ኤልያስ ማሞ፣ መሐመድ ናስር፣ ነጅብ ሳኒና ፍሬው ሰለሞን ለብሔራዊ ቡድን ተጠሩ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን እሑድ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከብሩንዲ አቻው ጋር ለሚያደርገው የቻን 2016 ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ አራት ተጨዋቾች በዋና አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ጥሪ ተደረገላቸው፡፡ኤልያስ ማሞ ከኢትዮጵያ ቡና፣ መሐመድ ናስር፣ ነጅብ ሳኒና ፍሬው ሰለሞን ከመከላከያ ከጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቡድኑ ጋር ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡
የኢትዮጵያና ብሩንዲ ብሔራዊ ቡድኖች የሚያካሂዱትን ጨዋታ የሚመሩት የግብፅ ዳኞች ሲሆኑ፣ ኮሚሽነሩ ሱዳናዊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ አገሮች ቻን ዋንጫ ከሚታደሙት የአፍሪካ ቡድኖች አንዱ ለመሆን ከሜዳው ውጪ ከብሩንዲ አቻው ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 2 ለ0 በሆነ ውጤትና እንድ ተጨዋቹን በቀይ ካርድ በማጣት ተመልሷል፡፡እሑድ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ 3 ጎል በማስቆጠር፣ እንዳይቆጠርባቸው ተከላክለው በጥንቃቄ የሚጫወቱ ከሆነ በ2016 ሩዋንዳ ለምታዘጋጀው የቻን ውድድር ማለፍ ይችላሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር በምድብ ‹‹ሲ›› ጋና፣ ሊቢያና ኮንጎ ጋር መደልደሏ ይታወሳል፡፡ በዚህ ውድድር ላይም ከሜዳ ውጭ ባደረገው ጨዋታ በሊቢያ አቻው 2 ለ0 በመረታት፣ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በኮንጎ አቻው 1ለ0 በሆነ ውጤት በመሸነፍ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ በጋና አቻው 1 ለ0 በመረታት ያለምንም ነጥብ ከምድቡ አራተኛ ሆኖ መጨረሱ ይታወሳል፡፡የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ቻን እ.ኤ.አ. በ2011 መስከረም ወር ላይ የጀመረ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ የመጀመርያው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ውድድር እ.ኤ.አ. 2009 በአይቮሪኮስት አዘጋጅነት የተካሄደ ሲሆን፣ በወቅቱም ኮንጎ የጋና አቻውን 2 ለ0 አሸንፎ የቻን ዋንጫን ማንሳት ችሏል፡፡ ውድድሩ ከጀመረበት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በ2014 ተሳታፊ ነበረች፡፡ከአፍሪካ አገሮች ተሳታፊዎች ውስጥ ሊቢያ፣ ቱኒዚያና ኮንጎ በቻን ውድድሩ ላይ ውጤታማ ቡድኖች ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእሑድ ጨዋታ በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፍ ከቻለ ለሁለተኛ ጊዜ በቻን መሳተፍ ይችላል፡፡