በኃይሉ ሻውልና በመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ቀጥሏል

በኃይሌ ሙሉ | ሪፖርተር

አቶ ያዕቆብ ልኬ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል መመረጣቸውን ተከትሎ፣ በመኢአድ ሥራ አስፈጻሚና በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በኢንጅነሩና በሥራ አስፈጻሚው መካከል ውዝግቡ የተፈጠረው ታኅሣሥ 19 ቀን 2003 ዓ.ም. በተካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ኢንጅነር ኃይሉ ከሕገ ደንብ ውጪ፣ የፓርቲውን ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በራሳቸው ሥልጣን መርጠዋል በሚል ሥራ አስፈጻሚው ተቃውሞውን መግለጽ ማሰማት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡

የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ማሙሸት አማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፓርቲው ሕገ ደንብ ተቀዳሚው ምክትል ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበርና ዋና ጸሐፊ በሥራ አስፈጻሚው አባላት ተመርጠው ለጠቅላላ ጉባዔ ከቀረበ በኋላ የሚፀድቅ ቢሆንም፣ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ይህንን ሕገ ደንብ ጥሰው ራሳቸው የፈለጉትን ሰው ምክትል ተቀዳሚ ሊቀመንበር አድርገው ሹመዋል፡፡

ታኅሣሥ 19 ቀን 2003 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ማግስት ሕገ ደንብ ተጥሷል ያሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላት በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲደረግ ቢጠይቁም፣ ኢንጅነር ኃይሉ ታመዋል በሚል ውይይቱ ሳይካሄድ መቅረቱን የጠቆሙት አቶ ማሙሸት፣ ከአምስት ቀናት በኋላ ኢንጅነር ኃይሉ የተገኙበት ውይይት ተካሂዶ ችግሩን የሚያጣራና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቢደረግም፣ እስካሁን ድረስ የኮሚቴው ሪፖርት እንዲቀርብ አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ችግሩን በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የቅዳሜው ውይይት በተደረገ በማግስቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ያዕቆብ ልኬ፣ ፖሊስ ይዘው በመምጣት በየሳምንቱ እሑድ የመኢአድ ወጣት አባላት በአገራዊ ጉዳይ የሚያደርጉትን ውይይት ሕገወጥ ነው በማለት ለመበተን ሙከራ አድርገዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ኢንጅነር ኃይሉ ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ በፓርቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የመኢአድ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሌላ ደብዳቤ እስከሚገለጽ ድረስ ማንኛውም ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አስታውቃለሁ፤›› ይላል ደብዳቤው፡፡

የደብዳቤው ግልባጭ ለሕግና ሥርዓት ኮሚቴ እንዲሁም ለፋይናንስ ኮሚቴ ተልኳል፡፡ ከደብዳቤው ወረድ ብሎ በእጅ በተጻፈ ጽሑፍም የጥበቃ ኃላፊውና የሁሉም ጉዳይ አሠራርና ጥበቃ ኃላፊ ውሳኔውን እንዲያውቁት የተደረገ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አቶ ማሙሸት እንደሚሉት ከሆነ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ፊርማ የወጣው የራስጌ መግለጫ የሌለው ደብዳቤ ሕገወጥ ማህተም ያረፈበት በመሆኑ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድና ለፖሊስ አስታውቋል፡፡

‹‹አንድ ፓርቲ የመቋቋሚያ ሰርተፍኬቱን ይዞ ካልሄደ በስተቀር ሌላ ማህተም ማሠራት አይችልም፤›› ያሉት አቶ ማሙሸት፣ ትክክለኛው የፓርቲው ማህተም እርሳቸው ቢሮ ያለ መሆኑን፣ ኢንጅነር ኃይሉ የፈረሙበት ደብዳቤ ላይ ያረፈው ማህተም ግን በሕገወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ማሙሸት እንደሚሉት፣ በደብዳቤው ላይ ግልባጭ የተደረገላቸው የሕግና ሥርዓት ኮሚቴና የፋይናንስና አስተዳደር ኮሚቴ የሚባሉ ኮሚቴዎች በፓርቲው ውስጥ የሌሉ ሲሆን፣ የጥበቃ ክፍል ኃላፊ ናቸው በሚል እንዲያውቁት የተባሉት ግለሰብ የፓርቲው አባል ያልሆኑ የማይታወቁ ሰው ናቸው፡፡ የሁሉ ጉዳይ አሠራርና ጥበቃ ኃላፊ ተብለው የተገለጹትም ተላላኪ መሆናቸውን አቶ ማሙሸት ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ ልኬ በበኩላቸው፣ የፓርቲው የውስጥ ችግር በፓርቲው ውስጥ መፍትሔ የሚያገኝ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የመኢአድ ዋና ጸሐፊ አቶ ማሙሸት አማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፓርቲው አሥራ ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል አሥራ አምስቱ የኢንጅነር ኃይሉን ሕገ ደንብ የጣሰ ውሳኔ የሚቃወሙ ናቸው፡፡