ታዋቂ አሊም ሼኽ ጂላን አዳኖ( አቡ ዓብዱረህማን) መንግስት በሽብርተኝነት መክሰሱ ታወቀ

መንግስት ሼኽ ጄይላን ኣደምን በሽብርተኝነት መክሰሱ ታወቀ

በራዲዮ ዳንዲ ሃቃ ነሀሴ 18 /2007

በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና ዞን ነዋሪ የነበሩትና በህዝበ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ተወዳች የነበሩትን ታዋቂ አሊም ሼኽ ጂላን አዳኖ( አቡ ዓብዱረህማን) ለሀጅ ፕሮሰስ አዲስ አበባ በመጡበት በእንግድነት ካረፋበት ቤት በደህንነቶች ተይዘው መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የመንግስት የደህንነት ሃይሎች በአካባቢው ሙስሊም ህብረተሰብ ዘንድ በጣም ተወዳጅ የሆኑትን ፣ ጠዋት ማታ ህዝቡን በማስቀራት ፣ ዳዕዋ በማድረግ እና በዛሂድነታቸው የሚታወቁትን : እኒህን ኣሊም ለሃያ ሰባት ቀን ያክል በማዕከላዊ ካሰቃዩዋቸው በኃላ : በትላንትናው እለት ሰኞ ነሀሴ 17 በአራዳ ምድብ ችሎት በማቅረብና በሽብርተኝነት በመክሰስ ተጨማሪ የሀያ ስምንት ቀን ቀጠሮ እንደጠየቁባቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።

አብሮዋቸው ታስሮ የነበረውና ከቦረና የመጣው ዳዒ መሊቹ ሁቃ : ከተወሰኑ ቀናት እስር በኃላ መለቀቁን የገለፁት ምንጮቻችን : በእንግድነት ያረፋበት ቤት ባለቤት የሆነው አቶ ሪድዋን ግን አሁንም ድረስ አለመፈታቱን : ነገር ግን በእርሳቸው ላይ በሀሰት እንዲመሰክር በየቀኑ ጫና እየፈጠሩበትና እያሰቃዩት መሆኑንና በቤተሰቡ ግን እየተዘየረ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እኚን በህዝባቸው ዘንድ ተወዳጅ ተሰሚና ትልቅ ቦታ ያላቸው ታላቅ ኣሊም ከቤተሰብ ከወገናቸው አለማገናኘቱ ሳያንሰው እሳቸውን በሽብርተኝነት ከሶ የሃያ ስምንት ቀን ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል።

መንግስታዊ ዳኞችም በአቃቤ ህግ የተጠየቁትን የሃያ ስምንት ቀን : ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ ተቀብለው ለመሰከረም 11 2008 ቀጠሮ ሰጥተዋል። የፍርድ ቤቱን ሂደት የተከታተሉትና: በቅርብ የሚያውቋቸው ሙስሊሞች የሚወዷቸው ሼክ በጣም ተጎሳቁለው ያለ ኮፍያ ራሳቸው ተከፍቶ ሲያዩ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉና እንዳለቀሱ ምንጮቻችን አያይዘው ገልፀዋል።

መንግስት በሙስሊሙ ኀብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና: ከእለት ወደ እለት አጠናክሮ መቀጠሉን የገለፁት ታዛቢዎች : ኢስላም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ኡለሞች ላይ እንዲህ አይነት ግፍ የተሞላበት እርምጃ መጀመሩ : ይህ መንግስት የትናንት አፄዎች : በአባቶቻችን ላይ በእምነታቸው ምክንያት ብቻ ይወስዱባቸው የነበረውን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር : ዛሬ የእነሱ ልጅ በሆነው በኛ ላይ ለመድገም እየተንደረደረ መሆኑን በአንክሮ ገልፀው : ሙስሊሙ ህብረተሰብ የዲኑ ብርሃን በሆኑት ኡለማዎች እና በዲኑ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ደባ በአንክሮ እንዲከታተለውና : መክፈል ያለበትን መሰዋእትነት ሁሉ በመክፈል ዲኑን እና የዲኑ ብርሃን የሆኑትን ኡለማዎች እንዲጠብቅ አደራ ብለዋል።

አላህ ሱ:ወ ዲኑን ኡለማዎቻችንና መላውን ሙስሊም እንዲጠብቅ እንማፀነዋለን !!!