክፍሎችና ለሚቀበሏቸው ተማሪዎች ያላቸው አቅም ከተጠናና ከታየ በኋላ ለተማሪዎቹ ይገለጻል፡፡ በአሥር ቀን ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበል አቅማቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ «ያን ጊዜ ማን የት ቦታ እንደተመደበ ይታወቃል፤» ብለዋል፡፡
ለጊዜው ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅማቸውን ያላሳወቁ በመሆኑ፣ ምን ያህል ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገቡ የማይታወቅ ቢሆንም፣ ካለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት ግን ከ70 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲዎቹ ይቀበላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ በየጊዜው ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያወጧቸው መመሪያዎችና ደንቦች ተማሪዎችንና አገሪቱን የሚጠቅም እንጂ የማይጎዳ መሆኑን አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡ በየጊዜው በተቋማቱ የአንድ ትምህርት ክፍልን የማጠናቀቂያ ጊዜ አንዳንድ ጊዜ የማሳጠር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የማራዘም ሁኔታ የሚታይ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት ለውጦች በዩኒቨርሲቲዎቹ ተጠንተው የሚደረጉ በመሆናቸው ችግር እንደሌለባቸው ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ሁለተኛ ዓመት የደረሰን ተማሪ ከአንድ ዓመት በኋላ እመረቃለሁ ብሎ ሲያስብ አራት ዓመት ተደርጓል ብሎ ከመግለጽ፣ ተማሪው መጀመሪያ ሲገባ አራት ዓመት እንደሚማር ለምን አይገለጽለትም? በሚል ለአቶ አበራ ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ለውጦች እየተደረጉ ያሉት በመምህርነት ለሚሠማሩ ተማሪዎች ሲሆን፣ ይህም ከሌሎቹ የትምህርት ክፍሎች አንድ ዓመት በመጨመር ሥልጠና ለመስጠት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌሎቹም የትምህርት ክፍሎች ላይ የተለየ ሁኔታ ሊታይ ይችላል የሚሉት ኃላፊው፤ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲዎቹ አጥንተው ከራሳቸው አካሄድና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመው የሚሄዱበት ስልት በመሆኑ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ አገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ኃይል ከማብቃት አንጻርም መደረግ ያለበት ውሳኔ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡