“የነጻነት ቀን ቀርባለችና ጸንታችሁ ቁሙ! እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ)

“የነጻነት ቀን ቀርባለችና ጸንታችሁ ቁሙ!
እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ)

እነሆ በጨለማ ቤት ውስጥ ከታጎርን 311 ቀናት ሞሉን፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል ባካችሁ? የዛሬ አመት በዚህ ወቅት ከጓደኞቼ ጋር በዝዋይ እስር ቤት የሚገኙትን ጀግኖቻችንን ለመጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ ለማለት የገና ዋዜማን በዝዋይ ወህኒ ቤት ተገኝተን ነበር፡፡ ግን ምኞታችን ቅዠት ሆኖ ያሰብነው ሳይሳካ አንድም የፖለቲካ እስረኛ ማግኘት ሳንችል በሩን ተሳልመን ተመለስን፤ መጠየቅ አትችሉም ተብለን፡፡
የገና ዕለትም እንደለመድነው ከጀግኖቻችን ጋር ለማሳለፍ መጀመሪያ በቂሊንጦ ወህኒ ቤት፣ ቀጥሎ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ናቸውና የቃሊቲ ጀግኖቻችን ከእነሱ ጋር በማሳለፍ ለማስታወሻ ይሆነን ዘንድ እዚሁ ቃሊቲ በር ላይ ተሰባስበን ፎቶ ተነሳን፡፡ ያ በዓል ለእኔ እና ለአባሪዎቼ የመጨረሻ በዓላችን ነበር፡፡ ሆኖም በዓሁኑ ሰዓት በዚያ ፎቶ ላይ ተሰባስበን ከተነሳነው ስንት ሰው እንደሆነ በሰፊው እስር ቤት የቀረው እናንተው ማየት ትችላላችሁ፡፡ (ፎቶ ከተገኘ ማለቴ ነው)


ግማሾቻችን ቃሊቲ፣ ግማሾቹ ቂሊንጦ፣ ግማሾቹ ማዕከላዊ፣ ግማሾቹ ሸዋሮቢት ታጉረዋል፤ የቀሩትም ከሀገር ተሰደዋል፣ አንድ ሁለት ቆራጦች ደግሞ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሀገር ቤት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጨረሻ! መታሰር አልያም ከሀገር መሰደድ! በቅርቡ የማደንቃቸውና የማከብራቸው ጓደኞቼ ወደ ማዕከላዊ መግባታቸውን ስሰማ በጣም አመመኝ፡፡ በእርግጥ ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መታሰር አዲስ አይደለም፡፡ ከመታሰርም በላይ ወንድማችን ሳሙኤል አወቀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል፤ በኦሮሚያ ያለውን ግድያ የምናውቀው ነው፡፡ ግን እስከመቼ ግፉ ይቀጥላል? እስከመቼስ በዚህ ሁኔታ ጀግኖቻችንን እያስበላን እንቀጠላለን? እስከመቼስ መረጃ ምንጮቻችን የሆኑት ሚዲያዎች ሲታገዱ እንታገሳለን? እስከመቼ በፍርሃት ቆፈን ተቀፍድደን እንቀመጣለን? እስከመቼ እስሩና ግድያው የእኛን ቤት እስኪያንኳኳ እንጠብቃለን?
ለመሆኑ ቆርጠን ተነስተን ወያኔን ታግለን እንዳንጥል ያደረገን ምንድነው? ከአፍሪካ የስልጣኔ እና የነጻነት ፈር ቀዳጅ ተምሳሌት እንዳልነበርን ዛሬ ከጎረቤት ኬንያ እንኳን አንሰን ስንገኝ ምን ይባላል? አዎ በረባ ባረባው ለራሳችን የምንሰጠው ምክንያት ወደኋላ እየጎተተን ይገኛል፡፡ ልጄ፣ ሚስቴ፣ ባሌ፣ ልጄ፣ እናቴ፣ አባቴ…ስንል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከካርታ ላይ እንዳትጠፋብን እሰጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጀግንነት ስሜቱ ወዴት ገባ? እድሜ ልክ በፍርሃት ከመኖር አንድ ቀን በጀግንነት መኖር አይሻልምን? ኸረ ንቃ ወገኔ…ተነስ! በቃ እኔ የምልህ ንቃ ነው!


ይህን የምልህ አንዳንድ የአዲስ አበባ ካድሬዎች በወያኔ ቴሌቪዥን እንደሚሉት አውሮፓ ተቀምጬ አይደለም፡፡ እዚሁ በግፍ እስር ላይ ሆኜ እንጂ! ተነስ የምልህ ፈርቼ በማፈግፈግ ሳይሆን ደፍሬ ከፊት በመቆም ነው፡፡ የጀመርኩት የነጻነት ትግል፣ የነጻነት መንገድ አለና ከዳር አድርስልኝ ነው የምልህ! በአንድ ወቅት የዛን ዘመኑ አሸባሪና የአሁን ዘመኑ የሰላም ኖቬል ተሸላሚ ኔልሰን ማንዴላ (ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልንና) እንዲህ ብለው ነበር፤ ‹‹ማንኛውም ህዝብ ሁለት ምርጫ ፊቱ ላይ የሚደቀንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እጅ መስጠት ወይም መሳሪያ ማንሳት? እኛም ሁለተኛውን ምርጫ እንድንመርጥ ተገድደናል›› ብለው ነበር፡፡ እኔም ኢትዮጵያዊነት አልደፈርም፣ አትንኩኝ ባይነት መሆኑን ተረድቼዋለሁና፣ እጅ መስጠት እንኳን ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ገብቶኛል ለምለው ይቅርና ለአንድ ጨቅላ ህጻን ልጅ እጅ መስጠት ማለት ሞት ነውና ልክ እንደ ማንዴላ ሁለተኛውን ምርጫ እንድመርጥ ተገድጃለሁ፣…መሳሪያ ማንሳት!


ምንም እንኳ አሁን ላይ በወያኔ እጅ ወድቄ በዚህ ጨለማ ወህኒ ቤት ብገኝም ራዕዬ ትልቅ ነውና ብዙ በመንገዴ እየሄደበት ይገኛል፡፡ አዎ ዛሬ አካሌ እዚህ ቢገኝም ልቤ ባህርን ተሻግሮ ኤርትራ በርሃ ውስጥ ከጀግኖቹ መንደር ይገኛል፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገሰግሱት ከነዚያ ልበ-ሙሉዎች ጋር የእኔ ልብ!
በመጨረሻም፣ ማንም ሰው ጀግና ነሽ፣ ጎበዝ ነሽ አይበለኝ! እኔ በሴትነቴ የጀመርኩትን እናንተም ተከተሉኝ፡፡ ልብ ከቆረጠ ሊገታው የሚችለው ምንም ኃይል የለምና! በዚያ በስቃይ ቤት ከማንም ሳትገናኙ መምሸቱንም መንጋቱንም ለምርመራ ስትወጡ ብቻ እያያችሁ በዓሉን የምታሳልፉት የምወዳችሁ ጓደኞቼ አይዟችሁ በርቱልኝ እላለሁ! የማያልፍ የለም!! የነጻነት ጊዜ ቀርባለችና ጸንታችሁ በአቋም ቁሙ! የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋራ ይሁን!!”

10 Comments on ““የነጻነት ቀን ቀርባለችና ጸንታችሁ ቁሙ! እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ)”

  1. ወያኔ ወጣቱን በጫትና በአደንዛዥ ዕፅ ገሎታል ብየ ነበር።ኧረ የወንድ ልጅ ያለህ የዝች ልጃችን ጥሪ የጦር ያህል የማይወጋው ማንኛችን እንሆን ? ? ? ጫት፥አደንዛዥ ዕፅ እና ራቁት ዳንስ የተከለከለው እኮ ትግራይ ውስጥ ብቻ ነው።ተቃዋሚ ነን የምትሉ ሁሉ በዚህ የአገራችን የመኖር እና የአለመኖር መስቀልኛ መንገድ ላይ ባለችበት ቅጽበት አሁንም በጸጉር ስንጠቃ ተዘፍቃችሁ ልትመለከቱ ይሆን ? ? ?

    እግዚአብሔር ይቅር ይበለን ! ! !

  2. እነዚህ ብርቅየ ወጣቶች ትኩስ የወጣትነትና የአበባ ጊዜያቸውን በወያኔ ጨለማ ቤት እንዲያሳልፉ የእኛ አባቶች የተከተልነው አሳፋሪ እና ቆሻሻ ፖለቲካ አስተዋፆ ማድረጉንስ እንገነዘባለን ? ? ? አባቶቻችን ስለሰሩት ገድል ማነብነብ አንድ እርምጃ ፈቀቅ አያደርገንም።በመጨረሻም እናንተ የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች እግዚአብሔር ከምድረ ገጽ ያጥፋችሁ።

  3. አድስ አበባ አሉሽ…በዘመኑ ከወያኔ በፊት ትክክል…!አሁን ግን አድስ ቆሻሻ ማፈሪያ ትውልድ…!ፍየል ይመስል ቁርሱ ጫት ምሳው ጫት ራቱ ጫት የሆነ ትውልድ ሆነ…!መብቱ 6ሰአት ላይጫት ቤት መሰለፍ የሚመስለው ትውልድ ሆነ…!ሴቶቹ ሱሪ አጣብቀው በታጠቁበት ሰአት ወንዱ ሲዝረከረክ ማየት ያማል(ያሳፍራል) ::ጎበዝ ንቃ በተለይ የአድስ አበባ ወጣት …ትግራይ…ጫትና ድሽ ክልክል እንደሆ :ሲጋራ ከተፈቀደለት ቦታ ውጭ ማጨስ እንደማይቻል ስንቶቻችን እናውቃለን?——የጎንደርን ህዝብ ሳላመሰግን አላልፍም አሁንም በርቱ………………እነ አፄ ቴዎድሮስ እጅ ለጠላት አንሰጥም ብለው ህይወታቸውን ሲሰጡ ወያኔ የማፊያው ቡድን በድርድር አገር እየሸጠ ነው::ዛሬ ደግሞ በወያኔ ስብሰባ አባይ ፀሀዬ እና ሳሞራ…እኛ ታግለን የኦሮሞን ህዝብ ነፃ አወጣነው …መሬት ለነሱ ማን ሰጣቸው እንደፈለግን…በማለታቸው ምን እንደተሰማኝ መግለፅ ይከብደኛል……………………………………!አገር መሪ!የሀይማኖት መሪ የሌትትን ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይድረስላት………ወያኔንና ተቀዋሚ ፓርቲ ተብየወችን ከምድረ ገፅ ያጥፋላት………

  4. በመጀመሪያ ወያኔ ኢትዮጵያን ሊያፈራርስ ሲመጣ ወጣቱን በአደንዛዥ እፅ በማደንዘዝ ለሀገሩ ተቆርቋሪ እንዳይሆን አድርጎታል ምን አለበት ወጣቶችን የሚያስተምር ድርጅት ቢፈጠር ።

  5. እኛ ትግሉ የኦሮሞ ብቻ ነው አላልንም።

    ድል የኢትዬጵያ ነው!!!

  6. ትግሉ ተጀምሯል እረ የሀገሬ ህዝብ ዝም አትበሉ እነ ደቡብ ህዝቦች;አፋር;ሀረሪ;ጋምቤላ;የአማራ አብዛኛዉ ክፍል;2ቱ ክፍለ ከተሞች;እንዲሁም ሌሎች የሀገሬ ህዝቦች የኦሮሞ;ጎንደር እና የተማሪ እንዲሁም የሌሎች ሞኦኦኦት!!!! ዝም ያሰኛል!! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ኡ! ያገር ያለህ!!! አለቅን!!!!።

  7. Weyane is building your country, weyane is making you modern society, weyane is making you hero. If you see ethiopia 25 years back it was only a land of war hanger and hate. But now thanks to the Weyan the name ethiopia is associated with development. If you go to BBc,CNN or CCCtv you see a train roaming in the city of ethiopia.
    But for some derg reminants the good news is a head ach. They want to make ethiopia land of war and backwardnes. Industrialization, house construction, roads, trains, dams etc are the backbones of the Weyane. So they dream to see them distroyed. They wish armed by Isaias to kill ethiopian youth and distroy thiopia. But this is impossible, Weyane has changed the coarse of The Nile and I am 100% sure he will change the mind of this few reactionaries who dream to kill their mothers

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*