በአዲሱ የዋጋ ተመን ምክንያት ግራ መጋባት እና ውጥንቅጥ በአዲስ አበባ ገበያዎች ላይ ሰፍነዋል ተባለ

መለስ ዜናዊ፥ እራሱን ከቱኒዚያ አይነት ህዝባዊ አመጽ ለመከላከል ሲል የወሰደው የችኮላ እርምጃ ከአሁኑ ብዙ ችግሮች እየታዩበት እንደሆነ ከአዲስ አበባ የሚደርሱን ዘገባዎች እያመለከቱ ነው።

በቅርቡ፥ የራሱ የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የፈጠረውን ችግር በነጋዴዎች ላይ ለማላከክ ሲል ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ በተለያዩ ምርቶች እና ሸቀጣሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን መጣል እንደሆነ ይታወቃል። ይህም እርምጃ ከወዲሁ ብዙ እክሎች የገጠሙት ሲሆን፤ ለበርካታ ቸርቻሪዎች መታሰር እና ለንግድ ቤቶች መዘጋት ምክንያት ሆኗል።

ሪፖርተራችን በላከው ዘገባ እንዳመለከተው ደግሞ፥ እንደ ስኳር ያሉ ሸቀጣሸቀጦች ፈጽመው ከገበያ እየጠፉ ነው። ይህም፥ የዋጋ ተመኑ ይጠቅመዋል የተባለውን ህዝብ መልሶ ጎድቶታል።

የዋጋ ተመኑ አዋጅ ከወጣ በኋላ በአዲስ አበባ ገበያ ላይ ግራ መጋባት እና ውጥንቅጥ መፈጠሩን አዲስ ፎርቹን የተባለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ዘግቧል። አገዛዙ አዋጁን ባስተላለፈበት በጥቂት ቀናት ውስጥ መልሶ የአንዳንድ ሸቀጣሸቀጦችን ዋጋ ለመጨመር ተገዷል። የዋጋ ተመኑ በስራ ላይ መዋል ያለበት በጅምላ ሻጮች ይሁን በቸርቻሪዎች ዘንድ ግልጽ አለመሆኑ ነጋዴዎችን እና ተጠቃሚዎችን ግራ አጋብቶ ሰንብቷል። በመርካቶ አካባቢም ክርክር እና ውጥንቅጥ እንደተበራከተ ለማወቅ ተችሏል።

የንግድ ሚኒስቴር ዲኤታ አህመድ ቱሳ በቀድሞው ዋጋ ሸቀጣሸቀጥ የገዙ ነጋዴዎችን አስመልክቶ፣ ለተወሰነ ጊዜ ኪሳራውን ከመቻል ውጪ አማራጭ የላቸውም ብሏል።

ሪፖርተራችን ያናገራቸው የመዲናይቱ ነዋሪዎች፥ አገዛዙ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቀነሰውን ዋጋ መልሶ መጨመሩን አስመልክቶ ሲናገሩ፥ እርምጃው ቀድሞውኑ ሲወሰድ ጥናት እንዳልተደረገበት ያሳያል ብለዋል።