የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሆይ! – የዒድ አል አድሐ በዓልን አስመልክቶ በእስር ከሚገኙ መሪዎቻችን የተሰጠ መግለጫ
የዒድ አል አድሐ በዓልን አስመልክቶ በእስር ከሚገኙ መሪዎቻችን የተሰጠ መግለጫ
ረቡእ መስከረም 12/2008
የመግለጫው ፒዲኤፍ ቅጂ ሊንክ፡-
http://goo.gl/XfMlRP
የመግለጫው ሙሉ ቃል በጽሁፍ፡-
*******************************
*******************************
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ፣ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው!
ጥያቄዎቻችን እስኪመለሱ እና ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናው እስከሚያከትም ትግላችንን እንቀጥል!!!
እንኳን ለ1436ኛው የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ዒድ ሙባረክ!
ረቡእ መስከረም 12/2008
አላሁ አክበር! …. አላሁ አክበር! ….. አላሁ አክበር! ላኢላሃ ኢለላህ!
አላሁ አክበር! …… አላሁ አክበር! ….. ወሊላሂል ሐምድ!
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሆይ!
በበደል እና በፍትህ መካከል የሚደረገው ተፈጥሯዊ ፍጥጫ ቀጥሏል። እንደሕዝብ አንድ ሆነን በሰላማዊ ትግላችን ላይ እንደፀናን አራተኛ የዒድ አል አድሃ በዓል ላይ ደርሰናል። በእነዚህ አስጨናቂና አጣብቂኝ የበዛባቸው አራት አመታት ውስጥ እንደ ህብረተሰብም ሆነ እንደግለሰብ ከፍተኛ መስዋእትነት ተከፍሏል። ዛሬ ላይ ሆነን ዒድ አል-አድሃን ስናከብር መስዋእትነት የነቢያት ሁሉ ፈለግ መሆኑን በመረዳት ስራችንን ወደ አላህ በማስጠጋት ያለምንም ዓይነት ቁጭት ነው። ኢድ አል ኣድሃን አማኞች ለአላህ ያላቸውን ውዴታ በመስዋአትነት የሚያሳዩበት ልዩ በዓል ነው። ነቢዩላህ ኢብራሂም ለጌታቸው መለኮታዊ ትእዛዝ እስከመጨረሻው ታዛዥ እና የፀኑ መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከሩበት፣ ልጃቸው ኢስማዒልም ለአላህ ትእዛዝ ራሳቸውን ለመሰዋት አንዳችም ማመንታት ሳያሳዩ አባታቸውን አይዞህ ያሉበት ትልቅ መንፈሳዊ ፋይዳን እና ተምሣሌትን ያዘለ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል እና የተመሠረተበት ይህ የሁለቱ አባትና ልጆች ክስተት ለእኛ ትልቅ ትምህርት ያዘለ ነው፡፡
ከሃይማኖታችንም ሆነ ከአባቶቻችን ታሪክ የምንረዳው ያለመስዋእትነት እና ጽናት ምንም ዓይነት ለውጥ አንደማይኖር ነው። ስለዚህም ‹‹በዚህ መስዋእትነትን መገለጫ ባደረገ በዓል ላይ ሆነን አሁንም የተነሳንባቸው ጥያቄዎች እስኪመለሱ እና ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናው አስኪቆም ድረስ በትግላችሁ በጽናት ልትቆሙ ይገባል›› ስንል አደራችንን እናስተላልፋለን፡፡
ምንም እንኳን በእስር ቤት ነንና ከምንወደው ሕዝባችን ጋር በዓሉን ለማሳለፍ ባንችልም ዒድ አል አድሃን እንደህዝብ ስናከብር ደስታችን በእኛው እና በቤተሰቦቻችን ብቻ የሚወሰን እንዳይሆን መጣር እንዳለባችሁ ለማስታወስ እንወዳለን። ወንድማማችነት የበለጠ እንዲጠናከር የምታደርጉበት፣ በትግሉ ምክንያት ከቤት እና ከቤተሰቦቻቸው የተለዩ ወንድም እና እህቶቻችሁን የምትዘይሩበት፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ፣ በዝዋይ እና በሻሸመኔ ብዙ ግፍና ስቃይ ከበዛበት እስራት የተፈቱትን ወንድሞቻችንን የምታበራቱበት አጋጣሚ ሊሆን ይገባል። ሁላችንም በያለንበት የተያያዝነው ተውሂድን በአስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የማቆየት ትግላችንን አጠናክረን አደራችንን ለመወጣት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት በዓልም መሆን ይኖርበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሙስሊሙን ህብረተሰብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ምንም ዓይነት ዝግጅት በማይታይበት ሁኔታ በሙስሊሙ መካከል ልዩነት ያለ ለማስመሰል የሚደረጉ የማታለያ እና አቅጣጫ የማስቀየሪያ ጥረቶች ከዋናው አጀንዳችሁ እንዳያዘናጓችሁ ዘወትር በተጠንቀቅ መቆም እንደሚኖርባችሁ ለማስታወስ እንወዳለን፤ ትግሉ አስቀድሞ በወጣለት የትግል አቅጣጫ መሰረት መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን አስኪመለሱ እና ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናው እስከሚያከትም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልና።
በትግል መስመር ላይ መከራ እና ፈተናን መጋፈጥ የተለመደ የእውነተኛ የአላህ አገልጋዮች ፈለግ ነው። እኛም በዚህ ፈታኝ የትግል ሂደት ውስጥ እንደ እስካሁኑ ሁሉ አሁንም በጥሩ ጽናት እና ጥንካሬ ላይ መሆናችንን ስንገልጽላችሁ መስዋእትነት መክፈል ባስፈለገበት ወቅት ለመክፈል መብቃታችን ትልቅ የአላህ ችሮታ መሆኑን በመገንዘብና ለኃያሉ ፈጣሪያችን ምስጋናን በማቅረብ ነው። አገራችን ፍትህ ሰፍኖባት፣ የህዝቦቿ ነጻነት ተረጋግጦ ማየት የእስር ቤት ግድግዳ አፍኖ የማያስቀረው የዘወትር ህልማችንም ነው። ለአገራችንና ለእድገቷ፣ ለሰላሟ እና ለልማቷ አበክረን የምንሰራ፣ በእምነታችን ምክንያት የታወጀብንን ብሄራዊ ጭቆናን ለማስወገድ የምናደርገው ትግልም ወገንን እና አገርን ቅድሚያ ታሳቢ ያደረገ መስመርን የተከተለ መሆኑን አጥብቀን እናምናለን፡፡ ምንጊዜም ለጋራ ጥቅም እና ለተሻለ ሰላምም ዝግጁዎች ነን።
እስከዛሬ በነበረው የትግል መስመር የተጎናጸፍናቸውን አንጸባራቂ ድሎች በመያዝ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አሁንም ጥያቄዎቹን ለማስመለስ እና ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናውን ለማስቀረት፣ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ መብቱን ለማስከበር መላውን ህብረተሰብ አሳታፊ በማድረግ ትግሉን መቀጠል ይኖርበታል። ራስን ብቁ በማድረግ ላይ ያተኮረው እና በመንግስትም ላይ ጫና ፈጣሪ የሆነው ትግላችን ሊቀጥል ግድ ነው፡፡ ቀድሞ በተቀመጠው የትግል አቅጣጫም ለመጓዝ እንረባረብ። የፓለቲካ ፍጆታን በመሻት የሚደረጉ የማደናገሪያ እርምጃዎችን በመጠንቀቅ ትግላችንን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ እናደርስ ዘንድ የሁልጊዜም ጥሪያችን ነው – ኢንሻአላህ!!!
አላሁ አክበር! …. አላሁ አክበር! ….. አላሁ አክበር! ላኢላሃ ኢለላህ!
አላሁ አክበር! …… አላሁ አክበር! ….. ወሊላሂል ሐምድ!
ብሄራዊ ጭቆናን እንታገል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
