ወፈፌው ፌስቡክ… (ትንሽ ቀልዳዘል ምክር) – ዳንኤል ተፈራ
ፌስቡክ አንዳንዴ ጨርቁን ጥሎ ያብዳል። እብደቱ ገጀራ እስከማቀበል ሊደርስ ይችላል። እንደዚህ ሲሆን በተቻለ መጠን ጥግ ይዘህ አሰላስል፤ አብረህ እንዳታብድ ተጠንቀቅ።
አንዳንዴ ደግሞ ፌስቡክ ወፈፌ ይሆናል። ወፍፎ ያወፍፍሃል። አብረህ ትወፍፍና “ግን ምን ነካኝ?” ብለህ ራስህን ትጠይቃለህ።
አንዳንዴም መረን የለቀቀ ባለጌ ያደርግሃል። ያበዱ ፈላስፎች ያሳብዱሃል። በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ህወሃት ትሰልልሃለች። ፌስቡክ ቀልድ አያውቅም ሀገር አማን ብለህ ስትበሻነን መርዶ ከች ያደርጋል። መዳፎችህን ጎፈሬህ ላይ እጅህን ጭነህ ሙሾ እንድታወርድ ያስገድድሃል።
እርግማን፣ ምርቃት፣ ሹመት፣ ማንዘጭዘጭ፣ መካብ፣ መናድ… አሉ። ወገብ ተይዞ መሰደብ የሚፈልግ ካለ ሰባተኛ መሄድ ቀረ(በሳምሶን ስታይል አንብቡት)፤ ፌስቡክ ላይ መምጣት ነው። ፌስቡክ ላይ እስከ ዶቃ ማሰሪያ የሚነግር በሽበሽ ነው። ሚስትህ አርግዛ ስድብ አማረኝ ካለችህ ምንም ሳታወላዳ ፌስቡክ ላይ ውሰዳት፤ እስከሚያነቅቃት ይነግሩልሃል። ከዛ ወደ ሆስፒታል ትወስዳትና ጠጉርህን በብር ላጭተው ወፈፌ ያደርጉሃል።
አይ ፌስቡክ “የኔ ምርጥ ደህና ዋል” እያለ የሚሰድብህ ካድሬ ያለው እዚሁ ፌስቡክ ላይ ነው። ወዳጀ የፌስቡክ ፖለቲካም ወፈፌ ስለሆነ አትመነው። ስንቴ አለም ተገለበጠች ይልሃል። ደንግጠህ ስትርበደበድ ህይወት እንደነበረ ቀጥላ ታያለህ። አስፓልቱ ዳር ወጥተህ ሰላም ነው ትልና ከአንዲት በቆሎ እሸት እየጠበሰች ከምትሸጥ ደሃ የተጠበሰ በቆሎ ገዝተህ ወደ ፌስቡክ ትመለሳለህ። ምርጫ የለህማ!! ከዚህ በላይ እንዳልጥፍ እየጣፍኩ ያለሁት በብዕር ሳይሆን በሞባይሌ ፌደል እየጠነኮልኩ ነው። ስለዚህ ሚዲያ የምትለው ሁሉ ለስርዓቱ አደግድግዋልና ተፈጥሮአዊ የሆነ ሀሳብን የመግለፅ መብትህን ለመግለፅ ወደ ፌስቡክ ትመጣለህ። ይህንንም የምታነበው ተፈጥርዋዊ መብትህን ለመጠቀም ስትንጦለጦል ነው። እኔም አንደዛው።