የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ዳግመኛ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ

በመለስ ዜናዊ የሚመራው የትግራይ ገዢ ቡድን በሱማሌ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው ሲል የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር መግለጫ መስጠቱን ሬውተርስ የዜና አገልግሎት ገለጸ።

አስራ ሰባት ዜጎች በደህንነት ሰዎች ታፍሰው በተወሰዱ ማግስት፥ ጥር 9 ቀን ከተወሰዱት ሰዎች መካከል የነበሩት አንድ የመንግስት ሰራተኛ እና አንድ ነጋዴ በቀብሪደሃር አካባቢ ሞተው መገኘታቸውን ግንባሩ ገልጿል። ሰዎቹ ታንቀው እንደተገደሉ እና አስከሬናቸው ሲገኝ በአንገታቸው ዙሪያ ሽቦ እንደነበርም ዘገባው አመልክቷል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ፥ የአገዛዙ ወታደሮች የሂግላላይን ከተማ ሲዘርፉ የአንዲትን ሴት አንገት እንደቆረጡ እና ሃያ ሰባት ሰዎችን እንዳቆሰሉ ግንባሩ አስታውቋል።

ከመለስ ዜናዊ እና ከበረከት ስምኦን ቀጥሎ በዋሾነቱ ዝናን ያተረፈው የአገዛዙ ቃል አቀባይ ሽመልስ ከማል እንደወትሮው ክሱን ክዷል። ይሁን እንጂ፥ ዘረኛው አገዛዝ ከዚህ ቀደም በዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በጦር ወንጀል እና በሰብአዊ ፍጡራን ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚከሰስ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ባሉ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ አንዳንድ ምንጮች፤ አገዛዙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠረፋማ ክልሎች ውስጥ እየፈጸመ ያለውን የመሬት ንጥቂያ እና የግዳጅ ሰፈራ ተከትሎ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊከተል እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።