የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት እራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል
የቱኒዚያው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ ሊደገም ይችላል በሚል ስጋት፣ አንዳንድ የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት እና ቅጥረኞቻቸው እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከጥቃት ለመከላከል እርምጃዎች መውሰድ እንደጀመሩ ለማወቅ ተችሏል።
ሪፖርተራችን የምንጮቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ስሙን የማይጠቅሰው አንድ የዘረኛው አገዛዝ ቅጥረኛ፣ በአውሮፓ የምትማር ልጁ ወደ ኢትይዮጵያ እንዳትመጣ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷታል። እንደ ምንጮቻችን፥ ይህች ወጣት ልጅ የቀን ገደብ የሌለው የአየር ቲኬት ተሰጥቷት ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ሌላ የአውሮፓ አገራት በየጊዜው ለእረፍት የምትጓዝ ነች።
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ስለሰሩት ግፍ ጠንቅቀው የሚያውቁት የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት፣ በምርጫ 97 ማግስት ገንዘባቸውን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ውጭ አገራት በማሸሽ ተጠምደው እንደነበረ ይታወሳል።
የንግድ ሚኒስቴር ዴኤታ አህመድ ቱሳ፥ አገዛዙ የዋጋ ተመን ያወጀው በቱኒዚያ የተፈጠረው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ እንደሆነ ማመኑን የሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። አህመድ ቱሳ በግልጽ በተደረገ ስብሰባ ላይ ይህንን ማመኑ ግሳጼን ሊያስከትልበት እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይገምታሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ በህዝብ አመጽ ከአገሩ የተባረረው የቱኒዚያ አምባገነን ቤን አሊ እና ቤተሰቦቹ 3.5 ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያህል ሃብት ከአገራቸው እንደመዘበሩ እና ከዚህም ውስጥ አብዛኛው በፈረንሳይ አገር ባንኮች እንደሚገኝ ዘገባዎች አመልክተዋል። የአምባገነኑ ባለቤት ለይላ ትራበልሲም ከአገር ከመውጣቷ በፊት ወደ ቱኒዚያ ማእከላዊ ባንክ በመሄድ አንድ ሺህ አምስት መቶ ኪሎግራም ወርቅ መዝረፏን የፈረንሳዩ ለሞንድ ጋዜጣ ዘግቧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቱኒዚያ ህዝባዊ አመጽ ለወደቁት ሰማእታት የሶስት ቀን መታሰቢያ እንዲደረግ መወሰኑ ታውቋል። በእራሱ ላይ እሳት በማቀጣጠል የሃያ ሶስት አመቱን አምባገነናዊ ስርአት ለመጣል የበቃውን የህዝብ ቁጣ የጫረው ወጣት ሙሃመድ ቦዚዚ በአገሩ ህዝብ ዘንድ እንደ ጀግና እየተዘከረ ይገኛል። አንዲት ቱኒዚያዊት እናት “ዩሮ ኒውስ” ለተባለው የቴሌቪዥን አገልግሎት በሰጡት ቃል፥ “ሙሃመድ ቦዚዚ ከፍርሃት ነጻ አወጣኝ” ሲሉ አሞግሰውታል።
ላለፉት ሃያ አመታት ኢትዮጵያን በግፍ ሲገዛ የቆየው መለስ ዜናዊ ቢያንስ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ቡድኖችን ከስራ ውጪ አድርጌያለሁ ብሎ ቢተማመንም፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቦዚዚዎች ባልታሰበ ጊዜ ሊነሱ መቻላቸው ባለስልጣናቱን አስጠብቧቸዋል።