የህንድ ኩባንያ የአዲስ አበባን ሁለት እጥፍ መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበ
(ሪፖርተር) — ቻድሃ የተባለው የህንድ ኩባንያ በእርሻ ሥራ ላይ ለመሠማራት የአዲስ አበባን ሁለት እጥፍ የሚሆን 100 ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበ፡፡ ጥያቄውን በማስተናገድ ላይ የሚገኘው የግብርና ሚኒስቴር ለኩባንያው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኘው ጉጂ ዞን ካሁን በፊት 22 ሺሕ ሔክታር መሬት ሰጥቶታል፡፡ ኩባንያው በዚሁ መሬት ላይ የሚያሳየው የልማት እንቅስቃሴ ታይቶ የጠየቀው 100 ሺሕ ሔክታር ሊሰጠው እንደሚችል ከኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ካገኘነው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ቻድሃ የተባለው ኩባንያ መሬቱን የጠየቀው በስኳር ልማት ኢንቨስትመንት ለመሠማራት መሆኑን የሚያሳየው የኮሚሽኑ መረጃ፣ በዕቅዱ መሠረት ኩባንያው በሰፊ መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ እርሻ ያካሂዳል፣ ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ይገነባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባለፈው ሰኔ 2002 ዓ.ም. ሰባት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ የኢንቨስትመንት ካፒታል የተመዘገበው የህንዱ ኩባንያ በሊዝ በወሰደው 22 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱን በቅርቡ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
ኩባንያው ወደፊት የሚገነባው የስኳር ፋብሪካ ግዙፍ እንደሚሆንና የማምረት አቅሙም በመንግሥት የሚገነባው የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ወደፊት ሊያመርት ከሚችለው የምርት መጠን ጋር ሊስተካከል እንደሚችል የኩባንያው ዕቅድ ያሳያል፡፡
ኩባንያው በጠየቀው 100 ሺሕ ሔክታር ላይ ማምረት ሲጀምር ለ35 ሺሕ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ዕቅዱ ያመለክታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቁጥራቸው እያደገ የመጡትንና እስከ 300 ሺሕ ሔክታር መሬት ለእርሻ ልማት የጠየቁትን አልሚዎች ቁጥር ከፍ የሚያደርገው የህንዱ ኩባንያ በዕቅዱ መሠረት ምርቱን ለውጪ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቻድሃ ከተባለው ኩባንያ በተጨማሪ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ከጠየቁና ከጠየቁት መሬት የተወሰነውን ከወሰዱት ውስጥ፣ ሌላኛው በዓለማችን ላይ ትልቁ የአበባ አምራች የሆነው ካራቱሪና በቅርቡ የተቋቋመው ሳውዲ ስታር የተባለው የሼክ አላሙዲ ኩባንያ ይገኙበታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ስኳር በማምረት ላይ የሚገኙት ሦስቱ የመንግሥት ፋብሪካዎች ማለትም ወንጂ፣ ፊንጫና መተሐራ ሲሆኑ፣ አል አበሻ የተባለ የፓኪስታን ኩባንያ በቅርቡ ስኳር ማምረት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡