ትችትና፡ ትዝብት፡ ሳቅና ቁምነገር: ታሪክና ተረት፡ ተማሪ ተክሌ፡ ኦታዋ፡ ካናዳ

1- ይሄ ጽሁፍ የተጻፈው ለለስላሳ አስተያየት እንጂ ለመረረ ውይይት አይደለምና፡ ጊዜው የመዝናናት አይደለም የምትሉ ይሄንን ጽሁፍ በማንበብ ግዜያችሁን አትግደሉ።

2- “ግለሰቡን መደብደብ ትተን፡ ምናለ ሀሳቡን ብቻ ብንተች፡” ይላል አንዱ የሰለጠነ ተቺ። ሌላኛው የሰለጠነ ተሳዳቢ ደግሞ “ድስት አጣቢ” ሲል ይሳደባል። አንዱ “አሁን ምናለ ይሄንን ሁሉ አተታ ለማተት ግዜ ባታጠፋ” ብሎ ሲል፡ “ይሄ ወቅቱን የጠበቀና ለብርቱካን መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው” ይላል ሌላኛው። የሚያስጨበጭቡም የሚያስደበድቡም ጽሁፎች መጻፍ ችሎታ ይጠይቃል ባልልም፡ አንዳንዴ ትችትን ተቋቁሞ መጻፍ ድፍረትንና መቻልን ይጠይቃል። እንደልጅነቴ ቢሆን፡ ሰዎች ሲተቹኝ ወይንም አቋሜን ሲጠራጠሩ ስቅስቅ ብዬ አለቅስ ነበር። አንድ ዘንቢል ማበሻም እንባዬን ለማድረቅ አይበቃኝ። በጊዜ ሂደት ግን ትችትን ለመድኩት። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በትንሹ እስኪገባኝ አመታት ፈጅተውብኛል። አመታት ብቻ አይደለም፡ አራት አገራት፡ ሁለት አህጉራት፡ ብዙ አመታት ማቋረጥና ከዚህ መድረስ ነበረብኝ። ሀሳብን በነጻነት የገለጽ መብትን መረዳት ማለት በተራ አገላለጽ “ሙልጭ ተደርጎ ለመሰደብም መዘጋጀት” ማለት ነው። አንዳንዴ ቢመረኝም፡ ዝግጁ ነኝ።

3- አንዳንድ ሰው ሀሳቡን ሳይሳደብ መግለጽ ይችላል። አንዳንዱ ደግሞ የሰለጠነ ተቺ ነው፤ በሰለጠነ ቋንቋ በትህትና ያስቀምጣል። ብታምኑም ባታምኑም ብዙ ጊዜ በምጽፋቸው ጽሁፎች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶች በደንብ እወዳቸዋለሁ። ስድቦቹንም ጭምር። እንደውም አሁን አሁን የሚሳደቡ ሲያንሱ፡ እንዳልጻፍኩ ይሰማኝ ጀምሯል። ስለዚህ ጽሁፎቼን ተከታትላችሁ ከሆነ፡ በደንብ አስተያየት ካልተሰጠባቸውና ስድብ ካልወረደብኝ፡ በቀጣዮቹ ጽሁፎቼ ላይ ስድብ የሚቀሰቅሱ አንቀጾችን እመርቅባቸዋለሁ። አንዳንዶቹ የሰዎች አስተያየቶች ለብቻዬ ያስቁኛል። በጣም ጥቂቶቹ ያሳቅቁኛል። መጨረሻ ላይ እንደምገልጸው አንገቴን ያስደፉኛል። ከማልቀስ ግን መሳቅ ይሻላልና፡ እስኪ ለሳቅ ለፈገግታ አንድ ሁለቱን ተቺዎች እንመልከት።

4- “ድስት አጣቢ” ካለው ተቺ ልጀምር። ይሄ ተቺ የቅርብ ሰው መሆን አለበት። ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ያውቃል ስለኔ። አንድም ወለል እንዳጠብኩ፤ አለዚያም ቢያንስ እቃ ማጠብ እንደምወድ ያውቃል ማለት ነው። በ2005 ከኬንያ ወደ ቫንኩቨር ስመጣ እሻል እንደሆነ እንጂ፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ስመጣ ማብሰል የሚባል ነገር አላውቅም ነበር። እንደ ኦሮሚያ አቆጣጠር፡ ከ1977 እስከ 1990 ቤተሰቦቼ፡ ከ1991 እስከ 1997 የቅዱስ ጊዮርጊስና አካባቢው አድባራት ደጀሰላማት፡ ከ1997 እስከ 2001 የአ.አ.ዩ. ምግብ ቤት ማብሰል እንድችል አላበረታቱኝም። መቼም ሳይደግስ አይጣላም፡ ይሄንን ድክመቴን በሁለት ነገር አካካሰልኝ። አንደኛ፡ የናት ያባቴ አምላክ ጥሎ አልጣለኝም፡ በሄድኩበት ሁሉ አብሳይ ይሰጠኛል። ጓደኞቼ ይወዱኛል። የሚወዱኝ ማለቴ ነው። እኔን መውደድ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የሚወዱኝ ሲወዱኝ አጥብቀው ነው። የሚጠሉኝም ሲጠሉኝ እጅግ በጣም አምርረው ነው። የሚወዱኝ፡ ድክመቴን ያውቃሉ። ሌላው ቢቀር ማብሰል እንደማልችል፡ የበሰለውን ግን አጣጥሜ እንደምበላ ያውቃሉ። ጥንካሬዬንም ያውቃሉ። ጥንካሬየም ሁለተኛው ማካካሻዬ ነው፡ እቃ ማጠብ እወዳለሁ።

5- ጓደኛዬ አትክልት፡ ያበስላል። ክትፎ በማሽን አስፈጭታ የምትሰራ ሴት አይወድም። ክትፎ ሲሰራ ከትፎ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን አንድ ግዜ ቫንኩቨር መጡና፡ ክትፎ ተጋበዙ አሉ። “እህ ይሄማ ክትፎ አይደለም፡” አሉ። “ክትፎ፡ የተከተፈ ነው። የተፈጨ አይደለም።” ስለዚህ ከተፈጨ ክትፎ ሳይሆን ፍጭቶ ነው። አትክልት ክትፎ ሲያበላን ከትፎ ነው። እኔ ደግሞ እቃ አጥባለሁ። አናዳንድ ግዜ እሱ ቤት እንደምመጣ ካወቀ፡ ይሄ ባለክትፎ ጓደኛየ የጎረቤት ሁሉ እቃ ሰብስቦ ነው የሚጠብቀኝ። እንዳጥብለት። ለነገሩ የሚያበላኝ ክትፎ የሱን ቤት በማጠብ ብቻ ሊካካስ አይችልም። አንዱ እንግዲህ ይሄን የሚያውቅ ሰው ነው”ብርቱካንን እባክሽ ዝም አትበይ፡ አለሁ በይን እንጂ፡ ድምጽሽን እንስማ ባልኩ” ድስት አጣቢ ያለኝ። እኔ ግን እቃ አጣቢ እንጂ ድስት አጣቢ አልነበርኩም። በእቃ አጣቢና በድስት አጣቢ መካከል ምን ልዩነት አለ? ነገሩ እንደተመልካቹ ነው። አንዱ ድስት አጣቢ ነው፡ አንዱ እቃ አጣቢ።

6- ሌላው እንግዲህ ይሄ ሰው “ድስት አጣቢ” ሊለኝ የሚችለው ካናዳ ስገባ የመጀመሪያው ስራዬ ወለል ማጠብ እንደነበር ስለሚያውቅ መሆን አለበት። መቼም የዛሬ ግዜ ሰው ምስጢር አይደብቅ። የመጀመሪያው ስራዬ ጽዳት ነበር። ስምንት ብር ከሰማኒያ ሳንቲም። ሌላ ሰው ቢሆን ዘጠኝ ብር ብሎ ነው የሚነግራችሁ። ወደ አስርም እያጠጋጋ የሚናገር አይጠፋም። እኔ ግን ለ20 ሳንቲም ስል አልዋሽም። ከዋሸሁም ወደታች ብዋሽ ይሻለኛል። ወደላይ ከምዋሽ። የሆነ ሆኖ፡ ካናዳ እንደገባሁ፡ ስራቸውን ባልነገሩኝ ጓደኞቼ በቅርብ የተገኘልኝ ስራ፡ ጽዳት ነበር። አንድ ሁለት ወር አጸዳሁ። ወደጥበቃ እስካድግ። ወደዘበኝነት።

7- ያኔ አብረውኝ ይሰሩት የነበሩትን ህንዶችን አልወዳቸውም። ያኔ ስሜን “ማይክ” ነው ያልኳቸው። ተክለ-ሚካኤል የሚለው ስም ሲያጥር ማይክ ሆነ። በኋላ በተለምዶ ማይክ የሚባሉ አበሻ ሰዎች ቆንጆዎችና መልካቸው ወደፈረንጅ የቀረቡ፡ አሪፎች፡ አራዶች ሰለመሰሉኝና እኔ ደግሞ አሪፍም ቆንጆም ስላልሆንኩ ራሴ “ማይክ” አልመስልህ አለኝና ተውኩት። እስከዚያው ግን “ማይክ” ይሄንን አድርግ፡ ማይክ ይሄንን ውሰድ ይሄንን መልስ እያሉ ሰላሳ ድስት ፎቅ ያሳጥቡኛል። ስኮት ይባላል ተክቼው እሰራ የነበረው ሰው ስም። እሱ የነገረኝና እነሱ የሚያሰሩኝ ተለያየብኝ። ስለዚህ ከህንዶች ጋር በዋልኩ ቁጥር እነዚያ ሴቶች ይመጡብኛል። እነሱ 16ኛው ፎቅ ላይ ቁጭ ብለው እኔን የሰላሳ ስድስት ፎቅ ወለል ማስወልወል ብቻ ሳይሆን፡ ጋርቤጅ ያስደፉኛል። ይድፋቸውና። ግን ለምን ይድፋቸው? በጎ ባይሰሩም ምሬያቸዋለሁ። ምህረት ጥሩ ነው።

8- ቀን ሲያልፍ ጠላትንም ቢሆን መማር ነው። እነጂ፡ አሁን ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ እስር ቤት ቢማቅቅ፡ ፍስሀ ደስታ ቢሰቀል፡ ተስፋዬ ወልደስላሴ አፈር ቢበላ፡ ከሰላሳ አመት በፊት ልጇን ያጣች እናት ምን ትጠቀማለች? ይቅር ባይነት ቆንጆ ነው። ሕወሀት ኢህአዴግንም ለመማር የተዘጋጀን መሆን አለብን። አንዳንድ ግዜ ሕወሀት/ኢህአዴግን ያበረታው “እነዚህ ሰዎች ቢይዙን አይምሩንም” የሚለው ፍራቻ ይመስለኛል። እንጂ ብናገኛቸው እንደምንምራቸው ከጠቆምን ትንሽ ሊያዳክማቸው ይችላል። ቢአንስ የተወሰኑትን።

9- ለነገሩ የዚህ የምሀረት ጉዳይ አንደኛውን ይሄ ስርአት አልፎ የተሻለ ስርአት ሲመጣ ቢደረግ ይሻልል። ምክንያቱም ባለፈው ሰሞን ይሄ የደርግ ባለስልጣናትን የምህረት ጥያቄ ጉዳይ ስንወያይ አንዱ ወዳጄ፡ አንዲት የሰባ አመት እናት፡ ልጃቸው በደርግ ግዜ ተገድሏል። የልጅ ልጃቸው ደግሞ በምርጫ 97 ተገድሎባቸዋል። ሁሉም መንግስታት ደም ተቃብተዋቸዋል። ስለዚህ አዲስ ስርአት በመጣ ቁጥር የምህረት አዋጅ ስናውጅ ከምንኖር፡ አንደኛውን የነዚህኞቹንም እንድንገላገል፡ የተሻለ የምህረት መንግስት እስኪመጣ መጠበቁ ይሻላል። ያ ቀን ደግሞ በቱኒዚያ ከለካነው ሶስት አመት ነው የቀረው።

10- ”ድስት አጣቢ” ከሚለው አስተያየት ቀጥሎ ከአስተያየቶች ሁሉ “ናይሮቢ ስትገባ እንጀራ ያበላህን ድርጅት አላውቀውም ያልክ” ከሀዲ የሚለው ድርጅታዊ አስተያየት ከምንም በላይ ነክቶኛል። ገብሬ ገብሩና ደምሴ ደሜ ምስክሮቼ ናቸው፡ ሌላም ምስክሮች መቁጠር እችላለሁ፡ ድግስና ክስ አልረሳም። ያበላኝንና ያጠጣኝን ሁሌም አመሰግነዋለሁ። ከኔ ሕይወት ግማሹ ምናልባትም ከግማሽ በላይ በድግስ የቆመ ነው። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፡ ከ1983 ዩኒቨርስቲ እስክገባ እስከ 1990 ድረስ ከደብረ ልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እስከ ወዮ መድሀኔዓለም፡ ከቀርሳ ኢላላ እግዚአብሄር አብ እስከ ሼዴማ ተክለሀይማኖት፡ ከሶጊዶ ማሪያም፡ እስከ አቦ ጎዶ የበላሁትን ድግስ ብረሳ፡ ቀኜ ይርሳኝ። ረሀብ ይፍጀኝ። ስድስት ኪሎ ገብቼም፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በነጻ፡ ለአራት አመት ሩብ ጉዳይ ያበላኝ ፓስታና ሽሮ፡ ስጋና ዳቦ፡ የምረሳው አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ከቤተሰቦቼም በላይ መግቦኛል። ተንከባክቦኛል።

11- ቤተሰቦቼ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኛን ልጆቻቸውን ለማስደሰት ያላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም፡ በአቅም ውሱንነት የተነሳ በቤታችን በወር በአማካይ አንድ ግዜ ቢበዛም ሁለት ግዜ ነው ስጋ የምንበላው። እሱም በኣልን ታኮ ስለሚመጣ፡ አንዳንድ በኣል የሌላቸው ወራት ያለስጋና ያለቅቤ ሊያልፉ ይችላሉ። የኛ ቤት የምግብ ስነ ስርአት ደግሞ ራሱን የቻለ ጽሁፍ ይወጣዋልና በሌላ ግዜ እመለስበታለሁ እንጂ ለመንደላቅና ለቅንጦት የሚመች አልነበረም። የሆነ ሆኖ ግን፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የድግስ ያህል ደግሶ፡ በሳምንት ሶስት አራት ቀን ስጋ፡ ወፍራም ሸሮ፡ ፓስታ፡ አብልቶኛል። ስለዚህ ቢያንስ ከእድሜዬ አንድ ሶስተኛውን በድግስ የቆምኩ ሰው፡ ያበሉኝን፡ የረዱኝን አልረሳም።

12- ወደ ናይሮቢ ልውሰዳችሁ። አቶ ቶልቻ ይባላል። እንዴት ያለ የኢህአፓ ሰው ነው። ያኔ አለም ድፍት ብሎብን እንደ ህጻን ስቅስቅ ብለን ስናለቅስ የተቀበለንና በመኪናው ያንሸራሸረን፤ ሌላው ሁሉ ቢቀር፡ ለመጀመሪያ ግዜ ቺፕስ ያበላኝ ሰው ቶልቻ ነበር። ናይሮቢ። ያኔ “ከቻፕ” ብርቃችን ከመሆኑ የተነሳ እንደ ሙቅ ድስት ነበር የላስኩት። ይጥማል። ከቻፕ ያበላኝን አልረሳሁትም እንኩዋን እንጀራ ያበላኝን። ኢህአፓዎች ከዚህ ቀደም በቪኦኤ ላይ ከበኩር ወጣታቸው ጋር ስንከራከር በንግግሬ አልተደሰቱም መሰለኝ አቂመው ወረፍ ያደርጉኛል። ለመጀመሪያ ግዜ ከቻፕ ያበላኝን ኢህአፓን ግን አልረሳውም። ምን ያህል ወርጄ እንደማስታውስ ለመግለጽ እንጂ፡ የኢህአፓ ሰዎች ያበሉን ቺፕስና ከቻፕ ብቻ አይደለም። ከጠቀማቸውና ካጽናናቸው ያበሉኝን ሁሉ ወደፊት ልዘረዝረው እችላለሁ። መቼም ይሄ ጽሁፍ ከላይ እንደገለጽኩት ለመረረ ውይይት አይደለምና ካካባቢዬም ይሁን ባካባቢዬ ከማይገኙ አገር ወደድ ኢህአፓ ወዳጆቼ ግልምጫ አይጋብዝብኝም።

13- ከናይሮቢ ቀጥሎ፡ በፈረንጅም ባበሻም ድግስ አምስት አመት ያቆየኝ የቫንኩቨርና የቪክቶሪያ አድባራት ናቸው። ቫንኩቨር በሰበብ አስባቡ ድግስ ከተደገሰ፡ ሰዉ እስኪወጣ እኔ ከዚያ ድግስ ቤት አልወጣም። በልቼ ብቻ አይደለም የምሄደው፡ የተረፈውን ጭኜ እሄዳለሁ። አልኮራም። ጥርግ አድርጌ እበላለሁ፡ ጥርግ አድርጌ እወጣለሁ። በዚህ በኩል እንዳባቴ ነኝ። ሀምሳ አለቃ አበበ ሳህለማሪያም። ሀምሳ አለቃ ሆኖ ይቅር እንጂ አገሩን ሰላሳ ሁለት አመት አገልግሏል። ምን አገሩን ብቻ፡ ዓለምንም እንጂ። ኮንጎ ዘምቷል፡ በ54 ዐ.ም። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ አባቶቻችሁ ኮንጉና ኮርያ የዘመቱ ስንት ሰዎች አላችሁ? በጣት የምንቆጠር ነን። ብርቅዬ ዜጎች ነን። እና አባቴ፡ ሰርግ ቤት፡ ለቅሶ ቤት፡ ክርስታና ቤት፡ ተዝካር ቤት፡ ምግብ ቤት፡ ሲሄድ፡ በልኩ ያነሳል። ያነሳውንም ጥርግ አድርጎ ይበላል። የኛ ቤት ሰዎች የምንበላበት ሰሀን ድጋሜ መታጠብ አያስፈልገውም። ስለዚህ የበላሁበትንና ያጠብኩትን ሰሀን አልረሳም። ያለበለዚያማ ወጭት ሰባሪ ነኝ።

14- ቤተክርስቲያን ለምን እንደምሄድ ታውቃላችሁ? ለምንስ እንደማልሄድ? ምክንያቶቼ ብዙ ናቸው። አንደኛው ምክንያቴ ግን ድግስ ነው። የአልማዝን እንጀራ፡ የስንታየሁን ቀይ ወጥ፡ የጂጂን ዱለት፡ የእንቶኔን ክትፎ፡ … ወይኔ ስንቱ ቀረ? በድግስ እንኩዋን ቫንኩቨርን የሚተካከል አላገኘሁም። ሲያትልም ሲነገርለት እሰማለሁ። አጋጥሞኝ ግን አያውቅም። ኦታዋ፡ ምናልባት በወንዝና በድርጅት ተወስኖ ይሆናል፡ ወይንም በሌላ ምክንያት፤ ብቻ በረዶውም አንቀሳቅሶኝ በደንብ ተዟዙሬ አላየሁትም፡ የቫንኩቨርን ያህል የሚሆን አይመስለኝም። ኦታዋ ድግስ ቢኖርም፡ “ግባ” የሚል አናሳ ነው። ከዚህ በላይ ከጻፍኩ ደግሞ ሌላ የትችትና የስድብ መቅሰፍት በራሴ ላይ መጋበዜ ነውና ይቅርብኝ። ዛሬ ግዜ የኮንጎና የኮሪያ ዘማች ቤተሰቦችን የሚያከብር ሰው የለም፤ እሱን እንኩዋን ተገን አድርጌ አልጽፍ ነገር።

15- ይሄንን ሁሉ መቀባጠር ምን ጫረው? ትቸት። “ብርቱካን ሚደቀሳ ከተፈታች ሶስት ወር ሆናት። ብርቱካን ሚደቅሳን እንደዋዛ ልናጣት አይገባም። ስለዚህ ቀስ በቀስ ከእጃችን ሳትወጣና ነገሮች ሳይበለሻሹም በፊት ወደ ፖለቲካ ብትመለስ መልካም ነው” ለሚል መልካም ጽሁፍ የተሰጡ አስተያየቶች ብዙ ናቸው። አስተያየቶቹን በሙሉ እቀበላለሁ ባልልም፡ አብዛኞቹን አስማማባቸዋለሁ። ጽሁፍ ግን በጣም ተቃራኒና ተጻራሪ ትችቶችን ካልጋበዘ ጽሁፍ አይደለም ለኔ። ስብከት ነው። ቅስቀሳ። ለምሳሌ “ግንቦት ሰባት ኢህአዴግን ይዘርረዋል” ብዬ ብጽፍ ቅስቀሳ ነው። ከመቶ ተመልካች፡ አስሩም አያነበውም። ቢያነቡትም አብዛኛዎቹ የኔ ቢጤ ቀንደኛ የግንቦት ሰባት ደጋፊዎች ናቸው። “ግንቦት ሰባትም እንደ ሌሎች ድርጅቶች አርባ አራት አመት አንድ አመራር ስልጣን ላይ አያስቀምጥም። እኛንም እድል ይስጠን” ብል ግን ሰላሳ አርባ ሰው ያነባል፤ ይተቻልም ብዬ አምናለሁ።

16- ብዙ ግዜ በኔም በሌሎች ሰዎችም ጽሁፎች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶች ሳይ፡ ሁለት አስተያየቶች ብቻ ናቸው እንዳይነሱብኝ የምፈልጋቸው፤ ወይንም ሲነሱ የሚያሙኝ። ወይም ሰው ወደፊት ባየነሳ የምማጠነው። አንደኛው አንተ እዚያ ካናዳ ቁጭ ብለህ ፈርጥጠህ፡ የሄድክ ፈርጣጭ፡ አንተ ፈርተህ ሌላውን እንዲሞት ትቀሰቅሳለህ፡ የሚለውና አንተ ምን አደረግክ የሚለው። ምክንያቱም እነዚህ ጥያቄዎች ቀድሞውንም ውስጤ ስላሉ ልክ ሌላ ሰው ሲያነሳብኝ ያመኛል። ያቃጥለኛል። ሰለዚሀ፡ አስተያየት የምትሰጡ ሰዎች ሁሉ፡ ሁሉንም ነገር በሉኝ። እንደዚያ ብቻ አትበሉኝ። እባካችሁ ልበልበት። ላውራበት። ልቀባጥርበት። ልተንፍስ። መሰደዴ የምኮራበት ነገር አይደለም። ስደት ያሳንሳል። ከኛ ከሚያንሱትም ያሳንሳል። ለዚህ ነው ብዙ ግዜ አገር ቤት ያሉ ፖለቲከኞችን ምን ጥፋት ቢሰሩ ለመተቸት የማፍረው።

17- ብርቱካንንም ስለሳሳሁላት፡ የሷ ከፖለቲካ ውጭ መሆን ምን ያህል እንደሚጎድልብን ለመግለጽ፡ እንጂ በምንም መልኩ ከፖለቲካ ብትርቅ እንኩዋን፡ ውሳኔዋን ተመርኩዤ ልተቻት አይደለም። ደግሞምኮ ነገሩን በደንብ ካጤነው፡ ላለፉት ብዙ አመታት ይህቺን አገር በተለያየ መልኩ በሙያቸውና በላባቸው ያገለገሉትና እድሜያቸው ወደሰባዎቹና ሰማኒያዎቹ የገሰገሰው፡ የዚያኛው ትውልድ አመራር አባላት፡ እነ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ፡ እነ አቶ ግዛቸው ሽፈራው፡ እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፡ እነ አቶ እንቶኔ ምንትሴና ከሙሉ ክብር ጋር ጡረታ ሰጥታ፡ ቢያጠፋም የሚያምርበት፡ ቢሳሳትም የማይገንበት፡ ቢፎክርም የሚመስልበት፡ ወጣትና ቀልጣፋ፡ አመራር ይዛ ካልተጓዘች፡ እንግዲህ ምን የተሻለ መፍትሄ አለን? የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፡ ብርቱካን ብዙዎቻችን መሆን የማንችለውን ሆናለች። ከዚህ በኋላ ስለሰላማዊ ትግል ካወራን፡ በተለያየ ምክንያት ተስፋ የጣልንባቸው ወንድም ልደቱና አባት ሀይሉ ሻውል የብዙሀኑን ህዝብ ድጋፍ አጥተዋል። በተወሰነ መልኩም ቢሆን የማናውቀው ተሰወረ ነገር ከሌለ በስተቀር፡ እንግዲህ በተለያየ ታሪካዊ ቁርሾ፡ በግራ ዘመም ፖለቲካ በሽታ፡ በግልም በጋራም ጉዳይ የተባሉትን አንጋፋና አረጋዊ ፖለቲከኞች በአማካሪነት ወደጎን አድርጋ፡ ሶስት መቶ ወጣት ጎበዛዝት ይዝ ልትመራ የተሻለ እድል ያላት ብርቱካን ነች። ለዚህ ነው ብርቱካንን ምርር አድርጌ የያዝኳት።

18- ከዚአ በተረፈ ግን፡ ሲጋራ አጨሳለሁና፡ ሌላው እንዳያጨስ መምከር አልችልም ማለት አይደለም። ወይንም መጠጥ ስጋት (“ጋ” ይጥብቃል) የማድር ሰካራም ብሆን፡ ሌላውን አትስከር ልል አይቻለኝም ማለትም አይደለም። መሰደዴ፡ መሸሼ ሁሌም የማፍርበት፡ የማልኮራበት ነገር ቢሆንም፡ እኔ ፈራሁ፡ ሸሸሁና ሌሎችን በርቱ ማለት አልችልም ማለት ነው? ካለሁበትስ ቦታ ሆኜ የምችለውን የሃሳብ የሞራል አስተዋጽኦ ማድረግ የለብኝም ማለት ነው? አለብን። ሌላውን ሁሉ ማድረግ ባልችል፡ ቢያንስ እጽፋለሁ። አንባቢና ተቺ እስካለ እጽፋለሁ። መጻፍ የማቆመው ተቺ ሲጠፋ ነው። ስለተቻችሁኝ አመሰግናለሁ። ይመቻችሁ። ተቺን ያኑርልኝ። ባልተች አልጽፍም። ተቺ ካገኘሁ፡ በሚቀጥለው ደግሞ ስለጥበቃ ስራየና እንዴት ህይወቴን እንደናደው ወይም እንዳነጸው አትትላችኋለሁ።

ተማሪ ተክሌ፡ ኦታዋ፡ ካናዳ፡ ጥር 2011