ደራሲ ማሞ ውድነህ በጠና ታመዋል

(ሪፖርተር) — ታዋቂውና አንጋፋው ደራሲ አቶ ማሞ ውድነህ ጤንነታቸው ታውኮ አልጋ ከያዙ አንድ ወር ሆኗቸዋል፡፡ በቅድሚያ ዳግማዊ ምኒልክ ቀጥሎም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ሕክምና ቢከታተሉም ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ኢንተርናሽል የልብና ልብ ነክ ደዌዎች ሆስፒታል ከገቡ ሦስት ቀኖች አስቆጥረዋል፡፡

ሔኖክ ያሬድ በተኙበት ሆስፒታል ትናትና አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕመምዎ ምንድን ነው?

አቶ ማሞ፡- ሕመሜ ከልብ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ቀደም ብዬ በውጭም ታክሜያለሁ፡፡ እግሬ እብጠት አሳይቷል፤ ሰውነቴ ውኃ ቋጥሯል፤ ሐኪሞች እርሱን ለማስወጣት ትንሽ ጊዜ ይጠይቀናል ብለዋል፡፡ ስኳሩም ሳስታምመው 24 ዓመት ሆኗል፡፡ የደም ዙረቱም ችግር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምናዎ ሒደት ምን ይመስላል?

አቶ ማሞ፡- መጀመርያ የታከምሁት ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ነው፡፡ የእግሬን ቁስል አዩና የሚችሉትን አደረጉና ወደ ጥቁር አንበሳ በሪፈራል ሄድኩ፡፡ ጥቁር አንበሳ በስንት መከራ ነው አልጋ ያገኘሁት፡፡ የመጀመርያው ቀን ድንገተኛ ክፍል ወደቅሁ፤ መከራዬን አየሁ፤ ያን ቀን ለመሞት ተመኝቼ ነበር፤ ሲዖል ነበር፡፡ በማግሥቱ ሁለተኛ ማዕረግ አልጋ ተገኝቶ ሜዲካል ገባሁ፤ የተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፤ ከ5ኛ ፎቅ ወደ 8ኛ ፎቅ ወሰዱኝ፤ ብዙ ምርመራ በያይነቱ ተካሔዶ ውጤቱ ደህና ነው፤ ያለው ችግር ቀስ በቀስ ይወጣል አሉኝ፤ ይሁን እንጂ አራት ቀን ተሰቃየሁና ትናንት ዲስቻርጅ አድርጉኝ አልኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያትዎ ምንድን ነው?

አቶ ማሞ፡- ሐኪሞቹ ራሳቸው ጉድለቱ ከእኛ ነው ወይ ብለው ጠይቀውኛል፡፡ በእኛ ደንብ መሠረት ከሆስፒታሉ የሚወጡበትን ምክንያት ጻፍ አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ጻፉ?

አቶ ማሞ፡- ያ ክፍል ለእኔ እስር ቤት ነበር፡፡ አልጋው ላይ እንደዚህ መተኛት አይቻልም፡፡ የረገበ ሽቦ ነው፤ ከሆስፒታሉ ጋራ አብሮ የተሠራ ይመስላል፡፡ ለመነሣትም፣ ለመተኛትም ሰው ያስፈልጋል፡፡ ክፍሉ 1ኛ ማዕረግ ተባለ እንጂ ውኃም መብራትም የለውም፡፡ ጭልጭል የምትል የራስጌ መብራት አለው፡፡ በረሮ ስገል ነው የምውለው፡፡ ምግብ ሲሸታቸው ይወጣሉ፡፡ ረጨን ብለውን ነበር፤ ተላምደውታል መሰለኝ፡፡ ውኃ በባልዲ እየተቀዳ ወደ በሽተኛ የሚገባበት ነውና ወጣሁ፡፡ እዚህ ሰው የሚተኛበት አልጋ አገኘሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ምርመራቸውን ፈልጌ ነበር ውጤቱን አልሰጡኝም፤ እዚህ እንደገና ልመረመር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነፃ ሕክምና ጤና ጥበቃ አልሰጠዎትም?

አቶ ማሞ፡- ለማን? ለእኔ? የት ያውቀኛል? ሚኒስትሩ አያውቁኝ፡፡ ልጆቼን ውሎ ያግባ እስከዛሬ ያለው ደህና ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን አላውቀውም፤ ከበድ እያለ ይሄዳል፡፡

የደራስያን ማኅበር ተጠርተው ሥራ አስፈጻሚዎቹ መጥተው ችግርህ ምንድን ነው? አሉኝ፡፡ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሕክምና በነፃ እንድታገኝ እንጽፋለን ብለው ሔዱ፡፡ ይጻፉ አይጻፉ አላውቅም፡፡

አቶ ጌታቸው በለጠ ባህል ሚኒስትሮችን ጠይቋቸው ነበር፡፡ ‹‹እኛ ለእርሳቸው ዕርዳታ እናደርጋለን›› ብለዋል የሚል ነገር ሰምቼ ነበር፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ዕርዳታ አልፈልግም፤ ከእንግዲህ ባለው ይከብደኝ እንደሆነ አላውቅም፡፡

ለባህል ነገር አስተዋጽዖ ላደረጉ ሰዎች ባህል ሚኒስቴር ምንድን ነው ሥራው? የማይገባኝ ይኸ ነው፡፡ ስፖርት ብቻ ነው ወይ የሚሯሯጠው፣ የሰውና የአገር ትልቅ ንብረት ዕውቀት ነው፡፡ ደራሲዎችና ሠዓሊዎች ዕውቀት አመንጪዎችና ፈንጣቂዎች ናቸው፡፡ እዚህ አገር እነርሱን የሚንከባከበው ማን ነው? እስኪ ንገረኝ? በሥራዎቻችን ተጠቃሚው ሕዝብ ነው እኮ፡፡ ሕዝብ በዕውቀት እንዲበለጽግ ማድረግ ያለበት ማነው? ያንን ዕውቀት የሚያመነጩ ሰዎችን መጠበቅ፣ የት ገቡ? ምን ሆኑ? ብሎ ማለት ያለበት ማነው? የማይገባኝ ደግሞ ይኼ ነው፡፡ ዱሮ እንደምናውቀው አፄ ኃይለ ሥላሴ ለዚህ ነገር በራቸው ክፍት ነበር፡፡ ሠዓሊዎችን፣ ደራሲዎችን፣ አዝማሪዎችንም ይወዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ምንም የለም? በአንድ ሰው የግል ጥረት ብቻ አገር ይገነባል ወይ? የሚያበረታታቸው ማነው? ያደረግነው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ካልገባ እንዴት ሆኖ ነው ዕውቀት የሚስፋው እስቲ ሰልቁልን፣ ንገሩልን፡፡

ከአዘጋጁ፡- የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠን ማኅበሩ ለአቶ ማሞ ውድነህ ምን እያደረገላቸው እንደሚገኝ ከትናንት በስቲያ ጠይቀናቸው የሚከተለውን መልሰዋል፡፡ ‹‹መታከም የሚችሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እኔ ራሴ በአካል ሔጄ ደብዳቤውን በጸሐፊያቸው በኩል አድርሻለሁ፡፡

ጉዳዩ ግፊት እንዲደረግበትም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታው ጽፈናል፡፡ ያለምንም ማጋነን በየቀኑ ቢያንስ ሦስቴ አራቴ እንደውላለን፡፡ ክቡር ሚኒስትር አይተዋል ወይ? በአገራቸው ውስጥ የነፃ ሕክምና እንዲፈቀድላቸው ብለን ጠይቀናል፡፡ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ዛሬ እንኳን በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ግፊት ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክረን፤ ስልክ ጠብቁ ተብለናል፡፡

ማኅበራችን እጅግ አዝኗል፤ ይቻላል አይቻልም አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ እንዳንፈልግ ወደ ሚረዷቸው ሰዎች እንዳንሄድ አድርገውናል፡፡ በመሠረቱ አቶ ማሞ ውድነህ በምንም ሆነ ምን አገራቸውን አገልግለዋል፤ በሙያቸው፣ በአገር ሽማግሌነታቸው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ለአገር የሚገባውን ሁሉ አድርገዋል፡፡

እስከመቼ ድረስ ነው የኢትዮጵያ ደራስያን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች ሲሞቱ የምንለምነው? እስኪ የአገር ውስጥ ሙከራ እናድርግ ክቡር ሚኒስትሩ ሊወስኑ ይችላሉ ብንልም ለሁለት ሳምንት በሞትና በሕይወት ላይ ያለን ሰው ውሳኔ ለመስጠት ስለመቸገራቸው ማኅበራችን እጅግ ማዘኑን በይፋ እንዲገለጽልን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡