አየር መንገድ ተቋርጦ የነበረውን የጅቡቲ በረራ ቀጠለ

ቃለየሱስ በቀለ

ከሁለት ሳምንት በፊት የጅቡቲ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጅቡቲ ያደርገው የነበረውን በረራ እንዲያቋርጥ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት፣ በረራውን አቋርጦ የቆየ ቢሆንም ትናንትና መደበኛ በረራውን መቀጠሉን አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጅቡቲ የበረራ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በፎከር 50 ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቦምባርዲየር Q 400 አውሮፕላኖች ነው፡፡ የጅቡቲ ባለሥልጣናት፣ ‹‹እነዚህ አውሮፕላኖች አነስተኛ ናቸው፣ አየር መንገዱ ቦይንግ 757 ሊመደብልን ይገባል፤›› ሲሉ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄያቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ምክንያት፣ ባለሥልጣናቱ አየር መንገዱ ወደ ጅቡቲ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ እንዲያቋርጥ አዘው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ከጅቡቲ ባለሥልጣናት ጋር ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ፣ አየር መንገዱ ቀድሞ በሚጠቀምባቸው አውሮፕላኖች አገልግሎት መስጠቱን እንዲቀጥል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

አንድ የአየር መንገዱ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለጊዜው የበረራ አገልግሎት የሚሰጠው በQ 400 አውሮፕላን ሲሆን፣ ለወደፊቱ እንደአስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል፡፡ ከጅቡቲ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት ቀርቦ የነበረው ቅሬታ ግን አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ አየር መንገዱ ላለፉት ረዥም ዓመታት በአብዛኛው ለአገር ውስጥ በረራ ሲጠቀምባቸው የቆዩ አምስት ፎከር አውሮፕላኖችን ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡