ትውስታዬ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር – ክፍል 2

ከይሁን ነጻነት

ክፍል አንድ የአቶ ሃዱሽ ገ/እግዚአብሄር መልካም ፈቃድ ሁኖ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር መቀጠሬን ገልጬ ነበር። እነሆ ቀጣዩ ክፍል ሁለት፤
ህወሃት ሠርቶና ለክቶ በወሰነልኝ የአስተሳሰብ መጠን መሰረት አስቤ፤መልካም የምለውንም ምኞት ተመኝቼ፤ምኞቴንም እውን ለማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተቀጥሬ በጣም መራርና ከባድ የሆነውን ኑሮ ተያያዝኩት።ወሩ በገባ በሃያኛው ቀን ኪሴ ውስጥ የሚቀረው ገንዘብ ቁርስ፤ምሳና እራቴን ለመብላት አልበቃ እያለኝ ተቸገርኩ።ጠጪ አይደለውም።ገንዘብ እንዲሁ በቀላሉ የማባክንም ሰው አይደለውም።ብዙውን ግዜ ደግሞ እጾማለሁ።እንዲህም ሁኜ ከ600 ብር ተቆራርጦ የሚደርሰኝ 520 ብር ጨርሶ ከወሩ ጥግ አያደርሰኝም።ከወሩ ውስጥ አምስቱን ቀናት ራቴን ዳቦ በሙዝ እየጨረግድሁ አድራለሁ።አንዳንዴም አጋጣሚ ሆኖ ከደላኝ አቦካዶ ገዝቼ እርሱን በዳቦ ገምጬ ተመስገን ብየ እተኛለሁ።በእንቅልፍ ከመውደቄ በፊት ግን ውጭ ስመደብ ይሄ ሁሉ እንደሚቀየር ስለሚሰማኝ ሥራየን ብቻ በርትቼ መሥራት እንዳለብኝ ለራሴ ነግሬ ጨለማው ሂዶ ብርሃን እስኪወጣ ለጥ እላለሁ።ሲነጋም ተነስቼ ፊቴን ተጣጥቤ በእግሬ ወደ ቢሮየ አዘግማለሁ።እግረ መንገዴን ግቢ ገብርኤል ጎራ እልና ጠበል መጠጣትን አልረሳም።ቁርስ መብላት ሲያቀተኝ ቁርስ ይሆነኝ ዘንድ ሁለት ጣሳ ሙሉ ቅዱስ ውሃ እጠጣለሁ።ይህን ቅዱስ ውሃ ስጠጣ ለምን እንደሆነ አላውቅም ሳይርበኝ እስከ ምሳ ሰዓት እቆያለሁ።11% ኢኮኖሚው አደገ በሚባልበት አገር ውስጥ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በዚህ ሁኔታ ይኖራል። በዘመነ ህወሃት ይህን የኢኮኖሚ እድገት መጠራጠር ወንጀል በመሆኑ እየራበንም ቢሆን የአገሪቷ ኢኮኖሚ በ11% አድጓል ሲባል አዎን እውነት ብለን እንድንቀበል ግዴታ ተጥሎብናል።ይህን አለማመን በአሸባሪነት ከሚያስከስሱ ዋና ነገሮች የሚመደብ ነው።

እስኪ ዘወትር ኢኮኖሚያችን በ11% አድጓል እያለ የሚያደርቀኝና ከእኔው ጋር አንዲቷን ቢሮ ወደ ሚጋራኝ ግለሰብ እንሂድ።
“ተራራውን አንቀጥቅጬአለሁ” ከሚለው ህወሃት ከተሰኘው ደርጅት ጋር ከትግል ሜዳ ያልዋለ ነገር ግን ከከተማ ሁኜ ስረዳ ነበርኩ የሚል አንድ አባል አብሮኝ አለ።ይህ ሰው “የነጻነት ታጋዮች” ነን ባዮች አገሪቷን ከተቆጣጠሩ በኋላ በለስ ቀንቶት በሚያስገርም ፍጥነት ትልቅ ህንጻ አሠርቶ ለውጭ አገር ሰዎች አከራይቶት በየወሩ 42 ሺህ ብር ይሰበስብ ነበር።ይህ ግለሰብ አለቃ የለውም።አለቃ ያለኝ እኔ ነኝ።እርሱ ደስ ባለው ሰዓት መኪናውን አስጓርቶ ልቡ ወደ መራው ይሄዳል ባሰኘው ሠዓት ደግሞ ይመለሳል።እኔ ከማን ጋር ሻይ እንደጠጣሁና የት እንደዋልኩ ፌርማቶሪ ተመድቦ አንደበቴን ይመለከታል።እርሱና መሰሎቹ አሳዳጅ እኔ ተሰዳጅ ሁነን በኢትዮጵያችን እንኖራለን።ሁለት የተለያየን ዜጎች በኢትዮጵያ አለን።ኢትዮጵያ የእኔና የእነርሱ አገር ብትሆንም እነርሱ ግን የሌላ ባእድ አገር የሚገዙ ይመስላቸዋል።እኔም ለእነርሱ እንደ ባእድ ነኝ።

የእነርሱ ላልሆነች አገር ደግሞ ምን አሳሰባቸው ? እኔን የመሰሉ ብዙ ሚሊዮናት ሲራቡ፤ሲጠሙ ፤ሲታረዙ፤እነርሱ ይስቃሉ እንጂ ትንሽም ደንገጥ አይሉም።በበሉትና በጠጡት መጠን እነርሱ እድገታችን ነው የሚሉትን እየለኩት ያደርቁናል እንጂ የእለት ጉርሱን አጥቶ በየሜዳው ወድቆ የሚቀረው የአገሪቱ ዜጋ አይታያቸውም።የእነዚህ ቡድኖች ብርቱ ችግር ሰዎች ሁሉ የእነርሱን ውሸት እንዲያምኗቸው ጽኑ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን በውሸታቸው አልተባበር ያላቸውን ሁሉ እንደጠላት ማየታቸው ነው።እኔ የመንግስት ሠራተኛ ሁኜ ከሰላሳ ቀኖች መካከል አምስቱን ቀን መራቤና መጠማቴ እውነት ነው።ብዙ ህጻናት እዚያ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ፊት ለፊት ሜዳ ላይ ወድቀው መኖራቸው ሌላው እውነት ነው።ህወሃቶች በዚህ እውነት ፈንታ 11% አድጓል የሚሉትን ብልጽግና እንዳምናቸው ይፈልጋሉ።የቢሮየ ተጋሪም የእርሱን ውሸት እውነት ነው ብየ እንደቀበል ይፈልጋል።ከህወሃት ብርቱ ችግሮች መካከል አንዱ ውሸቴን እመኑልኝ ማለቱ ነው።
ይህ የህወሃት አባል እንደፈለገ እየሆነ “ይህች ደግሞ ምን አላት” ብሎ የሚንቃትን የወር ደመወዙን ሳይቦዝን ይቀበላል።መቸስ የአገሪቷ ህግ እርሱን ለመሰሉት ሁሉ መጠቀሚያ እኔን ለመሰሉት ደግሞ መጠቂያ ሁኖ ተሰርቷል።በዚያች አገር እኔንና እርሱን እኩል የሚገዛ ህግ የለም።እርሱና መሰሎቹ ከህግ በታች ላለመሆን “ነፃ” ወጥተው ከህግ በላይ ሁነዋል።ግንቦት ሃያንም ይሁን የካቲትን የሚያከብሩት እነርሱ ከህግ በላይ የሆኑበት፤ሌሎች እነርሱ ህግ ከሚሉት በታች የሆኑበትን ቀን ለመዘከር ነው።እነርሱንና እኔን እኩል የሚገዛ ሥርዓት ቢሰራ ጥቅማቸው ስለሚቀርባቸው እንዲያ ያለ ሥርዓት እንዲፈጠር ፈጽሞ አይፈልጉም።እንዲህ ያለ ነገር የሚጠይቅ ካለም አሸባሪ ይባልና የመከራ እንጀራን ይበላል፤ የመከራ ጽዋንም ይጎነጫል።የቅንጅት መሪዎች የታሰሩት የህግ የበላይነት ይስፈን በማለታቸው መሆኑን እኔም እናንተም እናውቃለን።
የቢሮየ ተጋሪ የሥራ ደረጃው አንደኛ ጸሃፊ ነው።በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሥራ እርከኖች ከምሩቅ አታሼ ጀምሮ አታሼ ፤ሶስተኛ ጸሃፊ፤ሁለተኛ ጸሃፊ፤አንደኛ ጸሃፊ ፤አማካሪ፤ምንስትር አማካሪ ከዚያ እድለኛ የሆነ ከተገኘም አምባሳደር ይሆናል።እነዚህን የውጭ ጉዳይ እረከኖች አልፎ በችሎታውና በልምዱ ለአምባሳደርነት ደረጃ የበቃ ሰው አሁን ባለው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ውስጥ የለም።በእርግጥ አምባሳደር ቆንጅት የምትባል አለች።እርሷ የጊዜው ፖለቲካ ገብቷትና ዓለማችን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ተርዳታ አገራችንን ትጠቅማለች ተብላ የቆየች አይደለችም።ሴትየዋ ግዜ ተወስዶ የተተየቡ ደብዳቤዎችን “እዚህ ጋ ንጉሱ ‘ሠ’ ነው መግባት ያለበት፤እዚህ ጋ ደግሞ ዓይኑ ‘ዓ’ ነው መግባት ያለበት እያለች ለንጉሱ ‘ሠ’ እና ለዓይኑ ‘ዓ’ እያለች ግዜ ተወስዶ የተጻፈባቸውን ደብዳቤዎች ቀዶ ከመጣል በቀር ይሄ ነው የሚባል እውቀት የላትም።
ሌላ እውቀቷ ደግሞ “ኦባሳጆ እኮ ወሬኛ ነው።ጋዳፊ ባለጌ ነው።አለባሽር የዋህ ሰው ነው።ቻርሌስ ቴይለር የነጭ አሽከር አጨብርባሪ ነው” ማለትን ግን ተክናበታለች።ይህ ደግሞ ሃሜት ነው።

በሶስቱም ሥርዓት በዚያ መስሪያ ቤት ለመቆየት የቻለችው ሃሜተኛ እና አደር ባይ በመሆኗ እንጂ ለዲፕሎማሲ የሚሆን እውቀት ኑሯት አይደለም።እርሷ ሂሊናዋ ስለማይጠይቅ ለመልአክም ይሁን ለሰይጣን ለማገልገል አይከብዳትም።በንጉሱ ዘመን ዲፕሎማት ነበረች፤ መንጌ ንጉሱን ገድሎ ሲመጣ ደግሞ ከፍ ብላ አምባሳደርነትን ተቀብላ እሰይ ብላ ኖረች፤ ህወሃት ደግሞ ደርግንም ኢትዮጵያንም አንድ ላይ በልቶ ሲመጣም እርሱን ተቀብላ አሁንም እሰይ ብላ ደርግን እያማች አብራ ቀጠለች።ህወሃት የአጼ ሃይለ ስላሴ ሃውልት በአፊሪካ አዳራሽ አያስፈልግም ሲል እርሷም አዎን አያሳፈልግም ብላ ኑሯዋን ትኖራለች።ይህቺ ሴት አማራ ነች ቢሆንም ግን እነመለስ “አማራና ኤምፔሪያልዝም የትግሬ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው” ብለው የጻፍትን ሰነድ ያየችው አይመስለኝም።ምክንያቱም ማንበብና መጠየቅ እጣ ክፍሏ አይደሉም።ብታነበውም እንዲህ ዓይነቱን ነውር ለመቃወም የሞራል ልቀቱ ያላት ሴት አይደለችም።
የትምህርት ደረጃዋን በተመለከተ ድሮ በንጉሱ ዘመን ከእንግሊዝ አገር በሴርትፊኬት ተመርቃለች።ከዚያ ልቃ ሂዳ ቀለም አልቆጠረችም።

ከእንግሊዝ አገር ሰርቲፊኬቷን ይዛ እንደተመለሰች እንዲህ የሚል ማመልከቻ ጻፈች፤
“ከእንግሊዝ አገር ያገኘሁት ስርቲፊኬት ከኢትዮጵአያ ድግሪ ጋር የሚተካከል በመሆኑ በዲግሪ እንዲያዝልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ”
ይህ እንግዲህ ንጉሱ ሳይወርዱ የተጻፈ ማመልከቻ ነው።የንጉሱ ሹምም እውቀቷን ሳይሆን ጀርባዋን አይተው ቀጠሯት።ሴትየዋ በጻፈችው ደብዳቤ ውስጥ ለገዛ አገሯ ያላትን ንቀት ማየት የምትችሉ ይመስለኛል።

የስድስት ወር የምስክር ወረቀት እንደምን ሁኖ ድፍን አራት ዓመት ተለፍቶ ከሚገኝ ድግሪ ጋር እኩል ይሁንልኝ ተብሎ ይጠየቃል ?ለዚያውም በንጉሱ ዘመነ መንግስት። “ክብርት” አምባሳደር ቆንጅት ስነጊዮርጊስ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ካላት መልስ እንድትሰጥበት እጠይቃለሁ።አምባሳደሯ በህይወት ዘመኗ ትዳር አልያዘችም፤ ልጅም አልወለደችም።አምባሳደር የሚል ቅጽል ባይኖራት ኑሮ በስተርጅናዋ ዘመን ወ/ት ተብላ ትጠራ ነበር።እደለኛ ነች መደበቂያ ቅጽል ማንጠልጠልን ችላበታለች።

የወ/ሪት ቆንጂትስ ይሁን አስራ ሁለተኛን ጨርሳ እንግሊዝ አገር ሂዳ ጥቂት ተምራ ሰርቲፊኬት አምጥታለች ደግሞም ነጉሱ “ሠ”ን እና ዓይኑ “ዓ”ን ጠንቅቃ ለይታለች። በዘመነ ህወሃት ፊደል ቆጥረው መጨረሳቸው በውል ሳይለይ በህግ ማስትሬት ድግሪ የታደሉ ብዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሞልተው ተርፈው የለም እንዴ ? አገሪቷስ የምትመራው እንዲህ የአገሪቷን የትምህርት ስርዓት በሚያፈርሱ ቡድኖች አይደለም እንዴ ? ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት በስዊድን የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛ መብራት በየነ የምትባልን ሴትዮ ማየት ይቻላል።ይህች ሴት አሥራ ሁለተኛ ክፍል መጨረሷ በውል አይታወቅም፤የመጀመሪያ ድግሪ የሚባል የላትም ግን ደግሞ በህግ ማስትሬት ዲግሪ ተቀብላለች።የአገሪቷን ትምህርት ሥርዓት ከናደችው በኋላ የህወሃት መንግስት ልዩ መልእክተኛ ሁና ተሹማለች።
“ንግባኢኬ ሃበ ጥንተ ነገር”ይላል አንድ መጽሃፍ ወደ ቀድሞ ነገራችን እንመለስ ማለት ነው።

የቢሮየ ተጋሪ ደመወዙ ተጨምሮበት በወር ከ43 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኛል።እኔ በወር የተጣራ 520 የኢትዮጵያ ብር ሲደርሰኝ እርሱ ያን ያክል ማግኘቱ በዜጎች መሃከል እየተፈጠረ ያለውን የሃብት ክፍፍል ልዩነት ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ነው።እርሱም የመጀመሪያ ዲግሪ አለው።እኔም ከአዲስ አበባ ዩንቭርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ።ታዲያ ይሄ ሁሉ ልዩነት እንዴት ተፈጠረ ? እንደሰው ለፍቶ ጥሮ ግሮ በላቡ በወዙ አግኝቶ ልዩነቱን ፈጥሮ ቢሆን መልካም ነበር።ነገሩ ግን እንዲያ አይደለም።ዝርፊያ ነው።አገሪቷ የእነርሱ ስለማትመስላቸው የመንግስትን ስልጣን ተገን አድርገው ኮንትራባንድ ይነግዳሉ።መሬት ይነጥቃሉ ይሽጣሉ።ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ማንኛውንም ወንጀል የተባለ ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ።በአጠቃላይ አገሪቷን ባለው መንገድ ሁሉ በመቀራመት ተግባር ላይ ተጠምደዋል። የአገሪቷን መሬት እንደልባቸው ለመሸጥና ለመለወጥ ህወሃቶች መብቱ አላቸው እኔ ያ መብት እንዳይኖረኝ በህግ ደህና ተደርጌ ታስሬአለሁ።እነርሱ የዜጎችን መሬት ነጥቀው ይሸጣሉ ይለውጣሉ።እኔ ግን ወላጆቼ ያወረሱኝን መሬት እንኳ እንዳልሸጥ እንዳልለውጥ ህግ ተሰርቶልኛል።የህወሃት ዓባል የሆነ ሁሉንም ነው።ለእነርሱ ወሰንና ገደብ የለም እነርሱ ከሁሉ በላይ ናቸው።
እኔ የህወትን በጎ ነገር የማውቀው የለም። ህወሃቶች ሰው ምን ይለኛልን አያውቁም እንጂ የዚህ ድርጅት አባል መሆን ከአሳፋሪ በላይ ነው።እንዲያውም በነውራቸው ኮርተው በትግራይ 100% በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በ99.6% ተመርጠናል ብለው አገሪቷን በግምት እየገዟት ይገኛሉ።ምን ያድርጉ ሰው የሌለበት ባዶ ቤት አገኙ ፤ያንንም ቤት ጠያቂ ጠፋ እነርሱም በዚያ ጌቶች ሆኑ።እኛም የምናደርገውን አጥተን ዝም አልን።
መጥኔ ለህወሃቶች !!! መጥኔ ለእነርሱ !!! ብለን እንቀጥል።

አሁንም ወደ ቢሮየ ተጋሪ ግለሰብ እንመለስ።ከዚህ ሰው ጋር ብዙም ማውራት አልወድም።ክፉ ትእቢተኛ ነው።ሃይማኖቱን የማያውቅ ወይም ደግሞ የዓለሙን ነገር በደንብ የማይገነዘብ ዞንቢ ነው።ለሰው ልጆች ክብር የሚባል ነገር በውስጡ አልተፈጠረም።እኔን የሚያክል ልጅ ወልዶ ሲያበቃ ከአንደበቱ የሚወጣው ነውር አስደንጋጭ ነው።በሽምግልናው ወቅት እንኳ ራሱን መግራት ባለመቻሉ እርሱን ብቻ የሚያውቅ ሰው በትግሬዎች ላይ ብርቱ ጥላቻን ያሳድራል።እርሱን የመሰሉ ብዙ የትግሬዎችን መልክ የሚያጠፉ ከንቱ ግለሰቦች ሞልተዋል።እኔ ተወልጄ በኖርኩበት አካባቢ ትግሬዎች የሚገለጹት በታማኝነታቸው፤በታታሪነታቸው፤በየዋህነታቸው እና በግልፍተኝነታቸው እንጂ በጨካኝነት፤በስግብግብነት ፤በሌብነት እና ጥላቻን በመዝራት አልነበረም።አሁን የቢሮየን ተጋሪ የመሰሉ ህወቶች ያስተዋወቁን ትግሬዎች እኛ ድሮ የምናውቃቸውን አይደለም።ከህወሃቶች በፊት እኛ የምናውቃቸው ጥሩ የሚባሉ ትግሬዎች አሁን የት እንዳሉም አላውቅም።ምናልባት ህወሃት ልጇን ትበላለች እያሉ እነዚህ ክፉዎቹ በልተው ሳይጨርሷቸው አይቀርም።አሁን ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ትግሬዎች ሳይሆኑ እኛ የማናውቃቸው ፍጹም ጨካኝ ባዕዳኖች ናቸው።ደጋፊዎቻቸውም “ሁለት እግሮች ሁሉ መጥፎ፤ አራት እግሮች ሁሉ ጥሩ” ብለው የሚያላዝኑ በጎችን የሚመስሉ ናቸው።

ይህ የቢሮየ ተጋሪ አንዳንዴ ስዩምን ደደብ አህያ እያለ ይሳደባል። መለስን ደግሞ ጀግና እያለ ያሞካሻል። እንደፈለገ ቢል እኔ ግን ምንም አስተያየት አልሰጥም። እኔ ዝም የምለው እርሱ ወሬ ከእኔ ቀድቶ ለሌሎች ያስተላልፋል ብየ ሳይሆን ተፈጥሮየ ስለሆነ ነው። እንደ ህወሃት አባላት የሰውን ስም እያነሱ የማማት ተግባር ውስጥ መሳተፍ ስለማይመቸኝ ዝም ማለትን እመርጣለሁ።
ይቀጥላል…